የኢንተርኔት አገልግሎት ቢቆም ዓለም ምን ልትመስል ትችላለች?

የኢንተርኔት መቋረጥ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኢንተርኔት በአምባገነን መንግሥታት ወይም በሻርክ ጥቃት አልያም በአንድ ግለሰብ ስህተት በቀላሉ ችግር ውስጥ ሊገባ ይችላል።

በቅርቡም አንድ መተግበሪያ ላይ ማሻሻያ ሲደረግ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኮምፒውተሮችን አቁሟል። አየር መንገዶች በሺዎች የሚቆጠሩ በረራዎችን ሰርዘዋል። ሆስፒታሎች ቀዶ ሕክምና አቋርጠዋል። የአደጋ ጊዜ ጥሪ ተስተጓጉሏል።

ማይክሮሶፍት እና ክራውድስትራይክ በስተመጨረሻ ችግሩን ፈተውታል። ሆኖም የተፈጠረው መቆራረጥ አንድ ሳምንት ቆይቷል።

ሁሉም እንቅስቃሴ ከኢንተርኔት ጋር የተሳሰረ ከመሆኑ አንጻር እንዲህ ዓይነት መሰናክል ከዚህ በኋላም መከሰቱ አይቀርም።

ከዚህ ቀደም የተከሰቱ የኢንተርኔት መቆራረጦች ዓለም ያለ ኢንተርኔት ምን ሊገጥማት እንደሚችል ማሳያ ናቸው።

የበይነ መረብ ደኅንነት ባለሙያ እና የቴክኖሎጂ ተንታኝ ሪቴሽ ኮታክ “አሁን እያገኘን ያለው ጥቅም ዋጋም ያስከፍለናል” ይላሉ።

ዋነኛው የኢንተርኔት መቋረጥ የሚባለው በ1997 የተከሰተው ነው። ኔትወርክ ሶሉሽንስ የተባለው ተቋም ነበር የገጠመው።

ኒው ዮርክ ታይምስ እንደዘገበው፣ በወቅቱ በዶት ኮም እና ዶት ኔት የሚያልቁ ድረ ገጾች ሥራ አቁመው ነበር።

በመላው ዓለም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ድረ ገጾችን አቋርጧል። ሰዎች ኢሜል አይደርሳቸውም ነበር። ተቋማት ከደንበኞቻቸው ጋር መገናኘት ባለመቻላቸው ሥራቸው ተጎድቷል።

ኢንተርኔት ያኔ የነበረውን ጥቅም አሁን ካለው ጋር ስናነጻጽረው ያኔ የደረሰው ጉዳት ውስን ሆኖ ሊታይ ይችላል።

አሁን ላይ እያንዳንዱ ሕይወታችን ከኢንተርኔት ጋር የተሳሰረ ነው። ኢንተርኔት ተቋረጠ ወይም ኔትወርክ ተስተጓጎለ ማለት ሕይወታችን ምስቅልቅሉ ይወጣል ማለት ነው።

በአውሮፓውያኑ 2019 በማታኑስካ-ሱስትና በአላስካ ማኅበረሰብ ላይ የደረሰው የበይነ መረብ ጥቃት እንደ ምሳሌ ይጠቀሳል።

100 ሺህ ሰዎች ሕይወታቸው እንዲቆም አስገድዷል። የማኅበረሰቡ አባል የሆነችው ሔለን ሙንዝ “ሁሉም ነገር ቀጥ ብሎ ቆመ። እስካሁን አካባቢያችን ኮምፒውተሮችን አስተካክሎ አልጨረሰም” ትላለች።

ለአሥር ሳምንታት ያህል የኢንተርኔት መስመሩ አልተስተካከለም። ሠራተኞች በታይፕ ለመጻፍ ተገደው ነበር።

‘ትልቅ ኬብል ያስፈልገናል’

