ባለፉት ዓመታት በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን 229 ትምህርት ቤቶች መቃጠላቸው ተገለጸ

ባለፉት ዓመታት ሰላም ርቆት በቆየው ኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን 229 ትምህርት ቤቶች መቃጠላቸው ተገለጸ።
ከተቃጠሉት ትምህርት ቤቶች በተጨማሪ 217 ትምህርት ቤቶች በሰላም እጦት ምክንያት ማስተማር በማቆማቸው በጠቅላላው በዞኑ ከ67 ሺህ በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው መፈናቃላቸውን የዞኑ የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጋሻው አክሊሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“በዞናችን 229 ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ ተቃጥለዋል። 227 ትምህርት ቤቶች ደግሞ ምንም ባይሆኑም በሰላም እጦት የመማር ማስተማር ስራቸውን አቋርጠዋል” ብለዋል።
እንደ አቶ ጋሻው ገለጻ ትምህርት ቤቶች በመቃጠላቸው እና በሰላም እጦት ስራ በማቆማቸው ከ67ሺህ በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ውጪ ሲሆኑ፤ ሁለት ሺህ መምህራን ደግሞ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ተዘዋውረዋል።
በታጣቂዎች እንቅስቃሴ እና መንግሥት በሚወስዳቸው እርምጃዎች ምክንያት የሰሜን ሸዋ ዞን አካባቢዎች ሰላም ከራቃቸው ዓመታት አልፈዋል።
በቅርቡም የአካባቢው ሕዝብ፣ ልጆቹን ቀንበር አሸክሞ እና በማኅብረሰቡ ውስጥ ክብር ያላቸውን ዕቃዎች ይዞ አደባባይ በመውጣት ከአቅም በላይ ለሆኑ ችግሮች ፈጣሪ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ተማጽነዋል።
ነዋሪዎች በግብርና እና በወተት ምርቱ ይታወቅ የነበረው አካባቢያቸው ሰላም ርቆት በሰላም ወጥቶ መግባት፣ አርሶ መሰብሰብ፣ መገበያየት እና ልጆችን ትምህርት ቤት መላክ ካቃታቸው ዓመታት ማለፋቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የሰላማዊ ሰዎች ግድያ፣ ዘረፋ፣ መፈናቀል እና እገታ የዞኑን ነዋሪዎች ዕለት ከዕለት የሚረብሽ ጉዳይ ሆኗል።
ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸውን እንዳይጠቀስ የጠየቁ በዞኑ ያያ ጉለሌ ወረዳ ድሬ ዳለቲ የተባለች ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አባት፣ አራት የራሳቸውን እና የዘመድ ልጆችን ያስተምሩ እንደነበረ ያስታውሳሉ።
እኚህ አባት በአካባቢያቸው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አባላት በስፋት መንቀሳቀስ መጀመራቸውን ተከትሎ ከመንግሥት ኃይሎች ጋር የሚደረግ ግጭት የልጆቻቸውን ሕልም እንዳጨለመ ይናገራሉ።
“የዛሬ ሦስት ዓመት የዳለቲ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተቃጠለ። ትምህርት ቤቱ በእሳት ወደመ፤ትምህርትም በዛው ተቋረጠ። ልጆች ትምህርት ትተው በቤት ከተቀመጡ ሦስት ዓመት አለፋቸው” ይላሉ።
“የዛሬ ሦስት ዓመት 5ኛ ክፍል የነበረው ልጄ ዘንድሮ 8ኛ ክፍል ይደርስ ነበር። ይህ ግን ሳይሆን ቀርቷል። ልጆቻችን ስሜታቸው ተጎድቷል። እየሆነ ያለው ነገር ወላጆችንም በጣም እየጎዳ ነው።” ብለዋል።
በሁኔታው ተስፋ የቆረጠ ወላጅ ልጆቹን ለእረኝነት እና ለትዳር አሳልፎ እየሰጠ ነው ሲሉ እኚህ አባት በቁጭት ይናገራሉ።

የፎቶው ባለመብት, SM
“በአንድ ዞን ብቻ ከ67ሺህ በላይ ተማሪ ከትምህርት ውጪ ነው ብሎ ማሰብ ለእኛ ትልቅ ሃፍረት ነው” የሚሉት የዞኑ ትምህር ቢሮ ኃላፊ አቶ ጋሸው አክሊሉ ናቸው።
በአካባቢው ትምህርት ቤቶች ላይ ከሚፈጸመው በእሳት የማቃጠል ተግባር በተጨማሪ በትምህርት ተቋማቱ ላይ ዘረፋዎች በስፋት እንደሚፈጸሙ ኃላፊው ይናገራሉ።
በዞኑ በሚገኙት ሂዳቡ አቦቴ፣ ወረ ጃርሶ እና ኩዩ ወረዳዎች ታጣቂዎች የትምህርት ቤት ቆርቆሮዎችን እየነቀሉ ጫካ ወስደው ለራሳቸው መጠለያ ካምፕ እንደሚገነቡም ገልጸዋል።
“ለኦሮሞ ነጻነት እታገላለሁ የሚል ቡድን እንዴት ትምህርት ቤት አፍርሶ ለራሱ መጠለያ ይሰራል? እንዴት ኮምፒዩተር እና ሶላር ይዘርፋል?” ሲሉ አቶ ጋሻው ይጠይቃሉ።
ከዚህ በተጨማሪ በዋጪሌ ወረዳ የትምህርት ቤት ርዕሰ መምህርን በተማሪዎች ፊት በመግረፍ የማዋረድ ተግባር እየፈጸሙ የመማር ማስተማር ስራውን እያደናቀፉ ነው ሲሉ በአካባቢው በስፋት የሚንቀሳቀሱትን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አባላትን ይከስሳሉ።

እንደ አቶ ጋሻው ገለጸ በዞኑ ከስራ ወጪ የሆኑት በርካታ ትምህርት ቤቶች የሚገኙት በደራ ወረዳ ነው።
“በደራ ወረዳ በጠቅላላ 92 ትምህርት ቤቶች አሉ። ከእነዚህ ውስጥ እያስተማሩ ያሉት 28 ብቻ ናቸው። በዛ ደግሞ ሁለት ቡድን ነው ያለው” በማለት በኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች ድንበር አካባቢ የፋኖ እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አባላት እንደሚንቀሳቀሱ ይገልጻሉ።
አቶ ጌታቸው ትምህርት ቤቶችን ወደ ሥራ ለመመስ ጥረቶች ቢኖሩም በአካባቢው ሰላም ስለሌለ የተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ የመመለስ ተስፋ እንደጨለመ ነው ይላሉ።
ቢቢሲ በአካባቢው ይንቀሳቀሳል ከተባለው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ስለቀረበበት ውንጀላ ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።
የተባበሩት መንግሥታት በኢትዮጵያ በግጭት እና በተፈጥሯዊ አደጋዎች ምክንያት ከስምንት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ቤት ውጪ መሆናቸውን ይገልጻል።
እንደ ተመድ አሃዝ ከሆነ በመላው አገሪቱ ወደ ዘጠኝ ሺህ የሚጠጉ ትምህርት ቤት በተለያዩ ምክንያቶች በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ ወድመዋል።












