በአይቲ ብልሽት በመላው ዓለም በረራዎች ተቋረጡ፤ ባንክ እና ጤና ተቋማት ሥራቸውን አቆሙ

አየር መንገድ ውስጥ መጉላላት የገጠማቸው መንገደኞች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በመላው ዓለም ባጋጠመ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ብልሽት ምክንያት የግንኙነት መቋረጦች በማጋጠሙ በተለያዩ አገራት የሚገኙ ወሳኝ ተቋማት ሥራ መስተጓጎሉ ተገለጸ።

በዚህ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ (አይቲ) አገልግሎት መቋረጥ ሳቢያ በረራዎች ተስተጓጉለዋል፣ ባንኮች እና ሆስፒታሎች ሥራቸውን ሲያቆሙ መገናኛ ብዙላን ሥርጭታቸው ተቋርጧል።

የአይቲ ብልሽቱን ተከትሎ በመላው ዓለም የሚገኙ በርካታ አየር መንገዶች በረራዎችን መሰረዛቸውን የገለጹ ሲሆን፣ ብዙዎች ደግሞ በረራዎችን ለመሰረዝ ተገደዋል።

የአሜሪካዋ አልስካ ግዛት የአደጋ ጊዜ አገልግሎቶቿ ችግር እንደገጠማቸው የገለጸች ሲሆን፤ በአውስትራሊያ ያሉ ሱፐርማርኬቶች እና በበርካታ አገራት የሚገኙ መገናኛ ብዙኃን በሲስተም ብልሽት ሥራቸውን መከወን ተስኗቸዋል።

እስካሁን ድረስ ለአይቲ ብልሽቱ ይህ ነው የተባለ ምክንያት ግልጽ ባይደረግም፤ መስተጓጎል የገጠማቸው ተቋማት ችግሩ ከማይክሮሶፍት ኮምፒዩተር ሥርዓት ጋር የተያያዘ ነው እያሉ ነው።

ክራውድስትራይክ የተባለ የሶፍትዌር ኩባንያ ለዊንዶውስ ኮምፒውተሮች ያደረገው ማሻሻያ ለአይቲ ብልሽቱ ምክንያት ነው ብሏል።

ቀደም ሲል የማይክሮሶፍት 365 አገልግሎት በኤክስ ገጹ ደንበኞች የገጠማቸውን ችግር እየመረመረ መሆኑን ገልጿል።

ዘግይቶ ደግሞ ቢቢሲ ያነጋገራቸው የማይክሮሶፍት ቃል አቀባይ አብዛኛው ተቋርጦ የነበረው የኮምፒዩተር ሥርዓት ወደ ሥራ ተመልሷል ብለዋል።

ከፍተኛ የኮምፒዩተር ሥርዓት ብልሽት የገጠማት አውስትራሊያ እንደሆነችም ተነግሯል።

በአሜሪካ አልስካ ግዛት የሚገኙ ኃላፊዎች የአደጋ ጊዜ የጥሪ ማዕከል 911 በአግባቡ አገልግሎት እየሰጠ አለመሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በተለያዩ አገራት የሚገኙ ሰዎች የባንክ ካርዳቸውን ተጠቅመው ክፍያ መፈጸም እንደተቸገሩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ወጥተው አስተያየታቸውን እየሰጡ ነው።

በአሜሪካ ዩናይትድ፣ ዴልታ እና አሜሪካን ኤርላይንስ ሙሉ በሙሉ በረራዎችን ማቋረጣቸውን አስታውቀዋል።

በአውስትራሊያ የሚገኙት ቨርጅን እና ጄትስታር አየር መንገዶች ደግሞ በርካታ በረራዎቻቸው ተሰርዘዋል ወይም መዘግየት ገጥሟቸዋል።

በርካታ ተጓዦችን የሚያስተናግዱ እንደ በርሊን፣ ቶክዮ እና ዴልሂ ያሉ አየር መንገዶች እንዲሁ በብልሽቱ ችግር ገጥሟቸዋል።

ዛሬ የተከሰተው የአይቲ ብልሽት ከእአአ 2017 ወዲህ ከፍተኛው ነው እየተባለ ነው።

ከሰባት ዓመታት በፊት ‘ዋናክራይ’ የተባለው የሳይበር ጥቃት ያልተሻሻሉ ዊንዶውስ ኮምፒየተሮችን ዒላማ አድርጎ በ150 አገራት ከ300 ሺህ በላይ ኮምፒየተሮችን አበላሽቶ ነበር።