የዛምቢያ የቀድሞ ፕሬዚደንት ‘ፖለቲካዊ’ ከተባለ አካላዊ እንቅስቃሴ ታገዱ

የፎቶው ባለመብት, ANDY LUKI JR
የዛምቢያ የቀድሞ ፕሬዚደንት ኢድጋር ሉንጉ በአደባባይ አካላዊ እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ ታገዱ።
ፖሊስ የቀድሞው ፕሬዚደንቱ በየሳምንቱ በአደባባይ የሚያደርጉትን ስፖርታዊ እንቅስቃሴ “ፖለቲካዊ” ሲል ገልጾታል።
የቀድሞው ፕሬዚደንቱ ከሌሎች ተራ የማኅበረሰቡ አባላት እና የፓርቲያቸው ፓትሪዎቲክ ፍሮንት (ፒኤፍ) አባላት ጋር በየሳምንቱ ቅዳሜ የሚያደርጉት ሩጫ የበርካቶችን ትኩረት ስቧል።
በመሆኑም ሉንጉ በቀጣይ ለሚያደርጓቸው ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች የፖሊስ ፈቃድ እንዲጠይቁ ተነግሯቸዋል።
ይህ የፖሊስ ትዕዛዝ የተሰማው ሉንጉ በአውሮፓውያኑ 2026 በሚካሄደው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ላይ እንደሚወዳደሩ ከተወራ በኋላ ነው።
ፖሊስ በሰጠው መግለጫ ያለ ፖሊስ ፈቃድ በአደባባይ መሰብሰብ እና ሰላማዊ ሰልፎችን ማካሄድ የሕግ ጥሰት እንደሚሆን ሕዝቡን አለማሳወቅ የፓርቲው ድክመት ነው ብሏል። ይህም ለሕዝብ ደህንነት ሲባል እንደሆነ ገልጿል።
መግለጫው ጨምሮም “የቀድሞው ፕሬዚደንት እንቅስቃሴ ማድረግ ያለባቸውም ደኅንነቱ በተጠበቀ እና ከፖለቲካ እንቅስቃሴ በጸዳ መልኩ ነው" ብሏል።
ይሁን እንጂ የቀድሞው ፕሬዚደንት ጠበቃ ማኬቡ ዙሉ፣ የቀድሞው ፕሬዚደንት ለፖሊስ ሳያሳውቁ አካላዊ እንቅስቃሴያቸውን (ሩጫቸውን) እንደሚቀጥሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የ66 ዓመቱ የቀድሞ ፕሬዚደንት በየሳምንቱ ቅዳሜ ከሚያደርጉት አካላዊ እንቅስቃሴ የሚከለከሉ ከሆነም በመንግሥት ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስዱም ጠበቃው ዝተዋል።
“ሉንጉ ለረጅም ጊዜ አካላዊ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ቆይተዋል። አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረጋቸውም ሕጉን ተጻሮ አያውቅም” ብለዋል ጠበቃው።
አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች አገሪቷን እያስተዳደሩ ያሉት ፕሬዚደንት ሃኪያንዴ ሒቺሌማ ተቃዋሚ በነበሩበት ወቅት ለበርካታ ዓመታት ሲተቹት የነበረውን ስልት እየተጠቀሙ ነው ይላሉ።
ከአውሮፓውያኑ 2015 እስከ 2021 አገሪቷን በመሩት በቀድሞ ፕሬዚደንቱ ላይ ክልከላ ሲጣልም ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም።
ሉንጉ በቅርቡ ለስብሰባ ወደ ደቡብ ኮሪያ እንዳይሄዱ ከተከለከሉ በኋላ መንግሥትን ፍርድ ቤት ከሰው ነበር ። ከዚያ በኋላ ግን ክሱን አንስተዋል።
ፓርቲያቸው ፒኤፍ የቀድሞ ፕሬዚደንቱ ከካቢኔ ቢሮ ፈቃድ ቢያገኙም ለሕክምና እንዳይጓዙ ተከልክለውም ነበር ብሏል።
ቢቢሲ በጉዳዩ ላይ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ጃኮብ ምዊምቡ አስተያየት እንዲሰጡ የጠየቀ ቢሆንም እስካሁን ምላሽ አላገኘም።
የቀድሞው ፕሬዚደንቱ በ2021ዱ ምርጫ ከተሸነፉ በኋላ ፖለቲካ ሊያቆሙ እንደሚችሉ የተናገሩ ቢሆንም ከቅርብ ወራት ወዲህ በሕዝብ ዘንድ ያላቸውን ገጽታ እያነቃቁ ነው።
ከሦስት ዓመት በኋላ በሚካሄደው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ላይ ለመሳተፍ እቅድ እንደያዙም በስፋት ይታመናል።
ሉንጉ በምርጫው ለመወዳደር እቅድ የያዙት በነዳጅ እና በምግብ ዋጋ ንረት ሳቢያ እየጨመረ የመጣውን ቁጣ ለማስወገድ እንደሆነ ይነገራል።
አሁን አገሪቷን እየመሩ ያሉት ፕሬዚደንት ሒቺሌማ የአገሪቷን ምጣኔ ሃብታዊ ቀውስ ያስወግዳሉ በሚል ተስፋ ነበር በ2021 የተካሄደውን ምርጫ በአብላጫ ድምጽ ማሸነፍ የቻሉት።
ፕሬዚደንቱ ከዚህ በፊት በተካሄዱት ምርጫዎች አምስት ጊዜ ተወዳድረው አልተሳካላቸውም ነበር።












