በአዲስ አበባ ሲደረግ የነበረው የህዳሴ ግድብ የሦስትዮሽ ድርድር ያለምንም ውጤት መጠናቀቁ ተነገረ

በኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን መካከል በአዲስ አበባ ለሁለት ቀናት የተደረገው የታላቁ ህዳሴ ግድብ የሦስትዮሽ ድርድር ያለምንም ውጤት መጠናቀቁን ግብጽ አስታውቃለች።
በግድቡ የውሃ ሙሌት እና አለቃቀቅ ደንቦች እና መመሪያዎች ላይ አተኩሮ መስከረም 12 እና 1 የተደረገው ድርድር ውጤታማም እንዳልነበር ነው የግብጽ የውሃ እና መስኖ ሚኒስቴር ያስታወቀው።
ለዚህም ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በነበረው ድርድር በሦስቱ አገራት መግባባት ላይ የተደረሰባቸውን ጉዳዮችን ባለመቀበሏ እንደሆነ ነው የግብጽ ሚዲያዎች ሚኒስቴሩን ዋቢ አድርገው የዘገቡት ።
የሦስትዮሽ ድርድሩ መጠናቀቀቁን ያስታወቀችው ኢትዮጵያ በበኩሏ በአገራቱ መካከል ያሉትን ልዩነቶች ለማጥበብ የድርድርና የሃሳብ ልውውጥ ተካሂዷል ብላለች።
የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች እና የሕዳሴ ግድብ ዋና ተደራዳሪ እና አማካሪ አምባሳደር ስለሺ በቀለ “ኢትዮጵያ የጋራ መፍትሄ ላይ ለመድረስ በቀና መንፈስ አበክራ ትሰራለች” ሲሉም በኤክስ ገጻቸው አስፍረዋል።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት በግብጽ ከተደረገው በቀጠለው በዚህ ድርድር ላይ ሦስቱ አገራት በረቂቅ ደንቦችና መመሪያዎች ላይ ውይይት ተካሂዷል።
በዚህ የሦስትዮሽ ድርድር እልባት ባላገኙ ጉዳዮች ላይ መግባባት ላይ እንደሚደርሱም እምነት እንደነበራቸው ዋና ተደራዳሪው በመክፈቻ ንግግራቸው ወቅት ተናግረው ነበር።
“ኢትዮጵያ ቀደም ሲል በሦስቱ አገራት ማዕከል በድርድር ማዕቀፍ ውስጥ የተደረሱ በርካታ ስምምነቶችን ያለመቀበል አዝማሚያ አሳይታለች” ሲሉም የግብጽ ውሃ እና መስኖ ሚኒስቴር ቃለ አቀባይ መሃመድ ግሃኒም በመግለጫቸው መናገራቸውን አል አህራም ጋዜጣ አስነብቧል።
አል አህራም ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በሦስቱ አገራት መግባባት ላይ ተደርሶባቸው በአሁኑ ድርድር ያለመቀበል አዝማሚያ አሳይታባቸዋለች ያላቸውን ጉዳዮች በዝርዝር አላስቀመጠም።
ስምምነቶች ላይ ለመድረስ እንዲያስችል ከኢትዮጵያ ጥቅም በተጣጣመ መልኩ እና የታችኛው ተፋሰስ አገራትንም አደጋ ባልጣለ ሁኔታ በአለም አቀፍ ደረጃ የቀረቡ ሃሳቦችን እና የቴክኒካል ዝግጅቶችንም ኢትዮጵያ ውድቅ አድርጋለች ሲል አል አህራም ቃለ አቀባዩን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።
ኢትዮጵያ በሦስቱ አገራት መካከል በአውሮፓውያኑ 2015 በተደረሰው በመርሆች መግለጫ ስምምነት መሰረት የናይል ወንዝን ፍትሃዊ እና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ መጠቀም ብቸኛው አዋጭ መንገድ ነው ብላ እንደምታምን ነው አምባሳደር ስለሺ በድርድሩ የመክፈቻ ንግግር ወቅት ያሳወቁት።
ኢትዮጵያ ‘የመጨረሻ’ ያለችውን አራተኛ ዙር የህዳሴ ግድብ ሙሌት ከማከናወኗ በፊት ሦስቱ አገራት በግብጽ ነሐሴ 21 ተጀምሮ በማግስቱ ነሐሴ 22 የተጠናቀቀ ምክክር አድርገው ነበር።
ለሁለት ዓመት ያህል ተቋርጦ የቆየው የሦስትዮሹ የመጀመሪያው ዙር ድርድር የግድቡ የመጀመሪያ ዙር ሙሌት እና ዓመታዊ አሰራር ላይ ያተኮረ እንደነበር የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቆ ነበር።
ጳጉሜ መጨረሻ ላይ ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ አራተኛ ዙር ሙሌት ማካሄዷንም ተከትሎ ግብጽን አስቆጥቷል።
ግብጽ ከናይል ወንዝ የማገኘው የውሃ መጠን አቅርቦት ላይ አደጋ የጋረጠ እንዲሁም የታችኛውን ተፋሰስ አገራት ችላ ያለ ነው ስትልም ቅሬታዋን አቅርባለች።
በግድቡ የውሃ ሙሌት እና ከግድቡ በሚለቀቀው የውሃ መጠን ላይ ህጋዊ እና አስገዳጅ ሦስትዮሽ ስምምነት ካልተፈረመ ኢትዮጵያ የውሃ ሙሌቱን ማከናወን እንደሌለባትም ግብጽ ስትወተውት መቆየቷ ይታወሳል።
ኢትዮጵያ በበኩሏ ሦስቱ አገራት በናይል ወንዝ ላይ ባላቸው የውሃ ድርሻ ላይ መስማማት ከቻሉ ከህዳሴ ግድብ የሚለቀቀውን የውሃ መጠን በተመለከተ አሳሪ ስምምነት ላይ መድረስ እንደሚቻልም አቋሟን አሳውቃለች።
ግድቡን በሚመለከት በአፍሪካ ኅብረት አሸማጋይነት በተከታታይ ሲካሄድ የነበረው የሦስትዮሽ ድርድር በመጨረሻ ከሁለት ዓመታት በፊት ኮንጎ ኪንሻሳ ውስጥ ተደርጎ የነበረ ቢሆንም፣ አንዱ ወገን ሌላኛውን ለድርድሩ አለመሳካት ተጠያቂ በማድረግ ያለውጤት መበተኑ ይታወሳል።












