የህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር በአዲስ አበባ ተጀመረ

የፎቶው ባለመብት, @mfaethiopia
በኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን መካከል የሚደረገው የታላቁ ህዳሴ ግድብ የሶትዮሽ ድርድር በአዲስ አበባ ዛሬ መስከረም 12/ 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ተጀመረ።
ሁለተኛው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት እና አለቃቅ ደንቦችና መመሪያዎች የሶስትዮሽ ድርድር መጀመሩንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት በግብጽ ከተደረገው በቀጠለው በዚህ ድርድርም ላይ ሶስቱ አገራት በረቂቅ ደንቦችና መመመሪያዎች ላይ ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ኢትዮጵያ በመርሆች መግለጫ ስምምነቱ መሰረት አራተኛውን ዙር የህዳሴ ግድብ በስኬት ካጠናቀቀች በኋላ የሚደረግ ድርድር መሆኑንም የድንበር ተሻጋሪ ወንዞችና የሕዳሴ ግድብ ዋና ተደራዳሪ እና አማካሪ አምባሳደር በመክፈቻ ንግግራቸው ገልጸዋል።
በአሁኑ የሶስትዮሽ ድርድር አገራቱ እልባት ባላገኙ ጉዳዮች ላይ መግባባት ላይ እንደሚደርሱ ያላቸውን እምነት ዋና ተደራዳሪው አንጸባርቀዋል።
ኢትዮጵያ በሶስቱ አገራት መካከል በአውሮፓውያኑ 2015 በተደረሰው በመርሆች መግለጫ ስምምነት መሰረት የናይል ወንዝን ፍትሃዊ እና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ መጠቀም ብቸኛው አዋጭ መንገድ ነው ብላ እንደምታምን የአገራቸውን አቋም አሳውቀዋል።
ኢትዮጵያ በዚህ የሶስትዮሽ ሂደት በድርድር እና ሰላማዊ መፍትሄ ላይ ለመድረስ ቁርጠኛ ናት ብለዋል አምባሳደሩ።
የግብፅ የውሃና መስኖ ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሃኒ ሰዊላም እና የሱዳኑ የውሃ ተጠባባቂ ሚኒስትር ዳወልቤት አብደልራህማን ማንሱር ባሸር በመክፈቻ ንግግሮቻቸው ላይ ስምምነት ላይ ለመድረስ ያላቸውን ተስፋ ማንጸባረቃቸውም ተገልጿል።
ኢትዮጵያ ‘የመጨረሻ’ ያለችውን አራተኛ ዙር የህዳሴ ግድብ ሙሌት ከማከናወኗ በፊት ሶስቱ አገራት በግብጽ ነሐሴ 21 ተጀምሮ በማግስቱ ነሐሴ 22 የተጠናቀቀ ምክክር አድርገው ነበር።
ለሁለት ዓመት ያህል ተቋርጦ የቆየው የሶስትዮሹ የመጀመሪያው ዙር ድርድር የግድቡ የመጀመሪያ ዙር ሙሌት እና ዓመታዊ አሰራር ላይ ያተኮረ እንደነበር የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቆ ነበር።
የአገራቱ ተወካዮች ሁሉም አሸናፊ የሚሆኑበት ስምምነት ላይ ለመድረስም ሃሳብ መለዋወጣቸውን ያስታወቀው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቀጣዩም ዙር መስከረም 2016 በአዲስ አበባ እንዲካሄድ መግባባት ላይ ተደርሷልም ብሎ ነበር።
ኢትዮጵያ የናይል ወንዝ ላይ ያላትን ድርሻዋን ባረጋገጠ መልኩ ፍትሃዊ እና ምክንያታዊ አጠቃቀም ላይ በተመሠረተም የሦስትዮሽ ድርድር ስምምነትም ላይ እንዲደረስ እንደምትጥርም ገልጻለች።
ጳጉሜ መጨረሻ ላይ ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ አራተኛ ዙር ሙሌት ማካሄዷንም ተከትሎ ግብጽን አስቆጥቷል።
ግብጽ ከናይል ወንዝ የማገኘው የውሃ መጠን አቅርቦት ላይ አደጋ የጋረጠ እንዲሁም የታችኛውን ተፋሰስ አገራት ችላ ያለ ነው ስትልም ክሴታዋን አቅርባለች።
በግድቡ የውሃ ሙሌት እና ከግድቡ በሚለቀቀው የውሃ መጠን ላይ ህጋዊ እና አስገዳጅ ሶስትዮሽ ስምምነት ካልተፈረመ ኢትዮጵያ የውሃ ሙሌቱን ማከናወን እንደሌለባትም ግብጽ ስትወተውት መቆየቷ ይታወሳል።
ኢትዮጵያ በበኩሏ ሶስቱ አገራት በናይል ወንዝ ላይ ባላቸው የውሃ ድርሻ ላይ መስማማት ከቻሉ ከህዳሴ ግድብ የሚለቀቀውን የውሃ መጠን በተመለከተ አሳሪ ስምምነት ላይ መድረስ እንደሚቻልም አቋሟን አሳውቃለች።
ግድቡን በሚመለከት በአፍሪካ ኅብረት አሸማጋይነት በተከታታይ ሲካሄድ የነበረው የሦስትዮሽ ድርድር በመጨረሻ ከሁለት ዓመታት በፊት ኮንጎ ኪንሻሳ ውስጥ ተደርጎ የነበረ ቢሆንም፣ አንዱ ወገን ሌላኛውን ለድርድሩ አለመሳካት ተጠያቂ በማድረግ ያለውጤት መበተኑ ይታወሳል።












