የኢትዮጵያ አየር መንገድን ተቃውመው ታስረው የነበሩት 3 የውጭ ዜጎች ከአገር ተባረሩ

በፖሊስ ተይዘው ከነበሩት ሁለቱ
የምስሉ መግለጫ, በፖሊስ ተይዘው ከነበሩት ሁለቱ

አዲስ አበባ ውስጥ ባለፈው ረቡዕ ሐምሌ 10/2016 ዓ.ም. በኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ ተቃውሞ ሲያሰሙ በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩ ሦስት የውጭ ዜጎች ከአገር ተባረሩ።

ሁለት አሜሪካውያን እና አንድ ብሪታኒያዊ አየር መንገዱ ጦጣዎችን ኢሰብዓዊ በሆነ አያያዝ ሞት ወደሚጠብቃቸው ቤተ-ሙከራዎች ያጓጉዛል በማት ሲቃወሙ ነበር በፖሊስ የተያዙት።

ሦስቱ ግለሰቦች ለ25 ሰዓታት በቁጥጥር ስር ከቆዩ በኋላ ሐሙስ ሐምሌ 11/2016 ዓ.ም. ወደ አየር ማረፊያ ተወስደው ከአገር እንዲወጡ መደረጋቸውን ምንጮች ሊቢቢሲ ተናግረዋል።

'ፒፐል ፎር ዘ ኢቲካል ትሪትመንት ኦፍ አኒማልስ' (ፔት) የተባለው ድርጅት የእስያ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄሰን ቤከር እና የ11 ዓመት ልጃቸው እንዲሁም የዩናትድ ኪንግደም የፔት ፋውንዴሽን የቅስቀሳ መሪ ሩበን ስኬትስ ለገሃር አካባቢ በሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ ለአንድ ቀን ያህል በእስር ላይ ቆይተዋል።

ሦስቱ ግለሰቦች የተያዙት በአዲስ አበባ ከተማ ቸርችል ጎዳና ከሚገኘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቲኬት ቢሮ ፊት ለፊት አየር መንግዱ “ጨካኝ የጦጣ ጭነቶችን ያቁም” የሚል መፈክር ካሰሙ በኋላ ነው።

የእስሳት መብት ተሟጋቾቹ በአዲስ አበባ ሐሙስ ሐምሌ 11/2016 ዓ.ም. ሌላ ተቃውሞ ለማድረግ ጭምር የቦታ መረጣ ሲያደርጉ ነበር ተብሏል።

በአፍሪካ ቀዳሚ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የዱር እንስሳትን አስከፊ በሆነ አያያዝ ወደ ተለያዩ መዳረሻዎች ያጓጉዛል በሚል ክስ ሲቀርብበት ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

ከዚህ ቀደም ዎርልድ አኒማል ፕሮቴክሽን የተሰኘ ድርጅት በተለይ መነሻቸው መካከለኛው እና ምዕራብ አፍሪካ የሆኑ የዱር እንስሳት በአየር መንገዱ ወደተለያዩ መዳረሻዎች ተጓጉዘው ለቤት እንስሳትነት፣ ለንግድ እና ለምርምር እየዋሉ ነው ብሎ ነበር።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከጥቂት ዓመታት በፊት የወጣው ሪፖርቱ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አጥቢ እና ተሳቢ እንስሳት በአስከፊ ሁኔታ በኢትዮጵያ አየር መንገድ መጓጓዛቸውን አስፍሯል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለዚህ ሪፖርት በሰጠው ምላሽ “በሕይወት ያሉ የዱር እንስሳትን የማጓጉዘው በከፍተኛ ጥንቃቄ ዓለም አቀፍ፣ አህጉራዊ፣ ብሔራዊ ሕጎችን እና የውስጥ አሰራርን በተከተለ መንገድ ነው” በማለት የቀረበበትን ክስ አስተባብሎ ነበር።

ጄሰን ቤከር ለገሃር ፖሊስ ጣቢያ ሆነው በላኩት መልዕክት “የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አሜሪካ ቤተ-ሙከራዎች ስለሚልካቸው ጦጣዎች ስቃይ በመናገራችን ለእስር ተዳርገናል” ብለዋል።

“ትክክለኛው ወንጀል በጦጣዎቹ ላይ የደረሰው በደል ነው። መታሰር የሚያስደስት ነገር ባይኖረውም፤ ጦጣዎች በአየር መንገዱ ከሚደርስባቸው ስቃይ ጋር የሚነጻጽር አይለም” ብለዋል።

ጄሰን ቤከር አብሯቸው የታሰረው የ11 ዓመት ልጃቸው አብሯቸው እንደሚገኝ ገልጸዋል ባለፈው ሳምንት በኬንያ የነበራቸውን የሽርሽር ጊዜ አቋርጠው ተቃውሞ ለማሰማት ወደ አዲስ አበባ የመጡት ልጃቸውን ለእንስሳት መብት መቆም እንዳለበት ለማስተማር ጭምር ነው ብለዋል።

“በኬንያ ጦጣዎች መኖር ባለባቸው ተፈጥሯዊ መኖሪያቸው ሲኖሩ ተመልክተናል” ሲሉ ጨምረው ተናግረዋል።

የግለሰቦቹን እስር ተከትሎ የፔታ አሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ኬቲ ጉሌርሞ በበኩላቸው ጦጣዎችን ከቤተሰቦቻቸው በመለየት ወደ አሜሪካ ቤተ-ሙከራዎች ለመላክ የሚስማሙ በመላው ዓለም ካሉ ጥቂት አየር መንገዶች መካከል የኢትዮጵያ አየር መንገድ አንዱ ነው ብለዋል።

“አሳፋሪዎች ናቸው። ፔታ እና በመላው ዓለም ያሉ አገራት ኩባንያው ትክክለኛውን ነገር እንዲያደርግ መጠየቃችንን እንቀጥላለን” ብለዋል።

የሦስቱ ግለሰቦችን ተቃውሞ እና እስርን በተመለከተ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የመንግሥት እና የአዲስ አበባ ፖሊስ እስካሁን ያሉት ነገር የለም።