የእስራኤል የደህንነት ሚኒስትር ኤርትራውያን ስደተኞች ከአገር እንዲባረሩ ጠየቁ

ቀኝ ዘመሙ የእስራኤል ሚኒስትር ቤን-ጋቪር

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ቀኝ ዘመሙ የእስራኤል ሚኒስትር ቤን-ጋቪር

ቀኝ ዘመሙ የእስራኤል ብሔራዊ ደኅንነት ሚንስትር በእስራኤል የሚገኙ ኤርትራውያን ስደተኞች ከአገሪቱ እንዲባረሩ ጠየቁ።

ሚኒስትሩ ኢታማር ቤን-ጋቪር ኤርትራውያን ስደተኞች ከእስራኤል እንዲባረሩ የጠየቁት ቅዳሜ ነሐሴ 18/2016 ዓ.ም. በኤርትራውያን መካከል ግጭት ከተፈጠረ በኋላ ነው።

ከትናንት በሰቲያ በእስራኤል መዲና ቴል አቪቭ በኤርትራ መንግሥት ደጋፊዎች እና ተቃዋሚዎች መካከል ግጭት ተከስቶ ሁለት ኤርትራውያን ሲገደሉ ከ8 ያላነሱ ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸው ይታወሳል።

ይህን ተከትሎ የብሔራዊ ደኅንነት ሚንስትሩ የአገሪቱ ዐቃቤ ሕግ እና የአገር ውስጥ ሚኒስቴር ኤርትራውያን ስደተኞች ከአገር እንዲያባርሩ መጠየቃቸውን የእስራኤል መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

ከሚንስትሩ ጽ/ቤት የወጣ መግለጫ፤ ከአንድ ዓመት በፊት የቀረበውን ጥያቄ ተከትሎ የብሔራዊ ደኅንነት ሚኒስቴር እና የእስራኤል ፖሊስ “ኤርትራውያኑን ከአገር መባረር እንዳለባቸው ከመግባባት” ደርሰዋል ይላል።

ኤርትራውያን ስደተኞች ከእስራኤል እንዲባረሩ ሲጠየቅ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም።

ከአንድ ዓመት በፊት በተመሳሳይ ሁኔታ ከኤርትራ የባሕል ፌስቲቫል አከባበር ጋር በተያያዘ ኤርትራውያን ጥገኝነት ጠያቂዎች በቴል አቪቭ ከባድ ሁከት ፈጥረው በኤርትራዊያን፣ በእስራኤል ፖሊስ አባላት እና በንብረት ላይ ከባድ ጉዳት ደርሶ ነበር።

ከዚህ ከባድ አምባጓሮ በኋላ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ አፍሪካውያን ስደተኞች በሙሉ ‘በአስቸኳይ’ ከእስራኤል ለማባረር እቅድ እንዲወጣ ትዕዛዝ ሰጥተው ነበር።

ኔታኒያሁ ከአንድ ዓመት በፊት በቴል አልቪቭ በተፈጠረው ሁከት ውስጥ ተሳታፊ የነበሩ ኤርትራውያን በአስቸኳይ ከአገር እንዲባረሩ እፈልጋለሁ ካሉ በኋላ በአገሪቱ ያሉ አፍሪካውያን ስደተኞችን በሙሉ ከአገር ለማባረር ዕቅድ እንዲወጣ ትዕዛዝ መስጠታቸውን አሶሲዬትድ ፕሬስ ዘግቦ ነበር።

ጠቅላይ ሚንስትሩ “ሕገ-ወጥ ሰርጎ ገብ የሆኑ ሁሉንም ስደተኞች” ከእስራኤል ማስወጣት ስለሚቻልበት ሁኔታ ሚንስትሮቹ ሕጋዊ አማራጮችን እንዲያቀርቡላቸው አሳስበዋል።

ታዲያ ቀኝ ዘመሙ የደኅንነት ሚኒስትር ይህን ከአንድ ዓመት በፊት የተደረሰውን “ስደተኞችን ከአገር የማስወጣት መግባባት” ዋቢ አድርገው የአገሪቱ ዐቃቤ ሕግ እና የአገር ውስጥ ሚኒስቴር መግባባቱን ተፈጻሚ እንዲያደርጉ ጠይቀው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ እንዲሁ በጉዳዩ ላይ ጣልቃ እንዲገቡ አሳስበዋል።

በእስራኤል 20 ሺህ ኤርትራውያን ስደተኞች ይገኛሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በእስራኤል 20 ሺህ ገደማ ኤርትራውያን ስደተኞች ይገኛሉ

ከሚኒስትሩ ጽ/ቤት የወጣው መግለጫ ከአንድ ዓመት በፊት የአገሪቱ ዐቃቤ ሕግ እና የአገር ውስጥ ሚኒስቴር ስደተኞችን ለአገር ለማበረር ፍላጎታቸውን ገልጸው የነበረ ቢሆንም ይህ ተግባራዊ ሳያደረግ ቆይቷል ይላል።

ቀኝ ዘመሙ ሚኒስትር ከጥቂት ሳምንታት በፊት የይገባኛል ጥያቄ በሚነሳበት አል-አቅሳ ቅዱስ ስፍራ በመቶዎች የሚቆጠሩ አይሁዳውያንን ይዘው በመግባት ጸሎት ማድረጋቸው ብዙ አስወቅሷቸው ነበር።

ቤን-ጋቪር አል-አቅሳ መስጅድ በርካቶችን ይዘው ለጸሎት መግባታቸው በፍልስጤማውያን፣ አሜሪካ፣ ፈረንሳይ፣ በተባባሩት መንግሥታት እና በበርካታ የአረብ አገራት አስወቅሷቸው ነበር።

ሚኒስትሩ ግን በቅዱሱ ስፍራ ሆነው “ሐማስ እስኪንበረረከክ ድረስ” የተኩስ አቁም መደረግ እንደሌለበት አጽንኦት ሰጥተው ሲናገሩ ጨምር ተሰምተዋል።

ኤርትራውያን በአገራቸው ያለውን አስገዳጅ ገደብ አልባ ብሔራዊ አገልግሎት እንዲሁም አስተዳደርን በመመሸሽ በከፍተኛ ቁጥር ከአገራቸው ይሰደዳሉ።

በአሁኑ ወቅት ከ20 ሺህ የማያንሱ ኤርትራውያን ስደተኞች በእስራኤል ይኖራሉ።

እስራኤል ከእነዚህ መካከል ለጥቂቱ ብቻ የስደተኛነት እውቅና የሰጠች ሲሆን የተቀሩት ግን የኢኮኖሚ ጥገኛ ናቸው በማለት እነሱን ተቀብሎ የማኖር ሕጋዊ ግዴታ እንደሌላት ታምናለች።

ይሁን እንጂ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች አገር ጥለው የተሰደዱ ኤርትራውያንን ወደ አገራቸው መመለስ ደኅንነታቸውን አደጋ ላይ ይጥላል ይላሉ።

እስራኤል ስደተኞችን ርቀው ወደሚገኙ እስር ቤቶች የምትልክ ሲሆን ሌሎችን ደግሞ አፍሪካ ውስጥ ወዳለ ሦስተኛ አገር እንዲዘዋወሩ ስታደርግ ቆይታለች።