ከሰሞኑ በኢትዮጵያ ለምን ቅዝቃዜ በረታ?

ብርድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ለደብረ ብርሃን ብርድ እንግዳ አይደለም።

ቅዝቃዜ ለከተማዋ ቤተኛ ለመሆኑ ከደብረ ብርሃን ብርድ ልብስና ከደብረ ብርሃን አረቄ በላይ ምስክር የለም።

የዘንድሮው ግን ‘የተለየ ነው’ ይላሉ የከተማዋ ነዋሪዎች።

ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚስተጋባው አስተያየትም ቅዝቃዜው መበርታቱን ያሳብቃል።

በደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲ የአማርኛ ቋንቋና ሥነ ጽሑፍ መምህርት ሠርካለም ይገረሙ (ዶ/ር) ከቤት የምትወጣው ሁለት ሱሪ ደራርባ፣ በካናቴራ ላይ ካናቴራ በላዩ ላይ ደግሞ ሹራብና ጃኬት ጨምራ ነው። ከብርዱ ግን አላስጣላትም።

“አሁን ራሱ ብርዱን መቋቋም አቅቶኝ በእኩለ ቀን ከቢሮ ወደ ቤት መጥቻለሁ። በዚህ ሰዓት የቧንቧ ውሃ ብትከፍቺ እጅሽን መልሰሽ መጨበጥ ያቅትሻል። ቆፈን ስለሚይዝሽ እጅሽንም እግርሽንም ይጨመድድሻል። ጠዋት ግቢ ውስጥ በረዶ ሠርቶ ነው የምታገኝው” ትላለች።

ለወትሮውም ከጥቅምት እስከ ጥር ድረስ ቤት ውስጥ ከሰል አያይዘው፣ ጋቢ ደርበው ነው የሚቀመጡት። ዘንድሮ ግን ብርዱን ‘የሚያሸንፍ ኃይል’ አላገኘንም ትላለች። “በዚህ እቋቋመዋለሁ የሚባል ብርድ አይደለም የዘንድሮው” ብላለች መምህርቷ።

“ቤትም ይቀዘቅዛል፣ ውጭም ይቀዘቅዛል፣ ደራርበሽም ይቀዘቅዛል፣ ክፍል ውስጥ ሳስተምርም ይቀዘቅዛል፣ በተለይ ንጋት ከ11 ሰዓት እስከ 2 ሰዓት ፀሐይ ሆኖ ራሱ ንፋስ አለ፤ ከአምናውም ከካቻምናውም የተለየ ነው። የሚገርመው ደግሞ ፀሐዩ ለምን እንደሆነ እንጃ ሲነካሽ በጣም ያቃጥላል። ትንሽ ጥላ ስታገኚ ደግሞ ቅዝቃዜው ያንዘፈዝፋል። በቃ ‘አጥንት የሚሰብር ብርድ’ የሚለው ነው የሚገልጸው” ስትል ነው የሰሞኑን ብርድ የምትገልጸው።

የአዲስ አበባ ነዋሪዎችም በትዊተር እና በፌስቡክ ‘የዘንድሮው ዓይነት ብርድ አይተን አናውቅም’ እያሉ ነው። በተለይ ደግሞ ንጋት ላይ ያለው ቅዝቃዜ።

ካለፉት ዓመታት አንጻር የዘንድሮው ቅዝቃዜ የተለየ ነው? ብርዱ የተለያዩ አገራትን ተሰምቷቸው የማያውቅ ቆፈን ውስጥ የከተተው የአየር ንብረት ለውጥ ያመጣው ይሆን? ስንል በኢትዮጵያ ሜትሮሎጂ ኢንስቲትዩት፣ የሜትሮሎጂ ትንበያና ቅድመ ማስጠንቀቂያ መሪ ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት ዶ/ር አሳምነው ተሾመን ጠይቀናለ።

ዶ/ር አሳምነው እንደሚሉት፣ እስካሁን በመዘገቡት መረጃ መሠረት የዘንድሮው ቅዝቃዜ በኢትዮጵያ የበጋ ወቅት ከሚጠበቀው የተለየ አይደለም።

