የ22ኛው የኳታር የዓለም ዋንጫ የማይረሱ 12 ምስሎች እና ታሪካቸው
ምስል አቅራቢው ጌቲ ኢሜጅ ከ50 በላይ የፎቶ ባለሙያዎቹ አስደናቂ ምስሎችን እንዲያስቀሩለት ወደ ኳታር ልኮ ነበር።
ፎቶ አንሺዎቹም ለታሪክ የሚቀመጡ አስደናቂ ክስተቶችን የሚያሳዩ በሺዎች የሚቆጠሩ ምስሎችን አንስተዋል።
የጌቲ ፎቶ አንሺዎች ምርጥ የሚሏቸውን ፎቶዎች እንዲህ አጋርተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዳን ሙላን፡ ይህ ቅጽበት የሞት ሽረት የተደረገበት ነበር። በዚህ ጨዋታ ጃፓን ጀርመንን አሸንፋ ዓለም ጉድ ያለበት ነው።
በጨዋታው ማብቂያ የጀርመኑ ግብ ጠባቂ ሳይቀር የአቻነት ጎል ለማስቆጠር የተቻለው አድርጎ ነበር።
ፎቶ አንሺው ዳን ሙላን ሁለት ግብ ጠባቂዎችን በአንድ ምስል ማስቀረት ሁሌም የሚገኝ ዕድል አይደለም ይላል።
ስለዚህ ፎቶ ሌላው የመውደው ነገር ይላል ዳን፤ የትኛው ቡድን እያጠቃ የትኛው እየተከላከለ እንደሆነ ማወቅ አይቻልም።
በዚህ የምድብ ጨዋታ ጃፓን ጀርመንን 2 ለ 1 ማሸነፏ ወደ ሩብ ፍጻሜ እንድታልፍ አስችሏት ነበር። ጀርመን ደግሞ ከምድቧ ማለፍ ሳትችል ቀርታለች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ማይክል ስቲል፡ በኳታሩ የዓለም ዋንጫ ከተመዘበጉ ድንቅ፤ አስደማሚ ጎሎች አንዷ ሪቻርልሰን ሰርቢያ ላይ ያስቆጠረት ትገኝበታለች።
ፎቶግራፈሩ ማይክል ይህን ጎል ለታሪክ በምስል ያስቀረችው ደግሞ የመገናኛ ብዙኃን በሚቀመጡበት ቦታ ላይ ተዘጋጅታ የተቀመጠችው ካሜራ ናት ይላል።
ብራዚል በዚህ የመጀመሪያ የምድብ ጨዋታዋ ሰርቢያን 2 ለ 0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችላ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዴቪድ ራሞስ፡ የጌቲ ኢሚጄስ ፎቶ አንሺዎች በሜዳ ብቻ ሳይሆን ከሜዳ ውጪ የሚታዩ ክስተቶችንም በካሜራቸው አስቀርተዋል።
ይህ ምስል የጋና ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ከደቡብ ኮሪያ ጋር ጨዋታ ለማድረግ በኤጁኬሽን ሲቲ ስታዲየም እየጨፈሩ ሲገቡ ያሳያል።
ዴቪድ ራሞስ የጋና ተጫዋቾች ስታዲየም ሲመጡ የተለየ ክስተት እንደሚኖር እርግጠኛ ነበርኩ ይላል።
በመልበሻ ክፍሉ እና ከአውቶብስ ከሚወርዱበት አማካይ ቦታ ላይ ሆኖ ከተጠበቃቸው በኋላ ተጫዋቾቹ ሲጨፍሩ የሚያሳየውን አስደናቂ ምስል ማንሳቱን ይገልጻል።
ጋና ይህን ጨዋታ 3 ለ 2 ብታሸንፍም ከምድቧ ማለፍ ሳትችል ቀርታለች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሾን ቦትሪል፡ ድል ያደረጉ የቡድን አባላትን ፎቶ ግራፍ ማንሳት እንደሚያስደስት ሁሉ፤ ተሸናፊ ተጫዋችን ፎቶ ማንሳት ከባዱ የሥራ አካል ነው ይላል ፎቶግራፈር ሾን።
