እስራኤል እና ሄዝቦላ ቀጠናውን ወደለየት ጦርነት ውስጥ ሊያስገባ የሚችል የተኩስ ልውውጥ አደረጉ

የፎቶው ባለመብት, EPA
እስራኤል የሄዝቦላ የሮኬት እና የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃቶችን ለመከላከል በበርካታ የጦር ጀቶች የታገዘ ድብደባዎችን ማድረጓን አስታውቃለች።
በመቶዎች የሚቆጠሩ የእስራኤል ጀቶች እሁድ ንጋት ላይ የሄዝቦላ የሮኬት ማስወንጨፊያዎችን ማውደማቸውን የአገሪቱ ጦር አስታውቋል።
ሄዝቦላ እና አማል የተባለው አጋሩ ሦስት ተዋጊዎቻቸው መገደላቸውን አስታውቀዋል።
በኢራን የሚደገፈው ቡድን የእስራኤል ወታደራዊ ጣቢያዎችን ዒላማ ያደረጉ 320 ሮኬቶችን ወደ ሰሜናዊ እስራኤል ማስወንጨፉን አስታውቋል።
እንደ የእስራኤል ጦር ከሆነ በሄዝቦላ ጥቃት አንድ የአገሪቱ ወታደር ተገድሏል።
ምንም እንኳ እስራኤል እና ሄዝቦላ የተስፋፋ ጦርነት ማድረግ አንፈልግም ይበሉ እንጂ ሁለቱም ኃይሎች እራሳቸውን ለጦርነት እያዘጋጁ ነው።
የትናንቱ የተኩስ ልውውጥም ቀጠናውን ወደለየትለት ጦርነት ሊያስገባ ይችላል የሚል ከፍተኛ ስጋትን ፈጥሮ ነበር።
አሜሪካ ለ10 ወራት ተፋጠው የቆዩት እስራኤል እና ሄዝቦላ ወደጦርነት እንዳያመሩ እና በመካከለቸው ሌላ ውጥረት እንዳይከሰት እየሰራሁ ነው ብላለች።
የእስራኤል መካለከያ ሚኒስቴር እሁድ ንጋት ነሐሴ 19/2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ወደ እስራኤል ሚሳኤሎችን እና ሮኬቶችን ለመተኮስ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች መታየታቸውን ተከትሎ ራስን የመከላከል እርምጃ መውሰዱን አስታውቋል።
“ይህን ስጋት ለመቀልበስ በተደረገ ራስን የመከላከል ተግባር አይዲኤፍ (የእስራኤል መከላከያ ኃይል) አሸባሪዎችን ዒላማ ያደረገ ጥቃት እየፈጸመ ይገኛል” ሲሉ የእስራኤል ጦር ቃል አበባይ ዳንኤል ሃጋሪ ተናግረዋል።
ምንም እንኳ የመስከረም 26ቱን የሐማስን ድንገተኛ ጥቃት ተከትሎ እስራኤል እና ሄዝቦላ በየዕለቱ ሊባል በሚችል መልኩ የተኩስ ልውውጥ ሲያደርጉ ቢቆዩም፤ ትናንት የተደረገው የተኩስ ልውውጥ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከፍተኛው ነው ተብሏል።
ባለፉት ወራት እስራኤል በሊባኖስ በሚገኙ ዒላማዎች ላይ በፈጸመቻቸው ጥቃቶች አብዛኛዎቹ የሄዝቦላ ተዋጊዎች የሆኑ 560 ሰዎች መገደላቸውን የሊባኖስ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
የተባበሩት መንግሥታት ደግሞ በእስራኤል እና ሊባኖስ አዋሳኝ የድንበር አካባቢዎች የሚኖሩ ወደ 200 ሺህ የሚጠጉ ነዋሪዎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል ይላል።
ልክ እንደ ሄዝቦላ ሁሉ ሐማስ በኢራን የሚደገፍ ሲሆን ሁለቱም ቡድኖች በበርካታ ምዕራባውያን አገራት አሸባሪ ተብለው ተፈርጀዋል።

