ምባፔ እና የቡድን ጓደኞቹን መነጋገሪያ ያደረገው በፈረንሳይ ምርጫ ላይ የሰጡት አስተያየት

ምባፔ እና የብሔራቡድኑ አባላት ከፕሬዝዳንት ማክሮን ጋር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ምባፔ እና የብሔራቡድኑ አባላት ከፕሬዝዳንት ማክሮን ጋር

ፈረንሳይ በ2024 የአውሮፓ ዋንጫ መክፈቻ ጨዋታዋ ኦስትሪያን አንድ ለምንም አሸንፋለች።

ከጨዋታው በላይ አጥቂው ኪሊያን ምባፔ አፍንጫው ላይ የደረሰበት ጉዳት መነጋገሪያ ለመሆን በቅቷል። ተጫዋቹ ከዚህም በላይ መነጋገሪያ የሆነው ግን ስለቀጣዩ የፈረንሳይ ምርጫ በሰጠው አስተያየቱ ነው።

ከኦስትሪያ ጨዋታ በፊት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ “አክራሪዎች ሥልጣን ለመያዝ ከበር ቆመዋል” አለ። “የእኔንም ሆነ የሌሎችን እሴት የማይወክል አገር መወከል አልፈልግም” ሲል ሃሳቡን አጠናከረ።

የአገሪቱ ቀኝ ዘመም ፓርቲ የሆነው ናሽናል ራሊ (አርኤን) ፈረንሳይን ወክሎ ለአውሮፓ ፓርላማ በተደረገው ምርጫ አሸናፊ ለመሆን በቅቷል። ይህንን ተከትሎም የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ፓርላማውን በትነው አስቸኳይ ምርጫ እንዲካሄድ ውሳኔ አስተላለፉ።

የመጀመሪያው ዙር ሰኔ 23፣ ሁለተኛው ዙር ደግሞ ሰኔ 30/2016 ዓ.ም. እንዲካሄድ ቀነ ቀጠሮ ተይዞለታል።

የምባፔ አስተያየት በፈረንሳይ መነጋገሪያ ሆኗል። ዋናው ደግሞ ስፖርተኞች ምን ያህል በፖለቲካ ውስጥ ይሳተፋሉ የሚለው ነው።

ጉዳዩን በማንሳት በኩል አጥቂው የመጀመሪያው የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች አይደለም። ኡስማን ዴምቤሌ፣ ኦሊቨር ዥሩድ እና ቤንጃሚን ፓቫር የአገሪቱ ዜጎች በሙሉ በምርጫው እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል። ማርከስ ቱራም ግን ከዚህ አለፍ ያለ አስተያየት ሰጥቷል። ፈረንሳውያን አርኤንን እንዳይመርጡ በይፋ ጠይቋል።

“ጉዳዩ በጣም በጣም ከባድ ነው። ይህ አሳዛኙ የማኅበረሰባችን ሕይወት ነው” ብሏል የኢንትር ሚላኑ አጥቂ።

“እንደ ዜጋ እኔም ሆንኩኝ ሌሎች አርኤን እዳይሳካለት በየቀኑ መሥራት አለብን” ብሏል።

ተጫዋቾች የሚሰማቸውን ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ለመግለጽ መብት እንዳላቸው የገለጸው የፈረንሳይ እግር ኳስ ፌደሬሽን፣ እንደተቋም ግን ገለልተኛ መሆኑን አስታውቋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ምባፔ የፖለቲካ ፓርቲን በስም ከመጥቀስ ተቆጥቧል። የቱራምን ሃሳብ እንደሚጋራ ግን ገልጿል።

“ከማርከስ ጋር ተመሳሳይ ሃሳብ እጋራለሁ። ስለመቻቻል፣ ብዝሃነት እና መከባበር እሴት ነው የማወራው። ስለዚህ ከእሱ ጎን ነኝ” ሲል ለጋዜጠኞች ሐሳቡን አካፍሏል።

ቱራም በፖለቲካ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ ሲገባ የመጀመሪያው እግር ኳስ ተጫዋች አይደለም። የሚጠበቅም ነገር ነው። የማርከስ ቱራም አባት ዕውቁ የቀድሞ የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን ቀኝ ተከላካይ ሊሊያን ቱራም ነው።

ሊሊያን ፀረ-ዘረኝነት አቀንቃኝ በመሆን ይታወቃል። ለልጁም ስም ያወጣው ለጃማይካዊው የሰብዓዊ መብት ታጋይ ማርከስ ጋርቬይ ማስታወሻነት ነው። ሊሊያንም መድልዎን በመቃወም ድምጹን በማሰማት ይታወቃል።

የምባፔ አስተያየቶች የተለመዱ አይደሉም። የትውልድ ስፍራው የሆነችውን ቦንዲን በከንቲባነት ሲመሩ ከነበሩት ሶሻሊስቷ ሲልቪን ቶማስሲን እና እናቱ ፋይዛ ላማሪ ጋር የቅርብ ጓደኛሞች ነበሩ። ይህም ሆኖ ከዚህ ቀደም ስለፖለቲካ ዝንባሌው ምንም ፍንጭ አልሰጠም።

