ዩሮ በ20 ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ከዶላር በታች ወረደ

ዩሮና ዶላር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሩሲያ በዩክሬን ላይ በከፈተችው ጦርነት ምክንያት እያሽቆለቆለ የሄደው የአውሮፓ አገራት መገበያያ ገንዘብ ዩሮ ከ20 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከዶላር በታች ወረደ።

ሩሲያ የአውሮፓን የሃይል አቅርቦት ልትገድብ ትችላለች የሚለው ፍራቻ ዩሮን እንደ መገበያያ ገንዘብ በሚጠቀሙ አገራት (ዩሮ ዞን) እንዲወርድ እድሉን ጨምሯል።

የአውሮፓ ማዕከላዊ ባንክ ሌሎች ማዕከላዊ ባንኮች የመገበያያ ገንዘቡን የምንዛሬ ዋጋ ጭማሬ እንዲያዘገዩ ማድረጉን ተከትሎም ዩሮን የበለጠ አዳክሞታል ተብሏል።

ማዕከላዊ ባንክ የመገበያያ ገንዘቡን የምንዛሬ ተመን ምጣኔ ሲጨምር አለምአቀፍ ኢንቨስተሮች ዋጋ ያላቸውን ንብረቶች በዚያ ገንዘብ ለመያዝ ያላቸው ፍላጎት ስለሚጨምር ምንዛሬዎችም ይጨምራሉ ።

የአሜሪካ ዶላር በቅርብ ወራት ውስጥ ጠንካራ መሆኑ ታይቷል። ለዚህም እንደ ምክንያትነት የተጠቀሰው የአሜሪካዊ ማዕከላዊ ባንክ የምንዛሬ ወለድ ተመንን በማሳደጉ እና ዓለም አቀፉን የምጣኔ ኃብት ውዥንብር የፈሩ ባለሃብቶችም ዶላርን እንደ አማራጭ በመያዛቸው ነው።

ዩሮ ባለፈው ወር ከፓውንድም ጋር ሲነጻጸር መውረድ አሳይቷል።

የመገበያያ ገንዘቡን ማዳከም ዩሮን በመገበያያነት ለሚጠቀሙ ሃገራት ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በተለይም እንደ ድፍድፍ ዘይት ባሉ በዶላር የሚሸጡ ሸቀጦች የበለጠ ውድ ያደርግባቸዋል ተብሏል።

በነዚህ ሃገራት ውስጥ በባለፈው ወር 8.6 በመቶ የዋጋ ግሽበት ላስመዘገቡት የበለጠ እንዲያሻቅብ የበለጠ አስተዋጽኦ ሊያደርግ ይችላል።

የአውሮፓ ማዕከላዊ ባንክ ቃለ አቀባይ እንዳሉት “አንድ የተወሰነ የምንዛሬ ተመን ላይ አላነጣጠርንም። ነገር ግን የምንዛሬ ተመኑ በዋጋ ግሽበቱ ላይ የሚያሳድረውን ተፅእኖ ትኩረት እንሰጣለን። ቅድሚያ የምንሰጠው ስራ ዋጋ ማረጋጋት ነው” ብለዋል።

ባንኩ በሚቀጥለው ሳምንት የምንዛሬ ተመኑን ይጨምራል ተብሎ ይጠበቃል።

ከአውሮፓውያኑ አዲስ አመት ጀምሮ ዩሮ ከዶላር ጋር ሲነጻጸር በ12 በመቶ ወድቋል።

ዩሮ ለአመታት ከዶላር የበለጠ ዋጋ የነበረው ሲሆን ከዶላር በታች የወረደው በሁለት አጋጣሚዎች ነበር። በመጀመሪያ ለኤሌክትሮኒክ ክፍያነት አገልግሎት ላይ በዋለበት በአውሮፓውያኑ 1999 እንዲሁም የዩሮ ገንዘቦች እና ሳንቲሞች ለመጀመሪያ ጊዜ በገበያ ላይ በዋሉበት በአውሮፓውያኑ 2002 ነበር።