በዓለም ዙሪያ በረራዎችን ጨምሮ እንቅስቃሴዎችን ቀጥ ስላደረገው የአይቲ ብልሽት የምናውቀው

መንገደኞች በአውሮፕላን ማረፊያ ላይ

የፎቶው ባለመብት, EPA

አርብ ሐምሌ 12/2016 ዓ.ም. በዓለማችን ከባድ የተባለ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ (አይቲ) ብልሽት ተከስቶ ቀውስ አስከትሏል።

በዚህም ሳቢያ በበርካታ አገራት የትራንስፖርት፣ የባንክ እና የጤና አገልግሎቶች ተስተጓጉለዋል።

በአይቲ መቋረጥ ምክንያት በርካታ በረራዎች ተሰርዘው፣ አውሮፕላኖች እንዳይነሱ የተደረጉ ሲሆን የባንክ እና ጤና ተቋማትም አገልግሎት መስጠት ተስኗቸው ነበር።

በዓለም ዙሪያ ያሉ በርካታ ኮምፒውተሮች ስህተት መከሰቱን የሚያሳየውን ሰማያዊ ስክሪን እያሳዩ ነበር።

መንገደኞች በሰው መፈተሽ ስለነበረባቸው በዓለም ዙሪያ በሚገኙ አውሮፕላን ማረፊያዎች ውስጥ ረዣዥም ወረፋዎች እና መጓተቶች ታይተዋል።

እንዲሁም በርካታ በራራዎች ተሰርዘዋል።

በሳይበር ደኅንነት ላይ የሚሠራው ክራውድስትራይክ የተሰኘው ተቋም ችግሩ የተፈጠረው የማይክሮሶፍት ዊንዶውስ ኮምፒተሮችን ከጥቃቶች ለመከላከል በተሠራው ፀረ-ቫይረስ መተግበሪያ ማሻሻያ (አፕዴት) ምክንያት መሆኑን አምኗል።

አክሎም ማይክሮሶፍት በበኩሉ በአይቲ ብልሽት ምክንያት የተፈጠረው ችግር ዘለቄታዊ ተጽእኖ እንዳያመጣ የመከላከል እርምጃ እየወሰድኩ ነው ብሏል።

እስካሁን ስለ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ (አይቲ) ብልሽቱ ምን እናውቃለን?

የአይቲ መቋረጥ እንዴት አጋጠመ?

መቋረጡ እንዴት አጋጠመ የሚለው አሁንም ትንሽ ግልጽ አይደለም።

ክራውድስትራይክ የፀረ ቫይረስ መተግበሪያዎችን በማምረት የሚታወቅ ሲሆን፣ ይህም መረጃ መንታፊዎች አሁን የተፈጠረውን መስተጓጎል እንዳይፈጥሩ ለመከላከል ታስቦ ነው።

የክራውድስትራይክ ኃላፊ ጆርጅ ኩርትዝ ችግሩ የተፈጠረው ዊንዶውስ በተሰኙት ኮምፒውተሮች ላይ ብቻ ሲሆን፣ ይህም በቅርብ ጊዜ ከተደረገው ማሻሻያ (አፕዴት) ጉድለት ምክንያት የተከሰተ መሆኑን ገልጸዋል። “ችግሩ ተለይቶ ታወቋል እንዲሁም ማስተካከያም ተዘርግቷል” ብለዋል።

“አክለውም ይህ የፀጥታ ችግር ወይም የሳይበር ጥቃት አይደለም” ሲሉም ተደምጠዋል።

በማሻሻያው (አፕዴቱ) ላይ በትክክል ምን ዓይነት ችግር እንደተፈጠረ ገና ይፋ አልሆነም። ችግሩ ሊቀረፍ የሚችለው አንድ የተወሰነ ፋይል ማጥፋትን የሚያካትት መሆኑን ኩባንያው መጥቀሱን ተከትሎ የቀውሱ መንስዔ አንድ የተበላሸ ፋይል ብቻ ሊሆን እንደሚችል ተጠቁሟል።

ችግሩ መቼ ሊቀረፍ ይችላል?