በእርግጥ የማለዳና ሌሊት ቅዝቃዜ የሚበረታባቸው አካባቢዎች አሉ። የእነ ዶ/ር ሠርካለም ደብረ ብርሃን በግንባር ቀደምነት ትጠቀሳለች።

ባለፉት ቀናት (ከታኅሣሥ 24 እስከ ታኅሣሥ 26 ባሉት) በደብረ ብርሃን -1.2 ዲግሪ ሴልሸስ ነበር የቀኑ ዝቅተኛ የሙቀት መጠን።

በ24 ሰዓት ውስጥ የቀኑ ዝቅተኛ ሙቀት መጠን ከ0 በታች ሆኖ ከተመዘገበባቸው ሌላዋ ሐረር ናት። በሐረር ከ0 በታች 0.2 ዲግሪ ሴልሸስ ተመዝግቧል።

በአንጻሩ በአዲስ አበባ ለብዙ ቀናት ከ5 ዲግሪ ሴልሸስ በታች አልተመዘገበም። የቀኑ ዝቅተኛ የሙቀት መጠን ከ5 እስከ 7 ዲግሪ ሴልሸስ ሆኖ ቆይቷል።

በተቃራኒው፣ በወገል ጤና፣ ባቲ፣ አምባ ማርያም፣ ደባርቅ፣ ንፋስ መውጫ፣ ጅማ፣ ባሌ ሮቤ እና ሆሳዕናን በመሰሉ አካባቢዎች የቀኑ ዝቅተኛ የሙቀት መጠን ከ5 ዲግሪ ሴልሸስ በታች ሲሆን፣ በጥቂት ቦታዎች ደግሞ ከ0 ዲግሪ ሴልሸስ በታች ተመዝግቧል።

እንዲህ ያለ ቅዝቃዜ መነሻው ምንድን ነው? ለሚለው ጥያቄ ዶ/ር አሳምነው ማብራሪያ አላቸው።

የበጋ ብርድ

ብርድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የኢትዮጵያ ክረምት፣ በጋ እና በልግ እያንዳንዳቸው አራት ወራት አላቸው። ከጥቅምት እስከ ጥር የሚዘልቀው በጋ፣ ለደቡብ አጋማሽ ኢትዮጵያ ማለትም ለሶማሌ ክልል፣ ለደቡብ ኦሮሚያ ቆላማ ስፍራዎች ማለትም ለጉጂ እና ቦረና፣ ለሲዳማ ክልል፣ ለደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል፣ ለጋሞ ጎፋ፣ ለኮንሶ እና ለደቡብ ኦሞ ሁለተኛው የዝናብ ወቅታቸው ነው።

ሌሎቹ የአገሪቱ አካባቢዎች ግን በጋ ላይ ደረቅ፣ ፀሐያማና ነፋሻ ናቸው።

ደቡብ ምዕራብ እና ምዕራብ የኢትዮጵያ ክፍል ከስምንት እስከ ዘጠኝ ወራት ዝናብ ስለሚያገኙ እስከ ኅዳር መጨረሸና ታኅሣሥ መጀመሪያ ድረስ ዝናብ ይቀጥላል።

ዘንድሮ፣ በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው የሆኑ አካባቢዎች ከመደበኛው ያነሰ ዝናብ እንደሚኖራቸውና በቀሪው የአገሪቱ ክፍል በተለይም በአብዛኛው ትግራይ፣ አማራ፣ አፋር፣ ምሥራቅና መካከለኛው ኦሮሚያ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ፀሐያማና ነፋሻማ እንደሚሆኑ ነው የተተነበየው።

“በጋም፣ በልግም፣ ክረምትም በውቅያኖሶች በሚፈጠር የአየር ሁኔታ ገጽታ እና በየብስ በሚፈጠር የአየር ሁኔታ ገጽታ ምክንያት አሉታዊ እና አወንታዊ ተጽዕኖ ያድርባቸዋል” ይላሉ ዶ/ር አሳምነው።

