በዛምቢያ ምርጫ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪው አሸነፉ

የፎቶው ባለመብት, AFP
በአምስት ምርጫዎችን የተሸነፉት የዛምቢያ የተቃዋሚ መሪ ሃካንይን ሂቺሌማ ባለፈው ሳምንት የተካሄደውን ምርጫ አሸነፉ።
ሂቺሌማ ተሰናባቹ ፕሬዝደንት ኤድጋር ሉንጉን ከአንድ ሚሊዮን በላይ በሆነ ድምፅ ነው ማሸነፍ የቻሉት።
የረጅም ግዜ ተቀናቃኛቸው ፕሬዝደንት ኤድጋር ሉንጉ ከዚህ ቀደም ከፍተኛ ድጋፍ በነበሯቸው አካባቢዎች ጭምር መሸነፋቸውን ተከትሎ ምርጫው ነጻ እና ገለልተኛ አይደለም ሲሉ ወንጅለዋል።
ለ 21 ዓመታት በተቃውሞ ፖለቲካ ውስጥ የቆየው የዛምቢያ አንድነት ፓርቲ ለብሔራዊ ልማት ፓርቲ በመጨረሻም እድል ቀንቶታል።
ተቀናቃኙ ሂቺሌማ ከ2.8 ሚሊዮን በላይ ድምፅ ሲያመጡ ተሰናባቹ ፕሬዝደንት ደግሞ ከ1.8 ሚሊዮን በላይ ድምፅ አግኝተዋል።
የዛምቢያ የምርጫ ኮሚሽንም ለሶስት ቀናት ከቆየ የድምጽ ቆጠራ በኋላ ነጋዴው ሃካንይን ሄቺሌማ ፕሬዝዳንት ሆኖ መመረጡን ይፋ አድርጓል።
ውጤቱ መታወቁን ተከትሎም ከምርጫ ጣቢያዎች የጀመረው የደስታ የደስታ መግለጫ በዋና ከተማዋ ሉሳካ ጎዳናዎች ላይም ታይተዋል። ሂቺሊማ ምርጫውን ያሸነፉት ከአንድ ሚሊዮን ድምጽ በላይ በሆነ ልዩነት ነው።
የተሰናባቹ ፕሬዘዳነት የ ስድስት አመታት አገዛዝ በተለይም በሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ፣ በሙስና ፣ በኢኮኖሚ ውድቀት እንዲሁም በከፍተኛ የሥራ አጥነት ቁጥር ስሙ ይነሳል።
ምርጫው ነፃ እና ፍትሃዊ አልነበረም ብለው የተናገሩት እኚሁ ተሰናባች ፕሬዘዳንት ሉንጉ ምን ዓይነት እርምጃ እንደሚወስዱ እስካሁን ድረስ ግልፅ አይደለም። አዲስ የተመረጡት ፕሬዝዳንት በሚቀጥሉት 7 ቀናት ውስጥ ቃለ መሃላ ይፈፀማሉ ተብሎ ይጠበቃል።












