የዘር ማጽዳት እንዳይፈጸምባቸው የፈሩ አርመናውያን የካራባክን ግዛት ለቀው እየሸሹ ነው

የፎቶው ባለመብት, AFP VIA Getty Images
አዘርባጃን አወዛጋቢዋን የናጎሮኖ ካራባክን ግዛት መቆጣጠሯን ተከትሎ በሥፍራው የሚኖሩ አርመናውያን የዘር ማጽዳት ይፈጸምብናል በሚል ስጋት እየሸሹ ነው።
ወደ 6 ሺህ 500 የሚጠጉ አርመናውያንም ድንበር በመሻገር ወደ አርሜንያ እየገቡ ይገኛሉ።
በሥፍራዋ ከ120 ሺህ የሚበልጡ አርመናውያን ይኖሩባታል።
የአርመን መንግሥት በግጭቱ ምክንያት ቤት አልባ የሆኑትን ለመውሰድ ማወጁን ተከትሎ ነው ነዋሪዎቹ እየሸሹ ያሉት።
የአርሜኒያ ድንበር መንገዶችም በከፍተኛ ሁኔታ በትራፊክ ተጨናንቀዋል።
የአርሜኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር በዚህች ግዛት የዘር ማጽዳት ተጀምሯል ሲሉም አስጠንቅቀዋል።
“ይህ እየሆነ ያለው በአሁኑ ወቅት ነው።በጣም አሳዛኝ እውነታ ነው። ምክንያቱም በዚህ ጉዳይ ላይ ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ለማሳሰብ እየሞከርን ነበር” ሲሉም የአርመን ጠቅላይ ሚኒስትር ኒኮል ፓሺንያን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
አዘርባጃን በበኩሏ በአሁኑ ወቅት ሙሉ በሙሉ በተቆጣጠረቻት ግዛት የሚኖሩ አርመናውያንን ከሌሎች ዜጎቿ ጋር በእኩልነት ማዋሃድ እንደምትፈልግ ተናግራለች።
የካራባክ ግዛት የኔ ናት በሚል የሚወዛገቡት የአርሜኒያ እና የአዘርባጃን ልዑካን በአውሮፓ ኅብረት በሚደገፈው ውይይት ማክሰኞ ብራስልስ ላይ ይቀመጣሉ።
አዘርባጃን የናጎርኖ ካራባክን ግዛት ተቆጣጥሬያለሁ ካለች በኋላም የሚደረግ የመጀመሪያ ንግግር ነው።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃለ አቀባይ ማቲው ሚለር ሁለቱ ወገኖች ዘላቂ የሰላም ስምምነት ላይ እንዲደርሱ አሳስበዋል።
አዘርባጃን በአወዛጋቢዋ ናጎሮኖ ካራባክ ግዛት በሚገኙ የአርመን ኃይሎች ላይ ለ24 ሰዓታት የፈጀ ወታደራዊ ጥቃት ማድረጓን ተከትሎ የአገሪቱ ሉዓላዊነት እንደተመለሰ ፕሬዚዳንቷ ከሰሞኑ አስታውቀዋል።
የራሳችንን ነጻ አገር መስርተናል ሲሉ የነበሩት የአርመን ኃይሎችም ትጥቅ ለመፍታት እና እጅ ለመስጠት ተስማምተዋል።
እስያንና አውሮፓን የምታገናኘው፣የሩሲያ ዛሮችን ጨምሮ፣ ሮማ፣ ቱርክ፣ የቀድሞዋ ፋርስ ሌሎች ሌሎች መሪዎችም የገዟት ናጎሮኖ ካራባክ 120 ሺህ የሚሆኑ አርመናውያን እንዲሁም የአዘሪ ነገድ አባላት ይኖሩባታል።
ተራራማዋ እና ባህር በር አልባዋ ግዛት ናጎሮኖ ካራባካህ ከአዘርባጃን በስተደቡብ ምዕራብ ትገኛለች።
ሁለቱ የቀድሞ የሶቪየት ኅብረት አባል አገራት አርሜኒያና አዘርባጃን ግዛቲቷ የኔ ነው በሚልም ጦርነት ተማዘውባታል።በርካቶች አልቀውባታል።
በአውሮፓውያኑ 2020 ለስድስት ሳምንታት የዘለቀው ጦርነት ለብዙ ሺህ ሰዎች ሞት ምክንያት ቢሆንም፤አዘርባጃን በቱርክ በመደገፍ ግዛቲቷን እንድትቆጣጠር አድርጓታል። ይህም ሁኔታ በሥፍራው የሚኖሩ አርመናውያን እንዲነጠሉ አድርጓቸዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ምዕራባውያኑ ናጎሮኖ ካራባክን በአዘርባጃን ግዛትነት ዕውቅና ሰጥተዋታል።
ነገር ግን በአርመን መንግሥት የሚደገፉት የካራባክ ኃይሎች ግዛቲቷን ከአዘርባጃን ገንጥለው ነጻ አገር መመስረታቸውን በተመለከተ ድጋፍም ሆነ ተቃውሞ አላሰሙም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በካራባክ መዲና ስቴፓናከርት በነዳጅ ማደያ ላይ በደረሰ ፍንዳታ ከ200 በላይ ሰዎች ክፉኛ እንደቆሰሉ የአካባቢው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ጋገም ስቴፓንያን በኤክስ ገጹ ላይ አስታውቋል።
ፍንዳታው በምን ምክንያት እንደተፈጸመ እስካሁን አልታወቀም።