የአርሜኒያ ኢንተርኔት በአንድ ኬብል ላይ የተመሠረተ ነበር። መስመሩ በጆርጅያ በኩል ነበር የሚያልፈው።

በ2011 (እአአ) አንድ የ75 ዓመት አዛውንት የ2.9 ሚሊዮን አርመናውያንን ኢንተርኔት አቋረጠዋል።

አዛውንቷ ወደ ጆርጅያ ለመሻገር ሲሉ መስመሩን በስለት ቆርጠውት አለፉ።

አዛውንቷ ቢታሰሩም ኋላ ላይ ዕድሜያቸው ከግምት ገብቶ ተለቀዋል።

ሲለቀቁ “ኢንተርኔት ምን እንደሆነ አላውቅም” ነበር ያሉት።

የአውሮፓ፣ የመካከለኛው ምሥራቅና ማዕከላዊ እስያ የኢንተርኔት ፖሊሲ አማካሪ ቫን ሆፕስፓን “ኢንተርኔት ሲቋረጥ እንደ ማበድ ነው የሚያደርገን” ይላሉ።

ይህም በሺህ ኪሎ ሜትሮች ርዝመት ባለው የኢንተርኔት መስመር ላይ መተማመን ያለውን ችግር ያስረዳሉ።

መስመሮቹን ዲጂታል ማድረግ የተሻለ አማራጭ ሊሆን ይችላል።

በ2017 ዚምባብዌ ለግማሽ ቀን ኢንተርኔት አልነበራትም።

በደቡብ አፍሪካ በኩል የሚያልፍ ኬብልን ትራክተር ቆርጦት ነው ችግሩ የተከሰነው።

ከባሕር በታች የተዘረጉ ኬብሎች ለሻርክ ጥቃት ተጋላጭ ናቸው።

ከዚህ ቀደም ሻርኮች ኬብሎችን በጥሰዋቸው ያውቃሉ።

ሻርኮች እና ሌሎችም የዓሣ ዝርያዎች የሚያደርሱት ጥቃት ከ1964 ጀምሮ በስልክ እና በቴሌግራፍ መስመር ላይ ችግር ሲፈጥር ቆይቷል።

ጉግል ከውሃ በታች ያሉ ኬብሎቹን የሚጠቀልለውም ለዚህ ነው።

ሻርክ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ዲጂታሉ ዓለም ቢቋረጥስ?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በአውሮፓውያኑ 2022 የካናዳው ሮጀንስ ኮሚዩኒኬሽን በገጠመው ችግር የካናዳ አንድ አራተኛ የኢንተርኔት እና የስልክ መስመር ተቋርጦ ነበር።

በዚህም ምክንያት አስራ አንድ ሚሊዮን ሰዎች አጠቃላይ እንቅስቃሴያቸው እንዳልነበር ሆኖ ተስተጓጉሏል።

የአደጋ ጊዜ ጥሪ ተቋርጧል። ሆስፒታሎች ቀጠሮ ሰርዘዋል። የበይነ መረብ ክፍያ ተቋርጧል። ድምጻዊው ዘ ዊኬንድ (አቤል ተስፋዬ) ኮንሰርቱን ለመሰረዝ ተገዷል።

ኮታክ የተባለው የቶሮንቶ ነዋሪ “ጓደኛዬ የሮጀርስ ስልክ ተጠቃሚ ነበረች። የዚያን ቀን ፈተና አምልጧታል። ምክንያቱም የመፈተኛ ክፍሏን ቁጥር ከኢሜሏ ላይ ማውጣት አልቻለችም” ይላል።

አንዳንዴ ኢንተርኔት የሚያቋርጡት መንግሥታት ናቸው።

አምባገነን መንግሥታት እና ዲሞክራሲያዊ የሚባሉትም ሳንሱር ለማድረግ ሲሉ ኢንተርኔት ላይ ማቋረጥ እና ጫና የማሳደር ተግባርን ይፈጽማሉ።

በአክሰስ ናው የመረጃ ተንታኝ የሆኑት ዛክ ሮሰን “ከ2016 ጀምሮ 1500 ጊዜ በመንግሥታት፣ በታጣቂዎች እና በፖሊስ ኃይሎች ኢንተርኔት ተቋርጧል” ይላሉ።