ከርቀት ፎቶ ማንሳት የሚያስችሉ ሌንሶችን በመግጠም ፎቶ እናነሳለን እንጂ የሐዘን ስሜት ውስጥ ያሉ ተጫዋቾች ፊት ቆሞ ፎቶ ማንሳት ከባድ ነው ይላል።
ጀርመኖች የመጀመሪያ የምድብ ጨዋታቸውን ከተሸነፉ በኋላ ከፍተኛ ጫና ውሰጥ ነበሩ። የመጨረሻ የምድብ ጨዋታቸውን ቢያሸንፉም ከውድድሩ ቀድመው ተሰናብተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ማጃ ጂቲጅ፡ ተጫዋቾች ሁሌም ከመልበሻ ክፍል ሲወጡ ልዩ ስሜትን ይፈጥራል። በተለይ ደግሞ ሜሲ ሲጫወት ተጫዋቾችን አጅበው ለሚወጡት ታዳጊዎች ሌላ ዓለም ነው።
ቡድኖች ወደ ሜዳ ከመውጣታቸው በፊት የሚጠባበቁበት ቦታ ሁሌም የካሜራ ዐይን የሚበዛበት ቦታ ነው። ስለዚህም የቀጥታ ሥርጭት ውስጥ ላለመግባት ከፍተኛ ጥንቃቄ እናደርጋለን ይላል ፎቶግራፈሩ ማጃ ጂቲጅ።
ሜሲ ለታዳጊዎች ሰላምታ ሲሰጥ ነበር። ከእርሱ በተቃራኒ የተሰለፈ ቡድንን አጅባ ለመውጣት የተዘጋጀት አንዲ ሴት ልጅ ሾልካ ወደፊት በመምጣት አድናቂው እንደሆነች ገለጸችለት።
በዚህ ቅጽበት ነበር በምስሉ እንደምትታየው ልብ የሚያሞቅ ፈገግታዋን እየቸረችው በሁለት አውራ ጣቶቿ አድናቆትን የገለጸችለት።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ላውረንስ ግሪፊታስ፡ በዚህ ውድድር አስደናቂ ተጫዋቾች ብቻ ሳይሆኑ ትኩረትን በሙሉ መስረቅ የሚችሉ ለኳስ ብቻ የተፈጠሩ የሚመስሉ ተዓምራዊ ተጫዋቾች ነበሩ። የፈረንሳዩ ኪሊያን ምባፔ ይህን መስፈርት ያሟላል።
ፈረንሳይ ከፖላንድ በነበራት ጨዋታ ሁለት ጎሎችን በማስቆጠር ድንቅ አቋም አሳይቷል።
የምባፔን ፍጥነት እና ክህሎት የሚያሳይ ፎቶ ማስቀረት ነበረብኝ ይላል ፎቶ አንሺው ላውረንስ።
የካሜራ ጥበብን በመጠቀም ይህን አስደናቂ ምስል ማስቀረት ችያለሁ ይላል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ፍራንኮይስ ኔል፡ ብራዚላውያን ጎል ካስቆጠሩ በኋላ በሚያሳዩት ድንቅ ጭፈራ ይታወቃሉ።
ኔይማን ከፍጹም ቅጣት ምት ሁለተኛውን ጎል ካስቆጠረ የቡድኑ አባላት በተለየ ዳንስ ደስታቸውን እንደሚገልጹ ቀድሜ ገምቼ ስለነበረ ካሜራን አስተካክዬ ስጠብቃቸው ነበር ይላል ፍንኪይስ ኔል።
ብራዚል በስታዲየም 974 ደቡብ ኮሪያን 4 ለ 1 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችለው ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አሌክስ ግሪም፡ ሞሮኮ የዚህ ዓለም ዋንጫ ክስተት ነበረች።
እንደ ቤልጂየም፣ ስፔን እና ፖርቹጋል ያሉ ኃያል ቡድኖችን ማሸነፍ ችላለች።
