ለክርስቲያኖ ሮናልዶ የቀረበለት ረብጣ የዝውውር ዋጋ እና ሌሎች ዜናዎች

ክርስቲያኖ ሮናልዶ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ክርስቲያኖ ሮናልዶ

የአውሮፓ ታዋቂ ክለቦች የዓለማችንን ኮከብ ተጫዋቾችን ወደ ቡድናቸው ለማካተት ከፍተኛ ገንዘብ መድበው ፍላጎታቸውን እየገለጹ ነው።

በየአገሩ ያሉ የመገናኛ ብዙኃንም ክለቦች በየትኞቹ ተጫዋቾች ላይ አይናቸውን እንደጣሉና ምን ያህል ገንዘብ ለመክፈል እንዳሰቡ እየዘገቡ ነው።

በዚህም መሠረት ከዘመናችን ከዋክብት መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀሰው የ37 ዓመቱ የማንችስተር ዩናይትድ አጥቂ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ለሁለት ዓመታት እንዲጫወት ከአንድ የሳዑዲ አረቢያ ክለብ የ300 ሚሊዮን ዩሮ የዝውውር ዋጋ ቀርቦለታል።

አያክስ ማርቲኔዝን በክለቡ ለማቆየት ያደረገው ጥረት አለመሳካቱን አምኗል። ቢሆንም ግን አያክስ ማርቲኔዝን ለሚያስፈርም ክለብ 46 ሚሊዮን ፓውንድ የዋጋ ተመን አስቀምጧል።

የፈረንሳዩ ፒኤስጅ አርጀንቲናዊውን ኮከብ ሊዮኔል ሜሲን እስከ ፈረንጆቹ 2024 ድረስ ለማቆየት የአንድ ዓመት የኮንትራት ማራዘሚያ ውል አቅርቦለታል።

የ27 ዓመቱ ጀርመናዊ የክንፍ ተጫዋች ሰርጅ ግናርቢ ስሙ ከእንግሊዙ ቼልሲ ጋር ቢያያዝም ከክለቡ ባየር ሙኒክ ጋር ውሉን ሊያራዝም ተቃርቧል ተብሏል።

ማንችስተር ሲቲ የሲቪያውን ተከላካይ ፈረንሳያዊውን ጁሊየስ ኩዋንዴን ለማስፈረም ጥናት እያደረገ መሆኑ ታውቋል። ሲቲ ይህንን የሚያደርገው ተከላካዩ ናታን አኬ ቸልሲን ከተቀላቀለ እርሱን ለመተካት ነው ተብሏል። ባርሴሎናም ኩዋንዴን ለማስፈረም ፍላጎት አሳይቷል።

የዋይኒ ሩኒው ዲሲ ዩናይትድ ከማንችስተር ዩናይትድ ጋር ኮንትራቱን ያጠናቀቀውን ጄሲ ሊንጋርድን ለማስፈረም የአሜሪካ እና የእንግሊዝ ክለቦችን በመቀላቀል ፉክክር ውስጥ ገብቷል ተብሏል።

ባርሴሎና የ33 ዓመቱን የባየር ሙኒክ የፊት መስመር ተጫዋች ሮበርት ሌዋንዶስኪን ለማዘዋወር ክፍያውን ወደ 50 ሚሊዮን ዩሮ አሳድጓል።

ሊድስ ዩናይትድ በእዚህ ዓመት ከማንችስትር ዩናይትድ ጋር የነበረው ኮንትራቱ የሚያበቃውን የ34 ዓመቱን ሁዋን ማታን ለማስፈረም ፍላጎት አሳይቷል።

የቼልሲ እና የእንግሊዝ አማካይ ማሶን ማውንት የረጅም ጊዜ ኮንትራት ለመፈረም ድርድር መጀመር ይፈልጋል ተብሏል።

የብራዚሉ ኮከብ ኔማር ምንም እንኳ ስሙ ከዝውውር ጋር ቢነሳም በእዚህ ዓመት የፈረንሳዩን ፒኤስጅ እንደማይለቅ አስታውቋል።

የፈረንሳዩ የክንፍ መስመር ተጫዋች የ25 ዓመቱ ኦስማን ደምበሌ ከባርሴሎና ጋር የ2 ዓመት ተጨማሪ ኮንትራት ሊፈራረም መሆኑ ታውቋል።

የ35 ዓመቱ ኡራጓያዊ አጥቂ ኤድሰን ካቫኒን ለማስፈረም አዲስ ወደ ጣሊያን ሴሪ ኤ ያደገው ሞንዛ ክለብ ፍላጎት አሳይቷል።

ቶማስ ቶሬራ ወደ ቫሌንሽያ ለመዘዋወር ቢስማማም አርሰናል የኡራጓያዊውን የ26 ዓመት ተጫወች ዝውውር አዘግይቶታል።