የአውሮፓ ዋንጫ ከመጀመሩ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ለሪያል ማድሪድ የፈረመው የ25 ዓመቱ ኮከብ፣ በአገሪቱ ባለው ተወዳጅነት እና ተግባቦት በፈረንሳይ ፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ ተፈላጊ ሰው ነው።

ምባፔ ገና የ19 ዓመቱ ወጣት እያለ ፕሬዝዳንት ማክሮን በየካቲት 2018 በኤሊሴ ቤተ መንግሥት የዲፕሎማሲያዊ ምሳ ላይ እንዲገኝ ጋብዘውታል።

በ2022 ከፒኤስጂ ለቅቆ ወደ ሪያል ማድሪድ ለማቅናት በሚያስብበት ወቅት በፈረንሳይ እንዲቆይ በማሳመን የበኩላቸውን ተወጥተዋል።

ማድሪድ ተጫዋቾቹ በፓሪስ ኦሊምፒክ እንዳይሳተፉ ያገደበትን ውሳኔ እንዲያነሳ ማክሮን ጫና ፈጥረው ለምባፔ ሌላ ዕድል ፈጥረዋል።

ተጫዋቹ በቅርቡም ለኳታሩ ኢሚር ሼክ ታሚም በቤተ መንግሥት በተሰነዳ የእራት ግብዣ ላይ ተጋብዞ ተገኝቷል።

ኳታር ባለሃብት እአአ ከ2011 ጀምሮ ፒኤስጂ በባለቤትነት ያስተዳደራል። አገሪቱ መገናኛ ብዙላን የሆነው ቢኢን ስፖርት ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ የፈረንሳይ ሊግን እንዲያስተላለፍ አገሪቱን እያበረታቱ ነው።

ምባፔ በምርጫው ዙሪያ የሰጠው አስተያየት ከአርኤን ትችት እንዲቀርብብት አድርጓል። “ከእውኑ ዓለም የተራራቁ ሰዎች የፈረንሳይ ሕዝብን እናስተምር ማለታቸውን አልጥብቅም” ሲሉ የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንት ሰባስቲን ፔኑ ገልጸዋል።

ማርከስ ቱራም

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታሪክን ካገላበጥን የፈረንሳይ እግር ኳስ ተጫዋቾች ስለ ፖለቲካ ሲናገሩ እምብዛም አይደመጥም። ከምባፔ በፊት የፈረንሳይ እግር ኳስ ምልክት ተደርጎ ይቆጠር የነበረው ዚነዲን ዚዳን በ2002 በተመሳሳይ መልኩ በምርጫ ውስጥ ጣልቃ ገብቷል።

ዚዳን ሕዝቡ የማሪን አባት የሆኑትን እና አርኤንን የመሠረቱትን ዢን-ማሪ ለ ፔንን እንዳይመርጡ ጠይቆ ነበር።

ምባፔ ትኩረት ያደረገባቸው ወጣቶች በመጪው ምርጫ ቁልፍ ሚና ይኖራቸዋል። የ28 ዓመቱ የፓርቲው ፕሬዝዳንት ጆርዳን ባርዴላ ቀንደኛ የቲክ ቶክ ተጠቃሚ ናቸው።

በቅርቡ በተካሄደው የአውሮፓ ምርጫ ፀረ ስደተኛ ፓርቲያቸው ከ18 እስከ 24 ዓመት ካሉ ወጣቶች የ25 በመቶዎቹን ድምጽ እንዲያገኙ ረድቷቸዋል።

ለመሆኑ የምባፔ እና የቱራም ጣልቃ ገብነት የፖለቲካ ምህዳሩን ሊቀይረው ይችላልን?

“በዚህ ዙሪያ የተደረገው ውይይት ምርጫው ላይ ተጽዕኖ ሊፈጥር ይችላል። ምክንያቱም ድምጽ ለመስጠት ያላሰቡ ወይም ምርጫ መኖሩን እንኳን የማያውቁ ወጣት መራጮችን ሊቀሰቅስ ይችላል” ሲሉ በለንደን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የፈረንሳይ እና የአውሮፓ ፖለቲካ ፕሮፌሰር የሆኑት ፊሊፕ ማርሊየር ተናግረዋል።

“በፈረንሣይ ውስጥ ያሉ ወጣቶች በተለይም የከተማ እና ከአናሳ ማኅበረሰብ የመጡት በምርጫ የመሳተፍ ዕድላቸው አነስተኛ ነው። ምባፔ እና ቱራም ከከተማ የመጡ ሲሆኑ፣ ሁለቱም ከአናሳ ማኅበረሰብ የተገኙ ናቸው።

“የእነርሱ ማስጠንቀቂያ ማሪን ለፔን የሚደግፉትን ነጮች፣ የሠራተኛ መደብ አባላት እና ሥራ አጥ ላይ ተጽዕኖ ላያሳድር ይችላል። ለመምረጥ ያላሰቡ የከተማ ወጣቶች ድምጽ ለመስጠት እንዲያስቡ ይህ የማንቂያ ደወል ሊሆን ይችላል” ብለዋል።