የመንግሥት የሰላም ተደራዳሪ ቡድን ሥራ መጀመሩን አስታወቀ

የፎቶው ባለመብት, Ambassador Redwan Hussein Twitter page
አስራ ዘጠኝ ወራት የዘለቀውን የእርስ በርስ ጦርነት በሰላም ለመቋጨት የተቋቋመው የመንግሥት ተደራዳሪ ኮሚቴ ሥራ መጀመሩን አስታወቀ።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት ጉዳዮች አማካሪና የኮሚቴው አባል የሆኑት አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ኮሚቴው የመጀመሪያ ስብሰባውን ትናንት ማክሰኞ ሐምሌ 05/2014 ዓ.ም. ማካሄዱን አስታውቀዋል።
አምባሳደሩ በትዊተር ገጻቸው ላይ እንዳሰፈሩት የሰላም አማራጭ አብይ ኮሚቴ ሲሉ የጠሩት ይህ ኮሚቴ፣ በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር ለሚካሄደው ውይይት የአሰራርና ሥነ ምግባር አካሄድ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ማስተላለፉም ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም ንዑሳን ኮሚቴዎች የተደራጁ ሲሆን በዚህም መዋቅር መሰረት ኃላፊነት ተከፋፍለው ሥራው መጀመሩን ከአምባሳደሩ ትዊተር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል።
ከትግራይ ክልል አመራሮች ጋር መቼ ውይይት እንደሚጀመርም ሆነ፣ የት ይሆናል የሚለው ላይ እስካሁን ከሁለቱም ተደራዳሪ ወገኖች በኩል የተገለጸ መረጃ የለም።
ጦርነቱን በሰላም ለመቋጨት ይቻል ዘንድ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ተደራዳሪ ቡድን መሰየሙ የተገለጸው ከሁለት ሳምንት በፊት ነበር።
ተደራዳሪው ኮሚቴ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሚመራ ሲሆን ሰባት አባላት እንዳሉትም ተገልጾ ነበር።
ከአቶ ደመቀ መኮንን እና ከአምባሳደር ሬድዋን በተጨማሪ የፍትህ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ፣ የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ የመከላከያ ሠራዊት የመረጃ ደኅንነት ኃላፊ ሌ/ጄ ብርሃኑ በቀለ፣ የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶ/ር ጌታቸው ጀምበር፣ የብልጽግና ፓርቲ የዴሞክራሲ ማዕከል ዘርፍ ከፍተኛ ኃላፊ አምባሳደር ሐሰን አብደልቃድር በአባልነት ተካትተዋል።
ከትግራይ ክልል በኩል እስካሁን ድረስ ተደራዳሪ ሊሆኑ የሚችሉ ግለሰቦችን በተመለከተ እስካሁን ድረስ የተገለጸ ጉዳይ የለም።
ድርድሩ በአፍሪካ ኅብረት የሚመራ እንደሆነ የኢትዮጵያ መንግሥት አቋሙን ያስታወቀ ሲሆን፣ ከዚህ በፊት በኅብረቱ ላይ ያላቸውን ቅሬታ በገለጹት የትግራይ አመራሮች በኩል የተቋሙን አደራዳሪነት ይቀበሉታል ወይ ስለሚለውም ጉዳይ የተሰጠ ምላሽ የለም።
ከዚህ ቀደም የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ባለፈው ወር ለአፍሪካ ኅብረት ሊቀ መንበርና ለሴኔጋሉ ፕሬዚዳንት ማኪ ሳል በላኩት ደብዳቤ ተቋሙ ላይ ያላቸውን ቅሬታ ገልጸዋል።
“የአፍሪካ ኅብረት በጦርነቱ እንዲሁም በጦር ኃይሎች የደረሰብንን ግፍ እንዳላየ ዝምታን መምረጡ የኅብረቱ መሠረታዊ መርሆች ክህደት ነው። የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር እንዲሁም ከፍተኛ ተወካያቸው በኅብረቱ አሰራር የሰላም እና የፀጥታ ምክር ቤትን የሚያቋቁም ፕሮቶኮል መሰረት አቋም አለመውሰዱን በመጥቀስ የተጣለበትን ኃላፊነት አልተወጡም ስንል በተደጋጋሚ አውግዘናል። በትግራይ ሕዝብ እና መንግሥት አቋም መሰረት የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን አመራር ከውድቀቶቹ ተምሮ አመኔታውን ለማግኘት ሥራ መስራት አለበት” ብሏል ደብዳቤው።
ሁለቱም ወገኖች ጦርነቱን ለማብቃት ድርድር የማካሄድ ፍላጎት እንዳላቸው የገለጹ ቢሆንም፣ አስካሁን በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ንግግር ስለመጀመሩ በይፋ የተባለ ነገር የለም።
ባለፈው ዓመት ጥቅምት መጨረሻ ላይ ትግራይ ውስጥ ተከስቶ ወደ አማራና አፋር ክልሎች የተዛመተው ደም አፋሳሽ ጦርነት ሺዎችን በመቅጠፍና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን በማፈናቀል መጠነ ሰፊ ሰብዓዊ ቀውስ አድርሷል።












