የእሁድ ታኅሣሥ 30 የተጫዋቾች የዝውውር ጭምጭምታዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እስከ ጥር 23/2015 ዓ.ም. ክፍት ሆኖ በሚቆየው የአውሮፓ ሊጎች የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ዕውቅ ተጫዋቾች ከአንድ ክለብ ወደ ሌላኛው ሊዘዋወሩ እንደሚችሉ ጭምጭምታዎች እየተሰሙ ነው።
ጃኦ ፌሊክስ፣ ሚካሄሎ ሞድሪች፣ ኢንግስ፣ ፒክፎርድ፣ ትሮሳርድ . . . ክለባቸውን ለቅቀው ወደ ሌሎች ክለቦች ሊዘዋወሩ እንደሚችሉ መረጃዎች እየወጡ ነው።
ጃኦ ፌሊክስ
የአትሌቲኮ ማድሪዱ የፊት መስመር ተጫዋች ጃኦ ፌሊክስ ስሙ ከማንችስተር ዩናይትድ እና አርሰናል ጋር ተያይዞ በስፋት እየተነሳ ይገኛል።
ዩናይትድ የፊት መስመሩን ለማጠናከር፤ አርሰናል ደግሞ በትክክልም ሊጉን የማሸነፍ እቅድ ካለው ጃኦ ፊሊክስ ከአትሌቲኮ ማዘዋወር ይጠበቅባቸዋል እየተባለ ነው።
ይሁን እንጂ ሁለቱም የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ተጫዋቹን በውሰት ለመውሰድ ከአትሌቲኮ ማድሪድ በቀረበው ዋጋ ደስተኛ አይደሉም።
አትሌቲኮ ለስድስት ወራት ውሰት 9.5 ሚሊዮን ፓዎንድ ተከፍሎት ተጫዋቹን የሚወስደው ክለብ ሙሉ ደሞዙን መሸፈን አለበት በሚል አቋም ጸንቷል።
ሰንደይ ሚረር እንደዘገበው ከሆነ ማንችስተር ዩናይትድ ፖርቹጋላዊውን አጥቂ መውሰድ ከፈለገ ለውሰት ዝውውሩ 9.5 ሚሊዮን ፓዎንድ፤ እንዲሁም ከውሰቱ በኋላ ተጫዋቹን በ70 ሚሊዮን ፓዎንድ ለመግዛት መስማማት እንደሚኖርበት አትሌቲኮ አስታውቋል።
ሚካሄሎ ሙድሪክ
ቼልሲ እና አርሰናል ሚካሄሎ ሙድሪክን ለማስፈረም ጽኑ ፍላጎት እንዳላቸው ባለፉት ቀናት ሲዘገብ ቆይቷል።
አርሰናል ይህን ተጫዋች ለማስፈረም ያቀረበው ይፋዊ ጥያቄ በክለቡ ሻካታር ዶኔስክ ውድቅ ተደርጓል።
አርሰናል የ22 ዓመቱን የክንፍ ተጫዋች ወደ ኢሚሬትስ ለማምጣት ለሻካታር ያቀረበው 88 ሚሊዮን ፓዎንድ ተቀባይነት እንዳላገኘ ፎርፎርቱ ዘግቧል።
እንደዘገባው ከሆነ ይህ የአርሰናል ጥያቄ ውድቅ ሲደረግ ይህ ለሁለተኛ ግዜ ነው። መድፈኞቹ ተጫዋቹን ለመውሰድ ቀደም ሲል ያቀረቡት 70 ሚሊዮን ፓዎንድ የሚጠጋ ገንዘብ ውድቅ ሆኗል።
ምንም እንኳ ተጫዋቹ ወደ አርሰናል የመዘዋወር ጽኑ ፍላጎቱን ማሕበራዊ ሚዲያዎች ላይ ቢያሳውቅም ቼልሲም ተጫዋቹን ለመውሰድ ውድድሩን ተቀላቅሏል።
ቼልሲ የሰሜን ለንደኑ ክለብ አርሰናል ለተጫዋቹ ለመክፈል ከሚስማማው ገንዘብ በላይ ለመክፈል ዝግጁ ስለመሆኑ ለሻካታር ስለመግለጹ ፋብሪዚዮ ሮማኖ ዘግቧል።
ቶተነሃም ደግሞ ግብ ጠባቂውን ለመቀየር አቅዷል። የ36 ዓመቱን የስፐርስ አምበል የሆነውን ሂዩጎ ሎሪስን ይተካል የተባለው ደግሞ የኤቨርተን እና የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ ጆርዳን ፒክፎርድ ነው።
ፒክፎርድ በወረጃ ቀጠና የሚገኘውን ክለቡን ለቅቆ በአውሮፓ ጨዋታዎች የመሳተፍ ዕድል ወደሚሰጠው ቶተነሃም የመሄድ ፍላጎት ይኖረዋል ተብሏል።
ክርስቲያል ፓላስ እና ኤቨርተን ዳኒ ኢንግስን ከአስቶን ቪላ ለማስፈረም ፍላጎት ማሳየታቸውን ሰን ዘግቧል።
ከዓለም ዋንጫ በኋላ ቪላ በአዲሱ አሰልጣኝ ኡናይ ኢምሪ ስር ባደረጋቸው ሦስት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ዳኒ ኢንግስ ተሰልፎ አልተጫወተም።
የፓላስ አሰልጣኝ ፓትሪክ ቪዬራ ፓላስ የ30 ዓመቱን አጥቂ በውሰት ከተቻላቸው ደግሞ በቋሚ ዝውውር ወደ ለንደኑ ከለብ የማምጣት ጽኑ ፍላጎት አለው።
ተጫዋቹን በውሰት ለመውሰድ ፈልጎ ያልተሳካለት ኤቨርተን ተጫዋቹን በቋሚ ዝውውር ለማስፈርም ጥረት ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።
ምርጥ አቋም ላይ የሚገኘው ትሮሳርድ ብራይተንን ሊለቅ ይችላል የሚል መረጃ በወጣበት ግዜ ከቋሚ አሰላለፍ ውጪ ተደርጓል።
የብራተን ኤንድ ሆቭ አልቢየን አሰልጣኝ ሮቤርቶ ዲ ዜርቢ ከተጫዋቹ ብዙ እንደሚጠብቁ መናገራቸውን ዘ አትሌቲክ ዘግቧል።
ቤልጂየማዊው ትሮሳርድ ወደ ኒውካስል ወይም ቸልሲ ሊያመራ ይችላል ተብሏል።












