የሊቢያዋ ዴርና ከተማ ከንቲባ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከሞቱበት የጎርፋ አደጋ ጋር በተያያዘ ታሰሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በከፍተኛ ጎርፍ ተጥለቅልቃ አሰቃቂ አደጋ ያስተናገደችው የሊቢያዋ ከተማ ዴርና ከንቲባ ከክስተቱ ጋር በተገናኘ መታሰራቸውን ባለስልጣናት አስታውቀዋል።
አብዱልመናን አል ጋሃኣቲ የተባሉት ከንቲባ ከሳምንታት በበፊት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በተቀጠፉበት የጎርፍ አደጋ ምክንያት ክስ ከተመስረተባቸው በርካታ የመንግሰት ባለስልጣናት አንዱ ናቸው።
ባለፈው ሳምንት በክስተቱ የተቆጡ የዴርና ከተማ ነዋሪዎች ባደረጉት ተቃውሞ የከንቲባውን ቤት እሳት ለቀውበታል።
በትሪፖሊ የሚገኘው የሀገሪቱ ጠቅላይ አቃቤ ህግ መስሪያ ቤት ትላንት ባወጣው መግለጫ ባለስልጣናቱ በጎርፍ የፈረሰውን “የአካባቢውን ግድብ መሰረተ ልማት የማስተዳደር ኃላፊነት ነበረባቸው” ብሏል።
በዚህም ሳቢያ የወንጀል ክስ እንደከፈተባቸው ጠቅሷል።
ከንቲባ አል አል ጋሃኣቲን ጨምሮ የተወሰኑ ባለስልጣናት ከፍርድ ሂደቱ ቀደም ብሎ ታስረዋል።
የጠቅላይ አቃቤ ህግ መስሪያ ቤቱ በመግለጫው በዴርና ከተማ ከፍተኛ ጎርፍ እንዲከሰት ምክንያት ለሆነው የግድቡ መፍረስ ተጠያቂ ያደረገ ሲሆን ግድቡን ለመጠገን የቀረበውን ገንዘብ ተገቢ ባልሆነ መንገድ አስተዳድረዋል ብሏል።
የከንቲባው ጸህፍት ቤትም ከጎርፍ ጋር በተያያዘ በርካቶች እንዲሞቱና ሊቢያም የኢኮኖሚ ኪሳራ እንዲገጥማት ባደረገው አደጋ ባለስልጣናት ቀድመው እርምጃ ለመውስድ ቸልተኛ ሆነዋል ብሏል።
ከንቲባ አብዱልመናን አል ጋሃኣቲ ሰልጣንንን ያለአግባብ በመጠቀም ሌላ ክስ እንደሚጠብቃቸውም ተነግሯል።
ሊቢያ በምራቅና ምዕራብ የሀገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ ተቀናቃኝ ሃይሎች አስተዳደር ስር የምትገኝ ሀገር ናት።
በትሪፖሊ የሚገኘው ጠቅላይ አቃቤ ህግ የምዕራብ የሀገሪቱን ክፍል እንደመያዙ በምስራቁ ያሉ ተጠርጣሪዎች ለመያዝ ትዕዛዝ ምን ያህል ርቅት እንደሚጓዝ ግልጽ አይደለም።
ባለፈው ዕሁድ የምስራቁ የሀገሪቱ መንግሰት በጎርፍ አደጋው እንደሞቱ የተረጋገጡ ሰዎች ቁጥር 3 ሺህ 868 መደረሱን ገልጿል።
የጠቅላይ አቃቤ ህግ መስሪያ ቤት ከአደጋው ጋር በተያያዘ እየተደረገ ያለው ምርምራ እንደቀጠለ ገልጾ ሌሎች ተጨማሪ የሚታሰሩ ሰዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ አመላክቷል።