አሁን ያለንበት የበጋ ወቅት የሌሊትና የማለዳ ቅዝቃዜ የሚጨምርበት ነው። በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች የቀኑ ዝቅተኛ የሙቀት መጠን ከ5 ዲግሪ ሴልሸስ ወይም ከ0 ዲግሪ ሴልሸስ በታችም የሚሆንበት ጊዜ እንዳለም ያስረዳሉ።

ከሰሞኑ የተስተዋለው ቅዝቃዜ መነሻውም ይኸው ነው።

ዶ/ር አሳምነው እንደሚያስረዱት፣ ከሳይቤርያ በመነሳት የአውሮፓ አገራትን በማቆራረጥ ወደ ኢትዮጵያ የሚነፍሰው ወይም የሚገባው ደረቅና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ በብዙ የአገሪቱ አካባቢዎች የሌሊትና ማለዳ ቅዝቃዜ እንዲጨምር አድርጓል።

የዘንድሮው ቅዝቃዜ የተለየ ነው?

ዶ/ር ሠርካለምን ጨምሮ በርካቶች የዘንድሮው ብርድ እንደበረታ ይሰማቸዋል። ‘ከ0 ዲግሪ ሴልሸስ በታች ገብቷል’ ሲሉ በማኅበራዊ ሚዲያ የጻፉም አሉ።

በባለሙያው ዕይታ ግን “ዘንድሮ በጣም ቀዝቅዟል የሚል ግምገማ የለንም”።

የቀኑ ዝቅተኛ የሙቀት መጠን ከ0 ዲግሪ ሴልሸስ በታች ሆኖ የሚመዘገብባቸው አካባቢዎች ቀድሞውኑም እንዳሉ ያስረዳሉ።

በዘንድሮው በጋ፣ ብዙ ቀናት የቆየ የደመና ሽፋን (የደመና ክምችት) ነበር። ያ ሲሆን የቀኑ ዝቅተኛ የሙቀት መጠን ከ5 ዲግሪ ሴልሸስ በታች ወርዶ አይስተዋልም።

“ያለፉትን ዓመታት የበጋ ወቅት ስንመለከት፣ ለብዙ ቀናት ያን ያህል የተጠናከረና የተስፋፋ የደመና ሽፋን ስላልነበረ የቀኑ ዝቅተኛ የሙቀት መጠን በምሥራቅ አማራ እና አዲስ አበባን ጨምሮ በማዕከላዊ የአገሪቱ አካባቢዎች እንዲሁም በደቡብ ደጋማ የአገሪቱ ክፍሎች ባለፉት በጋዎች ከ0 ዲግሪ ሴልሸስ በታች የተመዘገበባቸው ቀናት በርካታ ነበሩ” ሲሉ ያስረዳሉ።

ዘንድሮ ግን በጥቂት ቀናት ውስጥ በደብረ ብርሃን ለአራት ቀናት እና በሐረር ለአንድ ቀን ከ0 ዲግሪ ሴልሸስ በታች ተመዝግቧል።

“የዘንድሮው በጋ ከሌሎቹ ቀዝቃዛ ነው የሚል መረጃ አልተሰበሰበም። የሌሊትና የማለዳ ቅዝቃዜ ግን ተስተውሏል። በጣም ጠንካራ ነው፣ ቀዝቃዛ ነው ባንልም” ሲሉ ያክላሉ።

በአንዳንድ አካባቢዎች ከ0 በታች የቀኑ ዝቅተኛ ሙቀት መጠን -2 ወይም -3 በሚሆንበት ጊዜ አነስተኛ የበረዶ ቅንጣቶች (frost) እንደሚከሰት ገልጸው፣ በዘንድሮ በጋ ግን ያን ያህል የበረዶ ቅንጣቶች እንዳልተስተዋሉ ይገልጻሉ።

