የግብጽን መንግሥት ለመደገፍ ጉቦ በመቀበል የተከሰሱት አሜሪካዊ የምክር ቤት አባል ነጻ ነኝ አሉ

 የአሜሪካ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ ሊቀመንበር ቦብ ሜንዴዝ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የግብጽ መንግሥትን ለመደገፍ ጉቦ ተቀብለዋል ተብለው የተከሰሱት የአሜሪካ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ ሊቀመንበር ቦብ ሜንዴዝ ከወንጀሉ ነጻ ነኝ ሲሉ ተናገሩ።

በቤታቸው በፍተሻ የተገኘው ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጋ ዶላር ለአስርት ዓመታት የለፉበት ገንዘብ እንደሆነም ገልጸዋል።

ቤታቸው ውስጥ ይህን ያህል ገንዘብ ያስቀመጡትም በባለስልጣናት ሊወሰድ ይችላል በሚል ከኩባ ወላጆቻቸው በተላለፈባቸው ስጋት መሆኑንም አስረድተዋል።

የኒውጀርሲው ተወካይ ሮበርት ሜንዴዝ ከሙስና ክስ ነጻ መውጣት ብቻ ሳይሆን በሚቀጥለው ዓመት በምርጫ እንደሚወዳደሩም ተናግረዋል።

የአሜሪካ የፍትህ ሚኒስቴር ፖለቲከኛው እና ባለቤታቸው የግብጽ መንግሥትን ለመደገፍ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ዶላር ጉቦ ተቀብለዋል ሲል ከሷል።

ባለፈው ሳምንት ዐርብ ዕለት ይፋ በሆነው ባለ 39 ገጾች ክስ መሰረት ሜንዴዝ ሥልጣናቸውን ተጠቅመው በአገራቸው እና በውጭ አገራት ባሉ የሙስና እቅዶች ላይ ተጽእኖ በማሳደር ክስ ቀርቦባቸዋል።

የቋሚ ኮሚቴው ሊቀ መንበር በአሜሪካ በሚገኘው የግብጽ ኤምባሲ ውስጥ የሚሰሩ ዲፕሎማቶችን በተመለከተ ከፍተኛ ምስጢራዊ መረጃዎችን በማጋራት እንዲሁም የግብጽን መንግሥት ምስጢራዊ በሆነ ሁኔታ የሚደግፉ እርምጃዎችን ወስደዋል ተብለዋል።

ለዚህም ሜንዴዝ እና ባለቤታቸው ናዲን አርስላኒያን ከሦስት የኒውጀርሲ ነጋዴዎች ገንዘብ፣ ወርቅ፣ ለቤት ብድር የተፈጸመ ክፍያ እና የቅንጦት ተሽከርካሪ ጉቦ እንደተቀበሉም ክሱ ያስረዳል።

ውዝግብ ውስጥ የገቡት የቋሚ ኮሚቴው ሊቀመንበር በትውልድ አገራቸው ኒውጀርሲ ከሚገኙ ዲሞክራቶች ከአባልነታቸው እንዲለቁ የቀረበላቸውን ጥያቄም ውድቅ አድርገዋል።

“ሁሉም እውነታዎች ግልጽ ሲሆኑ ከወንጀሉ ነጻ መሆን ብቻ ሳይሆን አሁንም በኒውጀርሲ ከፍተኛ የምክር ቤት አባልነቴ እቀጥላለሁ።” ሲሉም ሜንዴዝ ሰኞ እለት በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል።

ፖለቲከኛው ባለፈው ሳምንት ዐርብ ከተከሰሱ ጀምሮ በአደባባይ ላይ ሲታዩ ይህ የመጀመሪያቸው ነው።

“በኔ ላይ ለመፍረድ የተጣደፋችሁ አቃቤ ሕግ በሰጣችሁ እና ሆን ተብለው በተወሰኑ መረጃዎች ላይ ተመስርታችሁ ነው።” ብለዋል።

ባለፈው ዓመት የፌደራል የደኅንነት ሰራተኞች የፖለቲከኛውን ቤት በፈተሹበት ወቅት ከ480 ሺህ ዶላር በላይ “በጥሬ ገንዘብ በአብዛኛው በፓስታ ውስጥ እንዲሁም በልብስ ውስጥ ኪሶች፣ በቁም ሳጥኖች እና ካዝናዎች ውስጥ ተደብቀው” መገኘታቸውም ተገልጿል።

ሰኞ ዕለት በነበራቸው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ “ከግል ቁጠባ አካውንቴ በሺዎች የሚቆጠር ዶላር በጥሬ ገንዘብ አውጥቻለሁ።ይህንን ገንዘብ ቤት ያስቀመጥኩት ለድንገተኛ አደጋ እና ወላጆቼ ኩባ በነበሩበት ወቅት በባለስልጣናት ገንዘባቸው ከመወረሱ ጋር ተያይዞ ያደረብኝ ስጋት ነው።” ሲሉም ነው የተናገሩት።

“ገንዘቡ ለሠላሳ ዓመታት በሕጋዊ መንገድ የለፋሁበት እና የቆጠብኩት ነው።” ብለዋል።