ሪፐብሊካኖች ዶናልድ ትራምፕን በይፋ ፕሬዝዳንታዊ ዕጩ አድርገው አቀረቡ

ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሪፐብሊካን ፓርቲ ሕዳር 2017 ዓ.ም. ለሚደረገው የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ዶናልድ ትራምፕን የፓርቲው ዕጩ አድርጎ አቀረበ።

በቀጣዩ ምርጫ ትራምፕ የዴሞክራት ዕጩ ሆነው ሊቀርቡ ከሚችሉት ፕሬዝዳንት ባይደን ጋር ኃያሏን አገር ለመምራት ይፎካከራሉ።

ትራምፕ በዕጩነት መቅረባቸውን በክብር እንደሚቀበሉት ከገለጹ በኋላ ከቤተሰብ አባላቶቻቸው ጋር መድረክ ላይ ወጥተው ለፓርቲ አባላት እና ደጋፊዎች ሰላምታ አቅርበው ንግግር አድርገዋል።

ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ ከተፈጸመባቸው የግድያ ሙከራ በኋላ መድረክ ላይ ወጥተው ባደረጉት የመጀመሪያ ንግግራቸው ከሞት የተረፍኩት “ፈጣሪ ከጎኔ ስለነበር ነው” ብለዋል።

ጠንከር ባለ ንግግራቸው የሚታወቁት የ78 ዓመቱ የቀድሞ ፕሬዝዳንት፤ በፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ዕጩነታቸውን ሲቀበሉ ከወትሮው በተለየ መልኩ ለስለስ ያለ ንግግር አድርገዋል።

ትራምፕ ከቀናት በፊት በፔንሲልቬኒያ የምርጫ ቅስቀሳ ላይ ስለተፈጸመባቸው የግድያ ሙከራ ሲያስታውሱ፤ “በዛች በመጨረሻዋ ቅጽበት ጭንቅላቴን ወደ አንድ ጎን ዞር ባላደርግ ኖሮ፤ ያ ጥይት ዒላማውን ይመታ ነበር። . . . በዚህ ምሽት በዚህ ሁኔታ አልገኝም ነበር። እንደዚህ አንሰባሰብም ነበር” ብለዋል።

ትራምፕ ለ90 ደቂቃዎች በዘላቀው ንግግራቸው ስልጣን ላይ ያለው የአሜሪካ መንግሥትን በአገሪቱ ላለው የዋጋ ግሽበት፣ ለስደተኞች ቁጥር መጨመር እና በዓለም ላይ ላሉ ቀውሶች ተጠያቂ አድርገዋል።

“ሩሲያ ዩክሬንን ወርራ ቀውስ ተፈጥሯል። እስራኤል በታሪኳ የከፋ ጥቃት ተፈጽሞባታል። ቻይና ደግሞ ታይዋን ላይ አያንዣበበች ነው” ብለዋል።

ትራምፕ የአሜሪካ-ሜክሲኮ ድንበርን አቋርጠው አገራቸው የሚገቡ ስደተኞችን “ወራሪዎች” ሲሉ ገልጸዋቸዋል።

ትራምፕ ወደ ዋይት ሃውስ ሲመለሱም በአገሪቱ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መጠን ስደተኞችን ጠርዘው ወደ አገራቸው እንደሚመልሱ ዝተዋል። “ቅድሚያ ለአሜሪካ” የሚሰጥ አዲስ የንግድ ቀረጦችንም አስተዋውቃለሁ ብለዋል።

ትራምፕ ጨምረው እንደተናገሩት በእስራኤል ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው አይረን ዶም የሚሳኤል መቃወሚያ ስርዓት አሜሪካ እንደምትገነባ ተናግረዋል።

“ጦራችንን እናጠናክራለን፤ ጠላት አገራችንን እንዳይመታ አይረን ዶም እንገነባለን። ይህ አይረን ዶም በአሜሪካ የሚገነባ ይሆናል” ብለዋል።

ትራምፕ በመድረኩ ከቤተሰባቸው ጋር ደምቀው ታይተዋል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ትራምፕ በመድረኩ ከቤተሰባቸው ጋር ደምቀው ታይተዋል

የሪፓብሊካኑ ዕጩ የሰሜን ኮሪያውን መሪ ኪም ጆንግ ኡን በተመለከተ ሲናገሩ “ብዙ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ካለው ሰው ጋር መወዳጀት ጥሩ ነው” ካሉ በኋላ “ሳልናፍቀው አይቀርም” ሲሉ ቀልደዋል።

ትራምፕ የኮቪድ-19 ቫይረስን እንደከዚህ ቀደሙ “ቻይና ቫይረስ” ሲሉ ገልጸውታል። ትራምፕ በኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት ቫይረሱን “ቻይና ቫይረስ” ብለው መግለጻቸው ስህተት እና ዘረኝነት ነው ተብሎ በጥብቅ ቢተቹም፤ ዛሬም በንግግራቸው ይህንኑ ደግመውታል።

የቀድሞ ፕሬዝዳንት የተፈጸመባቸው የግድያ ሙከራ ከ4 ወራት ባነሰ ጊዜ ውስጥ በሚደረገው ምርጫ የተሻ የፖለቲካ ዕድል ይዞላቸው እንደመጣ ተንታኞች ይገልጻሉ።

ፕሬዝዳንቱ የፓርቲ ዕጩነታቸውን ሲቀበሉ በባለቤታቸው፣ በልጆቻቸው እና በልጅ ልጆቻቸው መድረክ ላይ ታጅበው ታይተዋል።