አሜሪካ ላይ ከባድ ኪሳራ አድርሳለች የተባለችው ሰላይ ከ20 ዓመታት እስር በኋላ ተለቀቀች

የፎቶው ባለመብት, FBI
በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት እውቅ እና ተጽእኖ ፈጣሪ ከነበሩ ሰላዮች መካከል አንዷ የነበረችው አና ሞንቴስ ከ20 ዓመታት እስር በኋላ ተለቀቀች።
አሁን ላይ 65 ዓመት የደፈነችው አሜሪካዊቷ ሰላይ በአሜሪካ የመከላከያ ደኅንነት ኤጀንሲ እየሰራች ለሁለት አስርት ዓመታት የአሜሪካ ባላንጣ ለሆነችው ኩባ ስትሰልል ነበር።
የአሜሪካ ባለስልጣናት እአአ 2001 ላይ አና ሞንቴስ በቁጥጥር ሥር ስትውል አሜሪካ በኩባ ስለነበራት እንቅስቃሴ ሙሉ መረጃ አሳልፋ ሰጥታለች ብለው ነበር።
አንድ ከፍተኛ ባለስልጣን በአሜሪካ ከተያዙ “ከፍተኛ ጉዳት ካደረሱ ሰላዮች” መካከል ሞንቴስ አንዷ ናት ብለው ነበር በወቅቱ።
እአአ 2012 ላይ በፕሬዝዳንት ጆርጅ ደብሊው ቡሽ አስተዳደር ስር ከፍተኛ የደኅንነት ኃላፊ የነበሩት ማይክል ባን ክሊቭ ለኮንግረስ ሲናገሩ፤ በኩባ ስለምናውቀው እና በኩባ እንዴት እንደምንሰራ ሙሉ በሙሉ አጋልጣለች ብለዋል።
“ኩባውያኑ ስለእርሱ የምናውቀውን ነገር በሙሉ ያውቁ ነበር። ስለዚህ ይህን ይጠቀሙበታል።” ሲሉም ተናግረው ነበር።
ሞንቴስ በቁጥጥር ሥር ስትውል በኩባ የሚገኙ አራት የአሜሪካ ሰላዮችን ማንነት እና ከፍተኛ ሚንስትራዊ መረጃዎችን አቀብላለች ተብላ ተከሳ ነበር።
በእነዚህ ወንጀሎች የ25 ዓመት እስር የፈረዱባት ዳኛ፣ ሞንቴስ “መላ አገሪቱን አደጋ ላይ ጥላለች” ብለው ነበር።
ሞንቴስ ለኩባ ለመስራት የተስማማችው በጥቅማ ጥቅም ተደልላ ሳይሆን በምትከተለው ርዮተ ዓለም ነው ተብሎ ነበር። ሰላይዋ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሬጋን አስተዳደር በላቲን አሜሪካ ያለውን እንቅስቃሴ መቃወሟ ለኩባ የደኅንነት ተቋም እንድትሰራ ምክንያት ከሆኑት አንዱ ነው።
አና ሞንቴስ የአሜሪካ መከላከያ ደኅንነት ከፍተኛ ተንታኝ ሆና እየሰራች ከኩባ ሰላዮች ጋር ዋሽንግተን ዲሲ በሚገኙ ምግብ ቤቶች እየተገናኘች ጥብቅ ሚስጢር የያዙ መረጃዎችን ታቀብል ነበር። ከኩባ ደግሞ ትዕዛዝ የምትቀበለው በአጭር ሞገድ ራዲዮ ነበር ተብሏል።
በመጨረሻም የአሜሪካ የደኅንነት ተቋም በደረሰው ጥቆማ መሠረት ሞንቴስ እአአ 2001 ላይ በቁጥጥር ሥር ውላለች።
ሞንቴስ አሁን ላይ ከአሜሪካ እስር ቤት ብትለቀቅም ለቀጣይ አምስት ዓመታት በደኅንንት አባላት ጥብቅ ክትትል ስር የምትቆይ ይሆናል።
የኢንተርኔት አጠቃቀሟ ክትትል ይደረግበታል፤ የውጭ አገር ሰዎችን ከማግኘቷ በፊት ፍቃድ ያስፈልጋታል እንዲሁም ለአሜሪካ መንግሥት መስራት አትችልም።
ከ20 ዓመታት በፊት ሞንቴስን በቁጥጥር ሥር ያዋለው የፌደራል ቢሮ መርማሪ (ኤፍቢአይ) ባልደረባ ሰላይዋ ከአሁን በኋላ ከኩባ ጋር የመስራቷ አጋጣሚ ያበቃለት ነው ብሏል።
ፒት ላፕ ለሲቢኤስ ሲናገር፡ “ያህ የሕይወቷ አካል አብቅቷል። ለእነርሱ ያደረገችው ነገር አብቅቶለታል” ብሏል።












