ኦባማን ጨምሮ ዴሞክራቶች ጫና ያበዙባቸው ባይደን ከምርጫው ሳይወጡ እንደማይቀር ተነገረ

ጆ ባይደን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን

የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማን ጨምሮ ተጽዕኖ ፈጣሪ ዴሞክራቶች በጆ ባይደንት ፕሬዝዳንታዊ ዕጩነት ላይ ጥያቄ እያነሱ መሆናቸው ተገለጸ።

አንድ ከፍተኛ የፓርቲው ኃላፊ ለቢቢሲ ሲናገሩ ባይደን ከዴሞክራቲክ ፓርቲ ፕሬዝዳንታዊ ዕጩነታቸው መውረዳቸው “አይቀሬ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

ዋሽንግተን ፖስት ባይደን ቀጣዩን ምርጫ የማሸነፋቸው ዕድል እጅግ የጠበበ ነው ሲሉ ባራክ ኦባማ አስተያየት ሰጥተዋል ሲል ዘግቧል።

ኦባማ የመጀመሪያው ጥቁር አሜሪካዊ ፕሬዝዳንት ሆነው ሲያገለግሉ ጆ ባይደን ምክትላቸው ሆነው መሥራታቸው ይታወሳል።

ይህ ባራክ ኦባማ ሰጥተውታል የተባለው አስተያየት የተሰማው የቀድሞው የምክር ቤት አፈ ጉባኤ እና ዴሞክራቷ ናንሲ ፔሎሲ ተመሳሳይ አስተያየት ሰጥተዋል መባሉን ተከትሎ ነው።

ሲንኤንኤን ደግሞ ባይደን በምርጫው የሚሳተፉ ከሆነ ምርጫውን እንደማያሸንፉ የሕዝብ አስተያየቶች እንደሚያሳዩ ፔሎሲ ለባይደን መናገራቸውን ዘግቧል።

ከፔሎስ በተጨማሪ ሁለቱ ተጽዕኖ ፈጣሪ ዴሞክራቶች ሐኪም ጄፍሪስ እና ቸክ ሹመር እንዲሁ ባይደን በምርጫው ከገፉ የማሸነፍ ዕድላቸው የጠበበ ስለመሆኑ ስጋታቸውን ለፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል ተብሏል።

በሴኔቱ እና በምክር ቤቱ ከፍተኛ ሥልጣን ያላቸው ሹመር እና ጄፍሪስ ባለፈው ሳምንት ባይደን በምርጫው የሚሳተፉ ከሆነ ፓርቲው መልሶ የማሸነፉ ዕድል አናሳ ነው የሚል “ስጋት” እንዳለ ለባይደን ስለመናገራቸው ተዘግቧል።

ቢቢሲ ዲሞክራቲክ ፓርቲ ጆ ባይደንን ዕጩ አድርጎ ማቅረቡን ወደመተው እየተቃረበ ነው ብሎ ለዋሽንግተን ግዛት የምክር ቤት አባል ለሆኑት አዳም ስሚዝ ጥያቄ አቅርቦ ነበር። ዴሞክራቱ ስሚዝ “ግምቴ እንደዚያ ነው” ሲሉ መልሰዋል።

“በትክክል ይህ ነው ማለት አልችልም። ግን እየሄደ ያለበት አቅጣጫ ወደዚያ ነው ብዬ አስባለሁ” ብለዋል።

ይህ ይሁን እንጂ የጆ ባይደን የቅስቀሳ ቡድን በፕሬዝዳንቱ ዕጩነት ላይ ዴሞክራቶች ስጋት አላቸው የሚለውን ሪፖርት “መሠረተ ቢስ” ሲል አጣጥሎታል።

ፕሬዝዳንት ባይደን እንዲሁ ከምርጫው እራሳቸውን እንደማያገሉ እየገለጹ ይገኛሉ። ፕሬዝዳንቱ ከዕጩነት እራሳቸውን እንዲያገሉ ጫናው በዝቶባቸዋል ቢባልም አሁን ድረስ በአሜሪካ ኮንግረስ ያሉ ፖለቲከኞች ጠንካራ ድጋፍ እንዳላቸው ይታመናል።

የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ኒውስ ከሕዝብ የሰበሰበው አስተያየት ትራምፕ ከዚህ ቀደም ባልታየ ልዩነት የተሻለ ተቀባይነት እንዳላቸው አሳይቷል።

በተቃራኒው ሪፐብሊካኖች ዶናልድ ትራምፕን በይፋ የፓርቲው ፕሬዝዳንታዊ ዕጩ አድርገው አቅርበዋል።

ትራምፕ ከጥቂት ቀናት በፊት የተፈጸመባቸው የግድያ ሙከራ ከ4 ወራት ባነሰ ጊዜ ውስጥ በሚደረገው ምርጫ የተሻ የፖለቲካ ዕድል ይዞላቸው እንደመጣ ተንታኞች እየገለጹ ይገኛሉ።

ትራምፕ ፓርቲያቸው የሰጣቸውን ፕሬዝዳንታዊ ዕጩነት በተቀበሉበት ንግግራቸው ቀጣዩን ምርጫ እንደሚያሸንፉ በራስ መተማመን ተናግረዋል።