አሌክስ ግሪም ፎቶ ከማንሳታችን በፊት እንዴት ማንሳት እንዳለብን ልናቅድ እንችላለን ይላል። ነገር ግን፤ የትኛው ቡድን በደስታ ስሜት እንደሚፈነጥዝ፣ የትኛው ደግሞ ባለማመን ስሜት ፈዞ እንደሚቀር መገመት ከባድ ነው ይላሉ።
ይህ አጋጣሚ የሞሮኮ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ስፔንን ማሸነፋቸው እርግጥ ከሆነ በኋላ ደስታቸውን ሲገልጹ፤ የስፔን ብሔራዊ ቡድን አባላት ደግሞ ባለማመን ስሜት ውስጥ ሆነው በአንድ ላይ ያሳያል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ማይክል ሬጋን፡ በዚህ የዓለም ዋንጫ ጌቲ ኢሜጅስ ከጨዋታ በኋላ ወደሜዳ ገብቶ ምስሎችን እንዲወስድ ፍቃድ አግኝቶ ነበር።
እኛ ፎቶግራፈሮች ይላል ማይክል ሬጋል፤ “እኛ ፎቶግራፈሮች ወደ ሜዳ በመግባት ተጫዋቾች ጥልቅ ስሜት ውስጥ ሆነው ፎቶግራፍ ለማንሳት እንሞክራለን።”
እኔም ምባፔ ፊት ሂጄ ‘የስስስስ ኪሊያያያያንንንን’ ስለው እርሱም ወደ ካሜራዬ ሌንስ እየተመለከተ በዚህ መልኩ ደስታውን ሲገልጽልኝ ምርጥ ፎቶ ግራፍ ማስቀረት ችያለሁ ይላል።
ኪሊያን ምፓቤ በዚህ ምስል ላይ የለበሰው የክለብ አጋሩን አሽራፍ አኪሚን መለያ ልብስ ነው።
ፈረንሳይ ሞሮኮን በማሸነፍ ለፍጻሜ መድረሷ ይታወሳል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ፓትሪክ ስሚዝ፡ ፖርቹጋል ከውድድሩ መሰናበቷ እርግጥ እየሆነ ሲመጣ የሮናልዶን እያንዳንዱን ስሜታዊ እንቅስቃሴ መከታተል ዋና ትኩረቴ አድርጌ ነበር ይላል ፓትሪክ ስሚዝ።
ይህ ምስል የተነሳው ሮናልዶ ተቀይሮ ገብቶ ያገኛትን ዕድል ወደ ጎል ለመቀየር ያደረገው ጥረት ሳይሳካ ሲቀር ሲሜቱን የገለጸበትን ሁኔታ ነው።
ፖርቹጋል በሩብ ፍጻሜውን በሞሮኮ 1 ለ 0 ከተሸነፈች በኋላ ከውድድሩ መሳናበቷ ይታወሳል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አሌክሳንደር ሃሴንሰቲያን: ይህን ጨዋታ ከፍ ብሎ ከሚገኘው የመገናኛ ብዙኃን ቦታ ሆኜ እንድዘግብ ዕድል ተሰጥቶኝ ነበር።
እኔ ካለሁበት ቦታ የሜዳው አካል በሙሉ በግልጽ ይታያል። ይህም የሞሮኮው ሶፊያን ቡፋል ከእናቱ ጋራ በደስታ ሲጨፍር ፎቶግራፍ የማንሳት ዕድሉን ሰጥቶኛል።
ይህን አስደናቂ ክስተት ተጫዋቹ እና እናቱ በተቀረው ሕይወታቸው መቼም የሚረሱት አይመስለኝም።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዴቪድ ራሞስ፡ ይህ ሜሲ ዋንጫ ይዞ በሰርጂዮ አጉዌሮ ትከሻ ላይ ሆኖ የሚያሳየው ምስል ማራዶና እአአ 1986 ላይ ያደረገውን ያስታውሳል።
ሜሲ ጨንቅላቱ በግቡ አግዳሚ እንዳይመታ እየተከላከለ ቢሆንም በደስታ ስሜት ውስጥ የነበሩት አርጀንቲናውያን የምንጊዜም ምርጡ ተጫዋቻቸው ጭንቅላት አደጋ ላይ ስለመሆኑ አለማየታቸው ፈገግ የሚያስብል ክስተት ነው።












