በአውስትራልያ ሠራተኞች ከሥራ ሰዓት ውጪ ከአለቆቻው ቢደወልላቸው ምላሽ ያለመስጠት መብት ተፈቀደላቸው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአውስትራሊያ ሠራተኞች ከሥራ ሰዓት በኋላ ከአለቆቻቸው ለሚላኩላቸው መልዕክቶችን ወይም የስልክ ጥሪዎችን መልስ መስጠት የማይገደዱበትን አዲስ ሕግ አወጣች።
በአዲሱ ህግ መሰረት ሠራተኞች ከመደበኛው የሥራ ሰዓት በኋላ ከአለቆቻቸው የሚላኩ መልዕክቶችን እና የስልክ ጥሪዎችን ቅጣት ይደርስበኛል ብለው ሳይፈሩ ምላሽ ያለመስጠት መብት ሰጥቷቸዋል።
በአውስትራልያ ሠራተኞች በዓመት በአማካኝ 280 ሰዓታት ያለተጨማሪ ክፍያ ከሥራ ሰዓት ውጪ እንደሚሰሩ ባለፈው ዓመት ይፋ የሆነ የዳሰሳ ጥናት አመላክቷል።
ከ20 በላይ አገራት ተመሳሳይ ሕግ ያላቸው ሲሆን አብዛኞቹ በአውሮፓ እና ላቲን አሜሪካ የሚገኙ ናቸው።
ሆኖም አዲሱ የአውስትራሊያ ህግ አለቆች ከሥራ ሰዓት ውጪ ወደ ሰራተኞቻቸው መልዕክት ከመላክ ወይም ከመደወል አያግድም።
በተቃራኒው ሠራተኞች መልዕክቶችን ወይም ጥሪዎችን ያለመመለስ መብት የሰጣቸው ሲሆን አሰሪዎች በቂ ምክንያት ካላቸው ግን ሠራተኞች ምላሽ እንዲሰጡ ይገደዳሉ።
አዲሱ ህግ ቀጣሪዎች እና ሠራተኞች ከሥራ ሰዓት በኋላ ባለ የስልክ ወይም የመልዕክት ልውውጥ ጉዳይ በመካከላቸው ያለውን ችግር በራሳቸው እንዲፈቱ ያበረታታል።
ያ ባይሳካ ግን ጉዳያቸው መንግስታዊ በሆነው የሥራ ኮሚሽን ሊዳኝ እንደሚችል አሰቀምጧል።
ኮሚሽኑ ቀጣሪዎች ከሥራ ሰዓት በኋላ ወደ ሠራተኞች መልዕክት እንዳይልኩ ወይም እንዳይደውሉ ሊያዝ ይችላል።
ሆኖም አሠሪዎች አሳማኝ ምክንያት ካላቸው ይኼው ኮሚሽን ሠራተኞች ምላሽ እንዲሰጡ ሊያዛቸው ይችላል።
መንግሥስታዊው የሥራ ኮሚሽን የሚሰጠውን ትዕዛዝ አለመተግብር ግን ቅጣትን ያስከትላል። በዚህ ህግ መሥራት ሠራተኞች እስከ 19 ሺህ ዶላር ድርጅቶች ደግሞ እስከ 94 ሺህ ዶላር ሊቀጡ ይችላሉ።
የሠራተኛ መብት ድርጅቶች ውሳኔውን አሞግሰዋል።
የአውስትራሊያ ሠራተኞች ማኀበር ምክር ቤት ህጉ ሰራተኞች ከሥራ ሰዓት ውጪ ምክንያታዊ ያልሆነ ግንኙነቶችን በራሳቸው ፍቃድ እንዳይቀበሉ እና ሚዛናዊ የሆነ የሥራ ህይወት እንዲኖራቸው የሚያስችል ነው ሲል አወድሶታል።
ቢቢሲ የነጋገራቸው የሥራ ጉዳዮች ባለሙያ የሆኑት እና በሰዌንብርን የቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የሚሰሩት ጆን ሆፕኪንስ አዲሱ ህግ ሠራተኞች በቂ የእረፍት ጊዜ እንዲኖራቸው በማድረግ በህመም ምክንያት ከስራ እንዳይቀሩ ይግዛል ብለዋል።
“ማንኛውም ሠራተኛውን የሚጠቅም ነገር መልሶ አሠሪውን መጥቀሙ አይቀርም” ሲሉም አክለዋል።