የማለዳና ሌሊት ቅዝቃዜ

በብዙ አካባቢዎች ሌሊትና ማለዳ የቀኑ ዝቅተኛ የሙቀት መጠን (minimum temperature) የሚመዘገብባቸው ናቸው።

ብዙዎችን ያስቸገረውም ይህ ቅዝቃዜም ነው።

በተለይም የአረብ ባሕር፣ የቀይ ባሕር እና የሜዲትራኒያን ባሕር ዝቅተኛ የአየር ግፊት በመፈጠሩ ምክንያት ወደ ኢትዮጵያ እርጥበት አዘል የአየር ሁኔታ ሲገባ እንደነበር ዶ/ር አሳምነው ያስረዳሉ።

ይህ ነው በብዙ የአገሪቱ አካባቢዎች የደመና ሽፋን የፈጠረው። ይህም የሌሊትና ማለዳ ቅዝቃዜን ያባብሳል።

ዘንድሮ ጥቅምት እና ኅዳር ላይ በብዙ አካባቢዎች ዝናብና የደመና ሽፋን እንደነበረና በተለይም የበጋ የመጨረሻ ወር በሆነው ጥር ቅዝቃዜ እንደሚጨምር የትንበያ መረጃዎች ያሳያሉ።

የአየር ንብረት ለውጥ በኢትዮጵያ

ባለፉት ሳምንታት በአሜሪካ እንዲሁም በካናዳ አንዳንድ አካባቢዎች በተነሳው ከባድ ቅዝቃዜ እና የክረምት ወጀብ ምክንያት የሰዎች ሕይወት አልፏል፤ በረራ ተቋርጧል፣ የኤሌክትሪክ አገልግሎት የተቋረጠባቸውም ነበሩ። ባለፉት አሠርታት ከታየው የከፋ ወጀብ ተብሎ ተመዝግቧል።

በሌሎች የዓለም ክፍሎችም ከፍተኛ ቅዝቃዜ ወይም ከፍተኛ ሙቀት አልያም የዝናብ መዛባት፣ ድርቅ ወዘተ ተስፋፍቷል። ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ ቀንድ በአሠርት ያልታየ ድርቅ ሚሊዮኖችን ለስቃይ ዳርጓል።

ለዚህ ሁሉ ተጠያቂው የአየር ንብረት ለውጥ ነው ይላሉ ባለሙያዎች።

ዶ/ር አሳምነውን፣ የአየር ፀባይ መለወጥ (climate change) እና የአየር ፀባይ መዋዠቅ (climate variability) በኢትዮጵያ ተጽዕኖ ያሳደረባቸውን አካባቢዎች ጠይቀናቸዋል።

በተለይም በደቡብ አጋማሽ የአገሪቱ ክፍል፣ በሶማሌ ክልል፣ በሐረር፣ በድሬዳዋ በደቡብ ኦሮሚያ ቆላማ አካባቢ ማለትም በጉጂ እና ቦረና፣ በተወሰኑ የባሌ አካባቢዎች፣ በሲዳማ ክልል፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል፣ በጋሞ ጎፋ ዞን፣ በኮንሶ፣ በኦሞ፣ በጂንካ እና በምሥራቅ አማራ አካባቢዎች ችግሩ ጎልቶ ይታያል።

ባለፉት አምስት ተከታታይ ወቅቶች ዝናቡ ከመደበኛው በታች በመሆኑ ከዝናብ መዋዠቅ ወይም ከበልግ ዝናብ መዳከም ጋር በተያያዘ በተለይም ግብርናው ላይ ጫና አሳድሮ ቀጥሏል።

የበልግና የበጋ ዝናብ ከመዋዠቁ ጋር በተያያዘ በደቡብ አጋማሽ የአገሪቱ አካባቢዎች ዝናብ አናሳ በመሆኑ አርሶ አደሮችን፣ አርብቶ አደሮችን እንዲሁም ከፊል አርብቶ አደሮችን ለእንግልት ዳርጓል።

የእንስሳት መጠጥ ውሃና የግጦሽ ሳርም ጠፍቷል።

የአየር ንብረት ለውጥ “በብዙ የአገራችን ክፍል የቀኑ ከፍተኛ ሙቀት መጠን እና የአየሩ መጠነ ሙቀት ከፍ እንዲል አድርጓል” ሲሉ ዶ/ር አሳምነው ያስረዳሉ።