ፈረንሳዊው ታዋቂ የካቶሊክ ቄስ ከሞቱ ከ17 ዓመታት በኋላ በወሲባዊ ጥቃት ተከሰሱ

ቄስ ፒዬር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

መጠለያ የሌላቸው ሰዎችን በመደገፍ ስማቸው የሚነሳው ፈረንሳዊው የሮማ ካቶሊክ ቄስ አቤ ፒዬር ከሞቱ ከ17 ዓመታት በኋላ በወሲባዊ ጥቃት ተከሰሱ።

በፈረንሳይ ስማቸው በበጎ ከሚነሱ የሃይማኖት አባቶች መካከል የሆኑት ቄስ ፒዬር በ94 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት በአውሮፓውያኑ 2007 ነበር።

ነገር ግን ከ1970 እስከ 2005 ባለው ጊዜ ሰባት ሴቶች ላይ ወሲባዊ ጥቃት አድርሰዋል መባሉ በርካታ ፈረንሳዊያንን አስደንግጧል።

ዜናው ይፋ የሆነው ቄስ ፒዬር ድህነትን ለመዋጋት በሚል ባቋቋሙት ድርጅት አማካይነት ነው። ድርጅቱ እንዳለው ከሰባቱ ሴቶች የሰማው የምስክርነት ቃል የሚታመን ነው።

“ጉዳዩ መጋለጡ ድርጅታችንን ያስደነገጠ ነው። የቄስ አቤ ፒዬር ስም በድርጅታችን ትልቅ ሥፍራ እንዳለው እሙን ነው” ሲል የተራድዖ ድርጅቱ ድረ-ገፁ ላይ ባሰፈረው መግለጫ አስነብቧል።

“ታሪካቸውን እና መልዕክታቸውን ሁላችንም እናውቃለን። ነገር ግን የሰማናቸው ምስክርነቶች ከዚህ በኋላ ለእሳቸው ያለንን ምሥል የሚቀይሩ ናቸው። ድህነትን፣ ማጣትን እና መገለልን የሚቃወሙ ሰው ነበሩ።”

በሕይወት ሳሉ በበርካቶች ዘንድ ትልቅ ስም የነበራቸው የሃይማኖት አባት ከሞቱ በኋላ የወጣው ዜና ክብራቸውን ዝቅ የሚያደርግ ነው ተብሏል።

ቄሱ በፈረንሳይ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ አገራት ውስጥ ጭምር ስማቸው በመልካም የሚነሳ እና የፈጠሩት ተፅዕኖም በብዙዎች ዘንድ የተሠራጨ ነበር።

ፒዬር በ2007 ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ የወቅቱ የፈረንሳይ ፕሬዝደንት ዣክ ሺራክ፤ ፈረንሳይ “ታላቅ ሰው አጥታለች፤ የመልካምነት መገለጫ የሆኑ ሰው ነበሩ” ማለታቸው ይታወሳል።

የተራድዖ ድርጅቱ እንደገለጸው ቄሱ የተነሳባቸውን ክስ በተለመከተ ምርመራ ማድረግ የጀመረው ከአንድ ዓመት በፊት ሲሆን፣ “መጀመሪያ በፒዬር ወሲባዊ ጥቃት የደረሰባት አንዲት ሴት ናት ጉዳዩን የነገረችን” ብሏል።

ከዚህ ወቀሳ በኋላ ድርጅቱ ገለልተኛ ተቋም ቀጥሮ ጉዳዩን እንደመረመረ ያስረዳል። በምርመራው መሠረትም ስድስት ተጨማሪ ሴቶች በቄሱ ወሲባዊ ጥቃት እንደደረሰባቸው ሲናገሩ፤ አንዷ ደግሞ በወቅቱ ዕድሜዋ ከ18 ዓመት በታች ነበር።

ኢማውስ የተባለው ተቋም እንደለገጸው ሌሎችም ሴቶች ተመሳሳይ ጥቃት ደርሶባቸው ሊሆን ቢችልም ቁጥራቸው ይህን ያህል ነው ብሎ መናገር አዳጋች ነው።

የእርዳታ ድርጅቱ ሴቶቹ ቀርበው ለመናገር ያሳዩትን “ድፍረት” አድንቆ ጉዳዩ አደባባይ እንዲወጣ ትልቅ አስተዋፅዖ አድርገዋል ብሏል።

የፈረንሳይ ጋዜጦች በሐሙስ ዕትማቸው ይህን ዜና በሰፊው ሽፋን የሰጡት ሲሆን፣ ላ ፓሪዚያን የተባለው ጋዜጣ “ከክብር ማማቸው የወረዱ” ሲል ቄሱን ገልጿቸዋል።

ግራ ዘመሙ ጋዜጣ ሊብራሲዮን በበኩሉ ፆታዊ ጥቃትን በተመለከተ ካቶሊክ ቤተ-ክርስቲያን ውስጥ ያለውን “የተዳፈነ ዝምታ” የሚያሳይ ነው ብሎ ሚቱ የተሰኘው ንቅናቄ ከመጀመሩ በፊት በርካታ ድምፆች ተቀብረው መቅረታቸውን አስነብቧል።

ተራድዖ ድርጅቱ ሌሎች በቄሱ ወሲባዊ አሊያም “አስነዋሪ ድርጊት” የተፈፀመባቸው ሴቶች ቀርበው ምስክርነታቸውን እንዲሰጡ ያበረታታ ሲሆን፣ ከለላ እና ድጋፍም እንደሚሰጥ ቃል ገብቷል።