ያልተገደበ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ወደ ትግራይ ምን ያህል እየደረሰ ነው?

የእርዳታ እህል ሲከፋፈል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከወልቃይት የተፈናቀሉት አለቃ ገ/መድኅን ገብረዋህድ የሰባት ቤተሰብ አስተዳዳሪ ሲሆኑ በሰሜን ምዕራብ ትግራይ በጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ ይገኛሉ።

በነሐሴ ወር ለእያንዳንዳቸው 15 ኪሎ ግራም፣ 1.5 ሊትር ዘይት (ለአምስት አባላት) እና አንድ ኪሎ ግራም ክክ እርዳታ እያገኙ ነበር። አሁን ግን የሚሰጠኝ ዕርዳታ በቂ አይደለም ሲሉ ያማርራሉ።

“ይሄ ግን ምንድን ነው? ከዚሁ ውስጥ ነው የምናስፈጨው። ጨውና በርበሬ ከእርሱ ነው። ይሄ ምን ሊባል ይችላል። ከቀድሞው የተሻለ ነገር አይደለም፣ በእርግጥ በነሐሴ ወር ሲሰጠን የነበረው የተሻለ ነበር” ይላሉ።

ቅሬታቸውን የሚሰማ እንደሌለም ሲያስረዱ “ብትጮህ ማንም አይሰማህም።. . . ሕዝቡ በእውነት በሐዘን ላይ ነው። ስሜታችን ተጎድቷል። በልተን አይደለም እየኖርን ያለነው። በእርግጥ ሰው መሆናችን የማይለይበት ደረጃ ላይ ደርሰናል” ብለዋል።

አብዛኞቹ የጤና እክሎች ያለባቸው መሆኑን በተለይ ስር የሰደደው በሽታ ያለባቸው ደግሞ መድኃኒት እንደማያገኙ ጨምረው ያስረዳሉ።

በጥቅምት ወር 2013 ዓ.ም ጦርነቱ ሲጀመር ከሁመራ ከተማ የተፈናቀለው ግደይ በበኩሉ፣ ከመቀሌ 70 ካሬ ሜትር አካባቢ በጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ እንደሚገኝ ተናግሯል።

በመጠለያው ውስጥ ብቻ ከ16,000 በላይ የተፈናቀሉ ሰዎች እንዳሉ የሚናገረው ግደይ፣ የምግብ እርዳታ በቅርቡ መሰጠት መጀመሩን ተናግሮ ይቀጥላል የሚል ተስፋ እንዳለው አስረድቷል።

እስካሁን ሦስት ጊዜ በወር 15 ኪሎ ግራም ተሰጥቷል የሚለው ግደይ፣ በምዕራብ ትግራይ ሁለት ልጆቹን፣ በአድዋ ከተማ ደግሞ አንዲት ሴት ልጁን ትቶ መምጣቱ ለቢቢሲ ገልጿል።

“ስንፈናቀል ተለያይተን ስለነበር ነው። አሁን ግን ተጨንቄያለሁ። ሁለት ዓመታት ሙሉ እዚያ የቀሩት ልጆቼ እርዳታ አላገኙም” የሚለው ግደይ ለመጀመሪያ ጊዜ በስልክ ያነጋገራቸው በቅርቡ ነው።

ለግደይ ድምጻቸውን መስማቱ ተስፋ ቢሆነውም ምን በልተው ነገን ይሻገራሉ የሚለው ነገር አስጨንቆታል።

በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መሪዎች መካከል የተፈረመው የሰላም ስምምነት መካከል ያልተገደበ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ማድረስ ይገኝበታል።

ስምምነቱ ከተፈረመ ሁለት ወራት አልፎታል፣ እስከ አሁን የስልክና የባንክ አገልግሎት መስጠት የጀመረ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ክልሉ የሚያደርገውን በረራ ጀምሯል።

እርዳታ ወደ ክልሉ በአራት አቅጣጫዎች (ከአማራ እና ከአፋር ክልል) እየገባ መሆኑ የሚነገር ሲሆን፣ በፀጥታ ችግር ምክንያት ዕርዳታ ያልደረሰባቸው ቦታዎች እንዳሉ የእርዳታ ሠራተኞች ይናገራሉ።

ወደ ትግራይ የእርዳታ አቀርቦት የሚያጓጉዙ ተሽከርካሪዎች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ወደ ትግራይ የተጓጓዘ እርዳታ

ለሁለት ዓመታት በቆየው ጦርነት በክልሉ ሁሉም የመንግሥት አገልግሎቶች ተቋርጠው የቆዩ ሲሆን፣ ዶክተሮች እና የመንግሥት ሠራተኞች ሳይቀሩ ለከፍተኛ ረሃብ እና ለልመና ተጋለጠው መቆየታቸው ይነገራል።

በአጠቃላይ በክልሉ ከ5.4 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የአስቸኳይ ጊዜ ርዳታ በመጠባበቅ ላይ እንዳሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ ያመለክታል። ከእነዚህ መካከል ከ2.3 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት በጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ ይገኛሉ።

የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት እና ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች ከኅዳር 15 እስከ ታኅሣሥ ባለው ጊዜ ከ100 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ የእርዳታ እህል በክልሉ ማከፋፈላቸውን የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት (ኦቻ) አስታውቋል።

ከዚህ ውስጥ ከ15 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ የሚሆነው ከኢትዮጵያ መንግሥት የተገኘ መሆኑን፣ በኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት አመራር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት አቶ ደበበ ዘውዴ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ለእርዳታ ተደራሽ ያልሆኑ አካባቢዎች

የረድኤት ሠራተኞች ለቢቢሲ እንደተናገሩት የሰሜን ምዕራብ ትግራይ፣ ደቡብ ትግራይ እና መካከለኛው ትግራይ ተደራሽ እንዳልሆኑና የእርዳታ ድርጅቶች በአካባቢው ያለቸው እንቅስቃሴ ውስን መሆኑን ይናገራሉ።

“በአሁኑ ወቅት ዋናው ችግር በርካታ የትግራይ አካባቢዎች ለዕርዳታ ድርጅቶች ተደራሽ አለመሆኑ ነው” ሲሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ አንዲት የረድኤት ሠራተኛ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የረድኤት ድርጅቶች ሊደርሱባቸው ካልቻሉት መካከል ሰሜን ምዕራብ ትግራይ እና የመካከለኛው ትግራይ አካባቢዎች በኢትዮጵያ ጦር፣ በኤርትራ ጦር እና በአማራ ጦር ቁጥጥር ስር ያሉ ናቸው።

የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ግን መንግሥት አድዋ፣ አክሱም እና ሽሬን ጨምሮ በከተሞች እርዳታ እያከፋፈሉ መሆናቸውን ዘግበዋል።

በደቡባዊ ዞን ደግሞ ከዋና መንገዶች ውጪ ያሉ ወረዳዎች እና ተደራሽ ያልሆኑ ቦታዎች አሁንም ዕርዳታ ለማድረስ ፈታኝ መሆኑን ኦቻ ይገልጻል።

እርዳታ የሚጠብቁ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, AFP

ለተረጂዎች የደረሰ እርዳታ

ባለፈው ዓመት ከመጋቢት እስከ ሐምሌ ጦርነት ባልነበረበት ወቅት አንድ ዙር ሲሰጥ ሁለተኛው ዙር በቅርቡ ከኅዳር እስከ ታህሳስ ወር መሰጠቱን መረጃዎች ገልጸዋል።

የእርዳታ ጠባቂ ሰዎች (በተለይ በመጠለያ ውስጥ ያሉት) በየወሩ እርዳታ ማግኘት እንደነበረባቸውና እስካሁንም ስድስት ዙር ማግኘት ይገባቸው ነበረ ሲል አንድ የእርዳታ ሠራተኛ ተናግሯል።

ጦርነቱን ተከትሎ በክልሉ ከፍተኛ የሆነ ረሃብ እንዳለ ገልጾ ችግሩ ግን ባለፈው ዓመት በቂ ትኩረት እንዳልተሰጠው ተናግሯል።

በጥቅምት ወር መጀመሪያ ላይ በጀመረው በሁለተኛው ዙር የምግብ ሥርጭት ከ3.3 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ የክልሉ ነዋሪዎች፣ ማለትም 61 በመቶ የሚሆኑት የሰብአዊ እርዳታ ድርጅቶች ድጋፍ ማድረጋቸውን የኦቻ መረጃ አመልክቷል።

እንዲሁም ወደ አንድ ሚሊዮን ሊትር የሚጠጋ ነዳጅ ወደ ክልሉ መግባቱን በሪፖርቱ ላይ ተጠቅሷል።

ግደይም ሆነ አለቃ ገ/መድኅን ወደ ቤታቸው የሚመለሱበት ሁኔታ ቢመቻችላቸው ደስተኞች ናቸው።

“እጅግ መጥፎ ሁኔታ ላይ ነው ያለነው። ‘ዛሬ ተመልሳችሁ መምጣት ትችላለሁ’ ብንባል አንድ አናድርም ነበር። ነገ ተጉዘን በነጋታው ቤታችን እንገባለን። ምክንያቱም ያለንበት ሁኔታ ​​​​በጣም አሳሳቢ ነው” ይላሉ አለቃ ገብረ መድኅን።

“ወደ ቀዬችን በሰላም መመለስ እንፈልጋለን። ችግሩን እየተቋቋምን ነው። ወደ ቤት ተመልሰን ከቤተሰቦቻችንን ጋር መገናኘት እንፈልጋለን። ጤነኛ አእምሮ፣ የሚሰሩ እጆች እና እግሮች ይዘን፤ ልመና ላይ ያለን ነው የሚመስለው” ያለው ደግሞ ግደይ ነው።