የሕንድ የዘር ግንድ ያላቸው ሪሺ ሱናክ ቀጣዩ የዩኬ ጠቅላይ ሚንስትር ለመሆን ፉክክሩን እየመሩ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ተሰናባቹን የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰንን ለመተካት እየተደረገ ያለውን ትንቅንቅ የሕንድ የዘር ግንድ ያላቸው ሪሺ ሱናክ እየመሩ ይገኛሉ።
ሱናክ የወግ አጥባቂ ፓርቲ መሪ ለመሆን እስካሁን የተካሄዱ ሁለት ተከታታይ ምርጫዎችን አሸንፈዋል።
ከሕንዳውያን ወላጆች የተወለዱት ሪሽ ሱናክ በመጀመሪያው ዙር ምርጫ 88 ድምጽ ያገኙ ሲሆን የንግድ ሚንስትሯ ፔኒ ሞርደንት 67 ድምጽ በማግኘት ሁለተኛ ሆነው ነበር። የውጭ ጉዳይ ሚንስትሯ ሊዝ ትረስ ደግሞ በ50 ድምጽ ሦስተኛ ደረጃን ይዘው ነበር በመጀመሪያው ዙር ምርጫ።
በሁለተኛው ምርጫ ሱናክ 101 ድምጽ ሲሰበስቡ ሞርደንት 83፤ ትረስ ደግሞ 64 ድምጽ አግኝንተዋል።
እስካሁን በተካሄደው ምርጫ ቻንስለር ናዲም ዛሃዊ እና የቀድሞው የጤና ሚንስትር ጀረሚ ሃንት ከውድድሩ ተሰናብተዋል።
አሁን ውድድሩ ላይ ያሉት ዕጩዎች ሌላ ፉክክር ይጠብቃቸዋል። በተጨማሪም ዛሬ አርብ ሐምሌ 15/2014 ዓ.ም. አምስት እጩዎች በቀጥታ የቴሌቪዥን መስኮት ክርክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ውድድሩ በዚህ መልኩ ከቀጠለ በኋላ በሚቀጥለው ሳምንት መጨረሻ ሁለት ተወዳዳሪዎች ብቻ እንዲቀሩ ይደረጋል።
ሁለቱን ተወዳዳሪዎች ደግሞ 160 ሺህ አካባቢ የቶሪ አባላት ድምጽ ሰጥተውባቸው አሸናፊው የፓርቲ መሪ እና ጠቅላይ ሚንስትር ይሆናል።
ውጤቱ በአውሮፓውያኑ መስከረም አምስት ይፋ ይደረጋል።
አሁን ውድድሩ ላይ የቀሩት ተፎካካሪዎች ቀጣዩን ዙር ለማሸነፍ ከሁለቱ ተሰናባች መራጮች [ጀረሚ ሃንት እና ዛሃዊ] ተጨማሪ ድምጽ ለመቀራመት ይፎካከራሉ። ተሰናባቹ ጀረሚ ሃነት ሱናክን እንደሚደግፉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ባለፈው ሳምንት የቦሪስ ጆንሰንን አመራር በመቃወም ከቻንስለርነታቸው የለቀቁት ሱናክ በውጤቱ ደስተኛ መሆናቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
የትረስ ቃል አቀባይ “አሁን ወዳጆች ተሰባስበው ታክስ የሚቀንስ፣ እውነተኛ የምጣኔ ሃብት ለውጥ የሚያመጣ እና ዩክሬን ውስጥ የፑቲንን ሽንፈት የሚያፋጥን መሪ ያስፈልገናል” ብለዋል።
“ሊዝ የብሬግዚትን ጉዳይ በማፋጠን እና የምጣኔ ሃብት እድገት በማምጣት ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል” ብለዋል።
ለረጅም ጊዜ የፓርላማ አባል የሆኑት ቱጌንዳት በትዊተር ገጻቸው “በጣም ደስ የሚል ውጤት ነው። አገራችንን ወደተሻለ ደረጃ ለመለወጥ በሚቀጥለው የምርጫ ሂደት ውስጥ ለመሳተፍ በእጅጉ ደስተኛ ነኝ። አገራችን ግልጽ የሆነ አጀማመር ሊኖራት ይገባል” ብለዋል።
በአውሮፓውያኑ 2019 በነበረው ውድድር ሁለተኛ ሆነው ያጠናቀቁት ጀረሚ ሃንት ወግ አጥባቂ ፓርቲ በቀጣይ “አስደናቂ ዘመን” ይኖረዋል ብለዋል።
ለተወዳዳሪዎቹም ምክር ለግሰዋል። “መሞካሸት እና መዘላለፍ ለአጭር ጊዜ እምርታ ሊያመጣ ይችላል፤ በረጅም ጊዜ ሂደት ግን አደጋ አለው” ብለዋል። ሌላኛው የውድድሩ ተሰናባች ዛሃዊ ደግሞ “አሁን ጣልቃ መግባት ባልፈልግም ለሁሉም ተወዳዳሪዎች መልካም ዕድል እመኛለሁ” ብለዋል።
ይህ ውድድር እየተካሄደ ያለው ባለፈው ሳምንት ቦሪስ ጀንሰን ስልጣናቸውን እንደሚለቁ ካሳወቁ በኋላ ነው። ቦሪስ ጆንሰን በኮሮናቫይረስ እገዳ ወቅት መመሪያ በመጣስ ጎዳና ዘግተው ድግስ አዘጋጅተዋል በሚል እና በሌሎች ክሶች ሲወቅሱ ሰነባብተዋል።












