ፕሬዝዳንቱ እላያቸው ላይ ሲሸኑ በሚያሳየው ቪዲዮ ምክንያት 6 ጋዜጠኞች ታሰሩ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር እራሳቸው ላይ ሲሸኑ የሚጠቁመው ተንቀሳቃሽ ምስል በስፋት መዘዋወሩን ተከትሎ ስድስት ጋዜጠኞች በቁጥጥር ሥር ዋሉ።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት በማሕበራዊ ሚዲያዎች ላይ በስፋት ሲዘዋዋር የነበረው ቪዲዮ ፕሬዝዳንት ኪር የአገሪቱ ብሔራዊ መዝሙር እየተዘመረ ሳለ እራሳቸው ላይ ሲሸኑ አሳይቷል።
ይህን ተከትሎም 6 የደቡብ ሱዳን ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ሠራተኞች በዚህ ሳምንት በቁጥጥር ሥር ውለዋል።
ተንቀሳቃሽ ምስሉ በስፋት ከተጋራ በኋላ ኪር አገር መምራት የሚያስችል የጤና አቋም ላይ አይገኙም በሚል ከሥልጣን እንዲወርዱ አስተያየት ሲሰጥ ነበር።
የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቹ (ሲፒጄ) የሚዲያ ባለሙያዎቹ ከእስር እንዲለቀቁ ጠይቋል።
የደቡብ ሱዳን የጋዜጠኞች ማሕበር ፕሬዝዳንት ፓትሪክ ኦዬት ለሮይተርስ እንደተናገረው ከሆነ ስድስቱ የሚዲያ ባለሙያዎች “ፕሬዝዳንቱ እራሳቸው ላይ ሲሸኑ የሚያሳየው ተንቀሳቃሽ ምስል እንዴት ሊወጣ እንደቻለ ያውቃሉ በሚል ተጠርጥረዋል”።
የደቡብ ሱዳን ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ይህ በስፋት የተጋራው ተንቀሳቃሽ ምስልን አላስተላልፍኩም ብሏል።
የሲፒጄ የሰሃራ በታች ተወካይዋ ሙቶኪ ሙሞ እስሩ ባለስልጣናት ያላስደስታቸው ነገር ሲሰራጭ በጸጥታ አካላት አማካይነት የሚደርግ እስር አይነት ነው ብለዋል።
ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ X ይዘት መጨረሻ
በቁጥጥር ስር ከዋሉት ስድስት የሚዲያ ባለሙያዎች መካከል 3ቱ የካሜራ ባለሙያዎች ናቸው። ሙቶኪ ጋዜጠኞቹ ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ ከእስር እንዲለቀቁ ጠይቀዋል።
የደቡብ ሱዳን ኢንፎርሜሽን ሚንስትር ማይክል ማኩይ በበኩላቸው ጋዜጠኞቹ የታሰሩበትን ምክንያት ለማወቅ ሕዝቡ መጠበቅ እንዳለበት ለአሜሪካ ድምጽ ተናግረዋል።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በተደጋጋሚ የደቡብ ሱዳን ባለስልጣናት ጋዜጠኞችን ከማዋከብ እንዲቆጠቡ ሲጠይቁ ቆይተዋል።
ሳል ቫኪር እአአ 2011 ላይ ደቡብ ሱዳን ከሱዳን ተነጥላ አገር ከሆነች ጀምሮ አገሪቱን በፕሬዝዳንትነት ሲመሩ ቆይተዋል።
ደቡብ ሱዳን ባለፉት ዓመታት በግጭት፣ በፖለቲካዊ ቀውስ፣ በረሃብ እና በተፈጥሯዊ አደጋዎች ስትታመስ ቆይታለች።