ችግሩ መቼ ሊቀረፍ ይችላል? ለሚለው ምላሹ የተወሰነ ጊዜ ሊወስድ ይችላል ነው።

የክራውድስትራይክ ኃላፊው ከርትዝ እያንዳንዱ ደንበኞች ከዚህ ብልሽት ሙሉ በሙሉ ማገገማቸውን ማረጋገጥ የኩባንያው “ተልዕኮ” ነው ሲሉ ለኤንቢሲ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

“በደንበኞች፣ በመንገደኞች እንዲሁም ድርጅቶቻችንን ጨምሮ በዚህ ጉዳት ለደረሰበት ማንኛውም ሰው በጣም አዝነናል” ብለዋል።

ኃላፊው አንዳንድ ሥርዓቶች በፍጥነት ሊስተካከሉ እንደሚችሉ ጠቅሰው ሌሎች ደግሞ “ሰዓታት ወይም ረዘም ያለ ጊዜ ሊወስዱ ይችላሉ” ሲሉም አክለዋል።

ክራውድስትራክ ብልሽቱን ለመቅረፍ ማስተካከያ የሚለውን ይፋ አድርጓል።

እነዚህም ማስተካከያዎች ለእያንዳንዱ እና ለተጎዱ ኮምፒውተሮች በተናጠል መተግበር እንዳለባቸው ተገልጿል።

እንደ መፍትሄ የተቀመጠው ኮምፒውተሮችን በእጅ ሪቡት ወይም እንደ አዲስ ለማስጀመር የኮምፒውተር ኦፐሬቲንግ ሲስተም እንደገና መጫን ያስፈልጋል ተብሏል። ይህ በበርካታ ቦታዎች ላሉ የአይቲ ዲፓርትመንቶች ከፍተኛ ራስ ምታት እንደሚሆን ጥርጥር የለውም።

መፍትሄው ምን ይሆን?

እዚህ ላይ ልብ ልንለው የሚገባው ጠቃሚ ነገር በቤት ውስጥ ያሉ ኮምፒውተሮች ወይም የግል ሞባይል ስልኮች የዚህ ችግር ተጠቂ አይደሉም።

ይህ መቋረጥ ወይም ብልሽት ያጋጠመው በንግድ ወይም በተቋማት ላይ ባሉ ኮምፒውሮች ላይ ነው።

ማይክሮሶፍት ደንበኞቹ መሠረታዊ የሚባለውን ኮምፒውተር አጥፍቶ እንደገና እንዲያበሩ እየመከረ ነው። በአንዳንድ ሁኔታዎችም ኮምፒውተሮችን እስከ 15 ጊዜ ድረስ አጥፍታችሁ አብሩ ብሏል።

ግዙፉ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ማይክሮሶፍት ይህ እርምጃ ኮምፒውተራቸው ከስክሪኑ ጋር ተመሳሳይ ባልሆነ ቦታ በሚገኙ የ’ቨርቹዋል ማሽኖች’ መፍትሄ እንደሆነላቸው አስታውቋል።

“ኮምፒውተሮቹን በተደጋጋሚ አጥፍቶ ማስነሳት ሊያስፈልግ ይችላል። እስካሁን ባገኘነው ምላሽ ኮምዊተሮቹን ‘ሪቡት’ ማድረግ ውጤታማ ሆኖ ተገኝቷል” ብሏል።

እንዲሁም ጠለቅ ያለ የኮምፒውተር እውቀት ላላቸው ደንበኞች ደግሞ አንድ የተጠቀሰ ፋይል ማጥፋት እንዳለባቸው ተገልጿል።

የክራውድስትራይክ ሠራተኛም በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ይህንን ያሉትን ተመሳሳይ መፍትሄ ሲገልጹ ነበር። እነዚህ ማስተካከያዎች በአይቲ ባለሙያዎች እና ልሂቃን የሚተገበር ሲሆን፣ ለመደበኛ ተጠቃሚዎች የሚሆን ግን አይደለም።

በዚህ ብልሽት የትኞቹ አየር ማረፊያዎች ተጎዱ?

ችግሮቹ በመላው ዓለም ቢከሰቱም መጀመሪያ የተስተዋሉት በአውስትራሊያ ውስጥ ነው። የተለያዩ ኢንዱስትሪዎች ላይ ተጽእኖ ቢያሳድሩም በተለይም የአየር ትራንስፖርት ዘርፉ ላይ ቀውስ ፈጥሯል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ3 ሺህ 300 በላይ በረራዎች እንዲሰረዙ ምክንያት ሆኗል።

