በሱዳን ግድብ ተደርምሶ 60 ሰዎች ሞቱ

የፎቶው ባለመብት, AFP
በጦርነት በምትታመሰው ሱዳን የጣለ ከባድ ዝናብን ተከትሎ ግድብ በመደርመሱ ቢያንስ ስልሳ ሰዎች ሞቱ።
የሟቾችን አስከሬን ፍለጋ አሁንም መቀጠሉ የተገለጸ ሲሆን ቁጥሩ ከዚህም ከፍ ሊል ይችላል ተብሎ ተሰግቷል።
አረባት የተሰኘው ግድብ 25 ሚሊዮን ኪውቢክ ሜትር ውሃ የመያዝ አቅም ያለው ሲሆን የጦር ኃይሉ መቀመጫ ለሆነችው ለባህር ዳርቻዋ ፖርት ሱዳን የመጠጥ ውሃ የሚቀርብበት ነበር።
ለ16 ወራት ያህል በጦርነት እየታመሰች የምትገኘው ሱዳን በአሁን ሰዓት ጎርፍ የቀላቀለ ከባድ ዝናብ እያስተናገደች ትገኛለች።
ይህ ከባድ ዝናብ በርካቶች ቀያቸውን ጥለው እንዲሰደዱ እንዲሁም እንደሚቱ ምክንያት ሆኗል።
የግድቡ መደርመስ በአካባቢው የሚገኙ ሰፋፊ ማሳዎችን እንዲሁም መኖርያ ቤቶችን ሙሉ በሙሉ አውድሟል።
አሊ ኢሳ የተባለ የአካባቢው ነዋሪ፤ “በሰባት መኪናዎች ተጭነው ከአካባቢው ለመውጣት የሚጠብቁ ነዋሪዎች ቢኖርም ልናጓጉዛቸው አልቻልንም” ሲል ለፈረንሳዩ የዜና ወኪል ተናግሯል።
ሙሳ መሐመድ ሙሳ የተባለ ሌላ ግለሰብ በበኩሉ በአንድ አካባቢ “ቤቶች እና ሌሎች ነገሮችን ጨምሮ ሙሉ በሙሉ በጎርፉ ተወስደዋል” መባሉን ገልጿል።
በሱዳን እየጣለ ያለው ከባድ ዝናብ ዋና የፋየር ኦፕቲክ መስመርን ሙሉ በሙሉ በማውደሙ የተነሳ በበርካታ የሱዳን ከተሞች ለሁለተኛ ቀን የኮሚዩኒኬሽን መቋረጥ አጋጥሟቸዋል።
የአገሪቱ አየር ኃይል ከጎርፉ ሸሽተው በከፍታ ቦታዎች ላይ የተጠለሉ ዜጎችን ለመታደግ እየሰራ መሆኑን የአገሪቱ ጋዜጣ ባለስልጣናትን ጠቅሶ ዘግቧል።
የጦር አዛዡ አብዱል ፈታህ አልቡርሃን በጎርፍ የተጎዱ አካባቢዎችን ጎብኝተዋል።
የጦር ኃይሉ በፌስቡክ ገጹ ባስለተላለፈው መልዕክት “የፌደራል እና የክልል አካላት በጎርፍ የተጎዱ ማህበረሰቦችን ለመደገፍ እና እርዳታ ለማቅረብ የተቻላቸውን እንዲያደርጉ” ጥሪ አቅርቧል።
ሱዳን በአገሪቱ ጦር ኃይል እና ፈጥኖ ደራሽ ኃይል መካከል ግጭት ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ በጦርነት እየታመሰች ነው።
በዚህም የተነሳ ሚሊዮኖች የሚኖሩበትን አካባቢ ለቅቀው የተሰደዱ ሲሆን በርካታ ክልሎችም ድርቅ መከሰቱን አውጀዋል።
አሁን እየጣለ ያለው ከባድ ዝናብም ያለውን የምግብ እጥረት ያባብሰዋል ተብሎ ተሰግቷል።