በቅርቡ የባንግላዴስ መንግሥትን ከሥልጣን ያስወገዱት በተቃዋሚ ተማሪዎች እና በፖሊስ መካከል ግብግብ መፈጠሩን ተከትሎ መንግሥት ኢንተርኔትን አቋርጦ ነበር።

የመንግሥት ኃይሎች በወሰዷቸው እርምጃዎች ቢያንስ 150 ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል።

በአሁኑ ወቅት የኢንተርኔት አገልግሎት ማግኘት ሰብአዊ መብት ነው የሚለው እንቅስቃሴ ዕውቅና እያገኘ ነው።

“ሥራ፣ የጤና አገልግሎት፣ ትምህርት፣ ንግድ፣ ከሰው ጋር መገናኘት እና አጠቃላይ ዓለምን ማግኘት የምንችልበት መንገድ ሲቋረጥ ምን ሊፈጠር እንደሚችል አስቡት። ኢንተርኔት ሲቋረጥ የሰብአዊ መብት ጥሰትን መመዝገብም አይቻልም” ሲሉ ተንታኙ ያስረዳሉ።

ሕንድ ተቃውሞን ለማፈን ኢንተርኔት በመዝጋት ቀዳሚ አገር ናት። ሌሎች 83 አገራትም ተመሳሳይ እርምጃ ይወስዳሉ።

ከዚህ አንጻር የኢንተርኔት አገለግሎትን በማቋረጥ በዋናነት ኢራን፣ ሩሲያ፣ አልጄሪያ፣ ሴኔጋል፣ ታንዛኒያ፣ ካሜሩን እና ቬንዝዌላን መጥቀስ ይቻላል።

ኢንተርኔት በዋነኛነት የሚጓዝበት ኬብል ከተጎዳ መጠነ ሰፊ ችግር ያስከትላል።

ይህ መስመር ያለውን ጠቀሜታ ያህል ጥበቃ እየተደረገለትም አይደለም።

የመረጃ ደኅንነት ተቋሙ ዲስኮኔክት ዋና ዳይሬክተር ካሲ ኦፕንሀይም እንደሚሉት፣ ከዚህ ቀደም እና በኢንተርኔት ማስተላላፊያ መስመር ላይ የተከሰተው ችግር አንቂ ደውል ነው።

“በአንድ ዘርፍ ውስጥ የሚሳተፉ ውስን ሲሆኑ ለችግር ተጋላጭነት ይሳፋል። የኢንተርኔት አቅርቦት ላይ ያሉት በጣም ጥቂት ተቋማት ናቸው” ይላሉ።

በጥቂት ተቋማት ዘርፉ መመራቱ የችግሩ አካል እንደሆነ ያስረዳሉ። አንድ ተቋም ኃያል ሆኖ ሲወጣ እዚያ ተቋም ላይ የሚከሰት ማንኛውም መስተጓጎል በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች እና ተቋማትን ይጎዳል ማለት ነው።

ይሄንን ጉዳይ መንግሥታት ሊያስቡበት እንደሚገባ ባለሙያው ያሳስባሉ።

ሚሊኒየሙ በጀመረበት በአውሮፓውያኑ 2000 ላይ ኮምፒውተሮች ቀን መቁጠሪያ ሲያስገቡ የኢንተርኔት መስተጓጎል ይፈጠራል የሚል ስጋት (ዋይ2ኬ ባግ) ተነስቶ እንደነበር ይታወሳል።

የኢንፎርሜሽን ኮሚዪኒኬሽን (አይቲ) ባለሙያዎች ቀን መቁጠሪያዎቹ ላይ አስፈላጊውን ማሻሻያ በማድረግ ሊከሰት የነበረውን ችግር መቀልበሳቸው አይዘነጋም።

በወቅቱ ሰዎች በተፈጠረባቸው ፍርሃት ምግብ እና መሣሪያ እስከማከማቸት ደርሰው ነበር።

እስካሁን ከታዩት የኢንተርኔት መቋረጦች በአጠቃላይ የከፋው ለወደፊት ሊመጣ እንደሚችል ይታመናል። የመረጃ ደኅንነት ባለሙያዎች ያንን ቀን በተጠንቀቅ እየተጠባበቁም ነው።