  • በዩኬ አየር ማረፊያዎች በለንደኑ ስታንስቲድ እና ጋትዊክ ረዣዥም ወረፋዎች እንዲሁም መዘግየቶች እና መስተጓጎሎች ተስተናግደዋል።
  • የአየርላንዱ ርያኤር አየር መንገድ ጥቂት ቁጥር ያላቸውን በረራዎች ለመሰረዝ ተገድጃለሁ ብሏል።
  • የብሪታንያው አየር መንገድ እንዲሁ በርካታ በረራዎችን ሰርዟል።
  • በርካታ የአሜሪካ አየር መንገዶች በተለይም ዩናይትድ እና ዴልታ አርብ ዕለት በዓለም ዙሪያ ያሉ በረራዎችን አቁመው ነበር። የአውስትራሊያው አየር መንገዶች ቨርጂን አውስትራሊያ እና ጄትስታር እንዲሁ በረራዎችን ማዘግየት ወይም መሰረዝ ነበረባቸው።
  • በተጨማሪም የቶክዮ፣ አምስተርዳም እና ደልሂ አየር ማረፊያዎችም በዚሁ የአይቲ ቀውስ መስተጓጎሎች ገጥመዋቸዋል።
  • ከአየር የትራንስፖርቱ ዘርፍ በተጨማሪ በዓለም ዙሪያ ባሉ የክፍያ ሥርዓቶች፣ የባንክ እና የጤና አገልግሎቶች ሥራቸውን ቀጥ እንዲል አድርጎት ነበር።
  • በአላስካ የ911 ድንገተኛ ጥሪ አገልግሎት ላይ ችግር ተፈጥሮ የነበረ ሲሆን፣ ስካይ ኒውስ አርብ ዕለት ለበርካታ ሰዓታት ሥርጭቶቹን ማስተላለፍ አልቻለም ነበር።

ይህ የአይቲ ብልሽት አንዳንድ ሰዎችን በወቅቱ ደመወዛቸው እንዳይከፈላቸው አስተጓጉሏል።

ግሎባል ፔይሮል አሶሲየሽን ኃላፊ ሜላኒ ፒዜ የደመወዝ ዝርዝር የያዙ ሶፍትዌሮችን መክፈት ያልቻሉ በርካታ ደንበኞች ማነጋራቸውን ለፒኤ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

በአይቲ መቋረጥ ምክንያት ኩባንያዎች በዚህ ሳምንት ማካሄድ የነበረባቸውን የሠራተኞች የደመወዝ ሂደት ባለመጨረሳቸው የወሩን መጨረሻ የደመወዝ ክፍያ እንዲዘገይ ሊያደርገው ይችላል ብለዋል።

በዚህ ሁሉ መካከል ድንገት ኮምፒውተሬ ወይም ስልኬ በዚህ ሊጎዳ ይችላል ብለው ከሰጉ አያሳስብዎ።

የዚህ የአይቲ ቀውስ ምክንያት የሆነው ሶፍትዌር (መተግበሪያ) በንግድ ተቋማት ጥቅም ላይ የሚውል ነው። ይህም ማለት የግል ኮምፒውተሮች ይህ ችግር የማይመለከታቸው ሲሆን፣ ኩባንያው እንደ ማስተካከያ የጠቆመው ፋይል ማጥፋትም ማድረግ አይጠበቅባቸውም።

ክራውድስትራይክ ምንድን ነው?

በቴክኖሎጂው ዘርፍ ስመ ጥር ያልሆነው ክራውድስትራይክ የተሰኘው ኩባንያ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲህ ዓይነት ቀውስ ማስከተሉ የዘመናችንን የዲጂታል መሠረተ ልማት ውስብስነት የሚያሳይ ነው።

በኦስቲን ቴክሳስ ተቀማጭነቱን ያደረገው ይህ ኩባንያ እንደ በርካታ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ያን ያህል ጊዜ አልቆየም።

ከ13 ዓመታት በፊት የተመሠረተው ኩባንያው በአሁኑ ወቅት 8 ሺህ 500 ሠራተኞች አሉት።

የሳይበር ደኅንነት አገልግሎቶችን የሚሰጠው ክራውድስትራይክስ የመረጃ ምንተፋዎች ሲያጋጥሙ መፍትሄዎችን ይሰጣል።

በአውሮፓውያኑ 2014 ሶኒ ፒክቸርስ የኮምፒውተር ሥርዓቱ የተጠለፈበትን አጋጣሚ ጨምሮ በበርካታ ታዋቂ የሳይበር ጥቃቶች በተደረጉ ምርመራዎች ላይ ተሳትፏል።

ለዓመታት የአይቲ ችግሮችን መፍትሄ ይሰጥ የነበረው ይህ ድርጅት በአሁኑ ወቅት በሶፍትዌር ማሻሻያ ምክንያት በተከሰተ ጉድለት ራሱ ቀውስን ፈጥሯል።

የድርጅቱ የመጨረሻው የገቢ ሪፖርት ላይ 24 ሺህ ደንበኞችን ማፍራት እንደቻለ ገልጿል። ይህም ማለት የቀውሱን ስፋት ብቻ ሳይሆን ያንን ለማስተካከል ምን ያህል ፈታኝ እንደሆነ አመልካች ነው።

የኩባንያው ደንበኞች ትልልቅ ድርጅቶች ከመሆናቸው አንጻር የተጎዱት ኮምፒውሮች ብዛትንም ለመገመት አስቸጋሪ ነው።