በኡጋንዳ ሰዎችን ለመስዋዕትነት እንደሚያቀርብ የተጠረጠረ ግለሰብ ከ24 ራስ ቅሎች ጋር ተያዘ

የፎቶው ባለመብት, NoelineNoeline Nabukenya Nabukenya
ማሳሰቢያ፦ ይህ ዘገባ የአንባቢዎችን ስሜት ሊረብሹ የሚችል ፎቶን አካቷል
በዩጋንዳ ራሱን ‘ፈዋሽ’ ነኝ ብሎ የሚጠራ አንድ ግለሰብ ለመስዋዕትነት እንደተጠቀማቸው ከተገመቱ 24 የሰዎች ራስ ቅል ጋር ተይዟል።
ግለሰቡ እድሜ ልኩን በእስር ቤት ሊያሳልፍ እንደሚችል ፖሊስ ለቢቢሲ ገልጿል።
ዲሞልያራ ጎድፍሬ የተባለው ተጠርጣሪ በሀገሪቱ ባለው በሰዎች ህይወት የሚቀርብ መሰዋዕትነትን ለመከልከል እና እና ለመቆጣጠር በወጣው ህግ እንደሚጠየቅ የፖሊስ ቃል አቀባይ ፓትሪክ ኦናይንጎ ለቢቢሲ ተናግሯል።
በካማፓው በተገኘው የተጠርጣሪው መስዋዕት ማቅረቢያ ስፍራ ላይ ከሰዎች የራስ ቅል በተጨማሪ የእንስሳት ቅሪት እና ቆዳ ተገኝቷል።
ፖሊስ የጎድፍሬን የመስዋዕት ማቅረቢያ ስፍራ ላይ ተጨማሪ የሰዎችን ቅሪተ አካል በሚል ፍለጋውን መቀጠሉን ተሰምቷል።
ግለሰቡ በመጀመሪያ በሀገሪቱ ባለው ሰዎችን እና የሰዎችን አካል ለመሰዋዕትነት ማቅረብን የሚከለክለው ህግ በመተላለፍ እንደሚከሰስ እና በዚህም የዕድሜ ልክ እስራት ሊጠብቀው እንደሚችል የፖሊሰ ቃል አቀባይ ለቢቢሲ ተናግሯል።
ጎድፍሬ የባህል ሃኪም እና መድሃኒት ቀማሚ ነኝ ብሎ ራሱን ይጠራል። ነገር ግን የሀገሪቱ የባህል ሃኪሞች ማኅበር ‘ሰውዬውን አናውቀውም’ ብለዋል።
ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ይህ አይነቱ አስደንጋጭ ዜና በኡጋንዳ ሲሰማ ይህ መጀመሪያው አይደለም።
ባለፈው ወር ከካምፓላ 41 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኘው ማዕከላዊ አውራጃ፣ ፖሊስ በአንድ የመስዋዕት ማቅረቢያ ቦታ 17 የሰዎች ራስ ቅሎችን አግኝቷል።
በዚህ አውራጃም ይሁን በካምፓላ በጥቂት ሳምንታት ልዩነት የተገኙት የራስ ቅሎች መስዋዕት ‘አቅራቢዎቹ’ ባላቸው ዕምነት ምክንያት ሰዎችን ለመስዋዕትንት እንደተጠቀሙባቸው ተገምቷል።
በአፍሪካ አንዳንድ ሰዎች፣ ሰዎችን ለማስዋዕትነት በማቅረብ ሀብት ማግኘት እና የሚጠሏቸውን ሰዎች እርግማን ላይ መጣልን ጨምሮ መልካም ዕድል እንደሚያመጣ ወይም ተአምር እንደሚሰራ ያምናሉ።

የፎቶው ባለመብት, Noeline Nabukenya












