በትግራይ ለ2.2 ሚሊዮን ሰዎች እርዳታ ማድረሱን ተመድ ገለጸ

እርዳታ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ዩኤን ኦቻ) ከኅዳር መጀመሪያ 2015 ዓ.ም. ወዲህ በትግራይ ክልል ከ2.2 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ሰዎች እርዳታ እንዳደረሰ ገለጸ።

በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት ከተደረሰ ወዲህ እርዳታ ወደ ትግራይ እየገባ እንደሚገኝና ከኅዳር መጀመሪያ እስከ ታኅሣሥ መጨረሻ ድረስ ከ3,000 በላይ ምግብ፣ የሕክምና፣ መጠለያ፣ ውሃ እና ሌሎችም ቁሳቁሶች የያዙ የጭነት መኪናዎች በአራት ኮሪደሮች በኩል ትግራይ እንደደረሱ ኦቻ ትላንት እሮብ ታኅሣሥ 27 ቀን 2015 ዓ. ም ባወጣው መግለጫ አሳውቋል።

የሕክምና እና የተመጣጠነ ምግብ ደግሞ በአየር ጭምር ወደ ክልሉ እንደተላከም ተገልጿል።

ከኅዳር ወዲህ ምግብ ከ2.2 ሚሊዮን በላይ ለሆኑ ሰዎች ማከፋፈሉን የገለጸው ኦቻ፣ በአንዳንድ የሰሜን ድንበር አካባቢዎች እና ከዋና መንገድ ወጣ ያሉ ቦታዎች ለመድረስ ግን ፈታኝ መሆኑን ጠቅሷል።

“የተመጣጠነ ምግብ እጥረት አሁንም አስጊ ሆኖ ቀጥሏል። ባለፈው ታኅሣሥ ምርመራ ከተደረገላቸው ሕጻናት አንድ ሦስተኛው የተመጣጠነ ምግብ እጥረት የገጠማቸው ሲሆኑ ከመካከላቸው 4 በመቶ ያህሉ በከፍተኛ ሁኔታ የተመጣጠነ ምግብ ያላገኙ ናቸው” ይላል መግለጫው።

በትግራይ መሠረታዊ አገልግሎቶች በመመለስ ረገድ መሻሻሎች እንዳሉ የተመድ መግለጫ ጠቅሶ፣ በዚህም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ መቀለ እና ሽረ በረራ መጀመሩን፣ የባንክ አገልግሎት በአንዳንድ የትግራይ አካባቢዎች መጀመሩን፣ የቴሌኮምንኬሽን እና የመብራት አገልግሎት መጀመር አበረታች እንደሆነም አክሏል።

ሆኖም ግን የባንክ አገልግሎት በአጠቃላይ አለመጀመሩ፣ የሕዝብ መጓጓዣ እና የንግድ መገልገያዎች አለመጀመራቸውንም እንደመሰናክል ጠቅሷል።

“በአፋር እና በአማራ ክልሎች ያለው የሰብዓዊ እርዳታ ፍላጎት አሁንም ከፍተኛ ነው። ምግብና ሌሎች ድጋፎች ቢቀጥሉም ነዋሪዎች ወደ ቀያቸው የተመለሱባቸው አካባቢዎችን ጨምሮ በሌሎችም አካባቢዎች ክፍተቶች ይስተዋላሉ” ተብሏል በመግለጫው።

ከሰሜኑ የርስ በርስ ጦርነት ባሻገር በምሥራቅ እና በደቡብ የአገሪቱ ክፍሎች ድርቅ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንዳሳደረባቸውም በመግለጫው ተጠቅሷል። በአፍሪካ ቀንድ በድርቅ ሳቢያ 12 ሚሊዮን ሰዎች የምግብ እጥረት እንደሚገጥማቸውና 8 ሚሊዮን ሰዎች የውሃና ንጽህና መጠበቂያ ድጋፍ እንደሚያሻቸው ተገልጿል።

ከዚህ ባሻገር በኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልሎች የተነሳው ኮሌራ አሁንም አስጊ እንደሆነ የኦቻ መግለጫ አክሏል።