የፎቶው ባለመብት, AFP
ሄዝቦላ ትናንት በእስራኤል የከፈተው ተኩስ ከእአአ 2006 በኋላ ከፍተኛው ነው።
የሄዝቦላ መሪ ሐሰን ነስራላህ የቡድኑ ጥቃት የእስራኤል ወታደራዊ ጣቢያዎችን ዒላማ ማድረጉን በቴሌቪዥን በተላለፈ ንግግራቸው አብራርተዋል።
የእስራኤል መከላከያ ኃይል ወደ 100 የሚጠጉ የጦር ጀቶቹ በተሳተፉበት የአየር ድብደባ በ40 ቦታዎች የነበሩ በሺዎቹ የሚቆጠሩ የሄዝቦላ የሮኬት ማስወንጨፊያዎችን ማውደሙን አስታውቋል።
እንደ የእስራኤል መከላከያ ኃይል ከሆነ ሄዝቦላ ከ150 በላይ ተተኳሾችን ከሊባኖስ ድንበር ሆኖ ወደ እስራኤል ተኩሷል።
የተኩስ ልውውጡን ተከትሎ የደኅንነት ካቢኔያቸውን አስቸኳይ ስብሰባ የጠሩት የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ “ዛሬ የተፈጸመው ነገር ማብቂያ አይደለም” ሲሉ ውጥረቱ ተባብሶ ሊቀጥል እንደሚችል ተናግረዋል።
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሆነ የእስራኤል ጦር ሄዝቦላ ያስወነጨፋቸውን ሁሉንም አጭር ርቀት ሮኬቶችን እና ሰው አልባ አውሮፕላኖች መትቶ ጥሏል።

የፎቶው ባለመብት, EVN
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ እስራኤል ካትዝ ደግሞ አገራቸው ጦርነት እንደማትፈልግ ይሁን እንጂ ዜጎቿን ለመጠበቅ ያሏትን አማራጮች በሙሉ እንደምትጠቀም በመላው ዓለም ላሉ አቻዎቻቸው መናራቸውን ገልጸዋል።
እስራኤል የሄዝቦላ ሮኬቶችን እና ድሮኖችን አውድሚያለሁ ትበል እንጂ የሺዓ ሙስሊም ቡድን የሆነው ሄዝቦላ 11 ወታደራዊ ጣቢያዎችን መምታቱን አስታውቋል።
ሄዝቦላ ይህን ጥቃት እስራኤል ላይ የከፈተው ሐምሌ ማብቂያ ላይ የቡድኑ ወታደራዊ ኮማንደር የነበሩት ፉአድ ሹከርን ግድያ ለመበቀል ነው ብሏል።
ቡድኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሮኬቶችን እና ድሮኖችን ካስወነጨፈ በኋላ ወታደራዊ ዘመቻው “ስኬታማ ሆኖ ተጠናቋል” ብሏል።
ከእስራኤል እና ሐማስ ጦርነት በኋላ በመካከለኛው ምስራቅ ከፍተኛ ውጥረት መከሰቱን ተከትሎ እስራኤል እና ሊባኖስ የተኩስ ልውውጥ ሲያደርጉ ቆይተዋል።
ምዕራባውያን እና በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ አገራት ቀጠናውን ወደለየት ጦርነት ሊያስገባ ከሚችል እንቅስቃሴ እስራኤል እና ሄዝቦላ እንዲታቀቡ ሲጠይቁ ቆይተዋል።
የእስራኤል እና የሄዝቦላ ጦርነት አይቀሬ ነው መባሉን ተከትሎ እንደ አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ካናዳ፣ ጀርመን እና ፈረንሳይ ያሉ ምዕራባውያን አገራት ዜጎቻቸውን ከሌባኖስ ሲያስወጡ ቆይተዋል።












