ቺምፓንዚዎች እፅዋት እየለዩ በመመገብ ራሳቸውን ከበሽታ እንደሚከላከሉ ጥናት አሳየ

የፎቶው ባለመብት, Elodie Freymann
የዱር ቺምፓንዚዎች እራሳቸውን ለማከም ህመምን የሚያስታግሱ እና ፀረ-ባክቴሪያ ባህሪያት ያላቸውን እፅዋት ለይተው እንደሚመገቡ ሳይንቲስቶች ገለጹ።
ተመራማሪዎቹ በኡጋንዳ ደኖች ውስጥ የምርመራ ሥራቸውን ባከናወኑበት ወቅት የተጎዱ ወይም የታመሙ ቺምፓንዚዎች የተለዩ እጽዋትን በመመገብ እራሳቸው ሲያክሙ ተመልክተዋል።
ተመራማሪዎቹ ጉዳት የደረሰባቸው ወይም የታመሙ ቺምፓንዚዎች ከጫካው ለይተው የተመገቡትን እፀዋት ናሙና በመሰብሰብ ምርመራ አድርገዋል። አብዛኛዎቹ ምርምር የተደረገባቸው ተክሎች ፀረ-ባክቴሪያ ባህሪያት እንዳላቸው ተረጋግጧል።
ግኝታቸውን ፕሎስ በተባለው መጽሔት ላይ ያሳተሙት ሳይንቲስቶች ቺምፓንዚዎች አዳዲስ መድኃኒቶችን በማፈላለግ የሰው ልጆችን ጭምር ሊረዱ ይችላሉ የሚል እምነት አድሮባቸዋል።
የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ዋና ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ኤሎዲ ፍሬይማን “በዚህ ደን ውስጥ ያሉትን ሁሉንም ነገሮች ለመድኃኒትነት ስለመዋላቸው መሞከር አንችልም። ታዲያ ቺምፓንዚዎች የሚፈልጓቸውን እና መረጃ ያገኘንባቸውን ተክሎች ለምን አንፈትሽም?" ሲሉ ጠይቀዋል።
ዶ/ር ፍሬይማን ባለፉት አራት ዓመታት በቡዶንጎ የደን ጥበቃ ማዕከል ያሉትን ሁለት የዱር ቺምፓንዚዎች ማህበረሰቦችን ሲከታተሉ አሳልፈዋል።
የህመም ምልክቶችን የሚያሳዩ (የሚያንክሱ እና ባልተለመደ መንገድ ሰውነታቸውን የሚነኩ) ቺምፓዚዎችን በመፈለግ ከባልደረቦቻቸው ጋር ሽንት እና ሌሎች ናሙናዎች በመውሰድ መታመማቸውን ለማረጋገጥ ሞክረዋል።
በተለይ የተጎዳ ወይም የታመመ ቺምፓንዚ እንደ የዛፍ ቅርፊት ወይም የፍራፍሬ ልጣጭ በተለምዶ የማይመገቡትን ነገር ሲመገቡ በትኩረት ተከታትለዋል።
“በእነዚህን ፍንጮች ተክሎቹ የመድኃኒትነት ባህሪ እንዳላቸው ለመለየት እየሞከርን ነበር” ሲሉ ዶ/ር ፍሬይማን አብራርተዋል።
በተለይም እጁ ላይ ክፉኛ ስለቆሰለ አንድ ቺምፓንዚ አንስተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Elodie Freymann
“እጁን ለመራመድ ከመጠቀም ይልቅ እያነከሰ ነበር የሚንቀሳቀሰው” በማለት ያስታውሳሉ።
"ሌሎቹ ለመብላት ሲቀመጡ የተጎዳው ቺምፓንዚ የሚፍለገውን እጽዋት ፍለጋ እያነከሰ መዞር ጀመረ። እነዚህን ተክሎች ፍልጎ የበላው ብቸኛው ቺምፓንዚ ነበር።"
ተመራማሪዎቹ ተክሉን ሰብስበው መርምረዋል። ይህ ክሪስቴላ ፓራሲቲካ የተባለው ተክል ከፍተኛ ሕመም የማስታገስ ባህሪ ይዞ ተገኝቷል።
ተመራማሪዎቹ ከ13 የተለያዩ የእፅዋት ዝርያዎች 17 ናሙናዎችን በማሰባሰብ የጀርመኑ በኒውብራንደንበርግ አፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ በሆኑት በዶ/ር ፋቢየን ሹልትስ እንዲመረመሩ ልከዋቸዋል።
90 በመቶ የሚሆኑት ንጥረ ነገሮች የባክቴሪያዎችን ዕድገት የሚገቱ ሲሆን አንድ ሶስተኛዎቹ ደግሞ ተፈጥሯዊ ፀረ-ማቃጠል ባህሪ አላቸው። በዚህም እጽዋቱ ህመምን በመቀነስ ወይም በመፈወስ ያግዛሉ ማለት ነው።
በዚህ ጥናት ውስጥ የተካተቱት ሁሉም የተጎዱ እና የታመሙ ቺምፓንዚዎች ሙሉ በሙሉ አገግመዋል ሲሉ ዶ/ር ፍሬይማን ሪፖርት አድርገዋል። “እጁን ታሞ ተክል ሲበላ የነበረው ቺምፓንዚም በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ውስጥ እንደገና እጁን መጠቀም ጀምሮ ነበር” ሲሉ አክለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Austen Deery












