ቻይና ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ እንድታልፍ ‘ረድቷል’ የተባለው የሴንጋፖር በረኛ የገንዘብ ስጦታ እየጎረፈለት ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሴንጋፖር ብሔራዊ ቡድን ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ከታይላንድ ጋር በነበረው ጨዋታ ሦስት ለአንድ ቢሸነፍም የቡድኑ በረኛ ከቻይና ደጋፊዎች በኩል የገንዘብ ስጦታ እና የምስጋና መልዕክት እየደረሰው መሆኑን ተናገረ።
የሴንጋፖሩ ግብ ጠባቂ ሐሳን ሰኒ ስጦታው እየደረሰው ያለው በጨዋታው ወቅት ግብ ሊሆኑ የሚችሉ 11 ኳሶችን ማደን በመቻሉ ቻይና በእስያ ምድብ ከሚካሄደው የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ውድድር እንዳትወጣ በማድረጉ ነው።
ቻይና፣ ሴንጋፖር፣ ታይላንድ እና ደቡብ ኮሪያ በተደለደሉበት ምድብ ውስጥ ሲካሄድ በነበረው ጨዋታ ባለፈው ማክሰኞ በደቡብ ኮሪያ አንድ ለዜሮ የተሸነፈችው ቻይና ለ2026 የዓለም ዋንጫ በሚደረገው ማጣሪያ ውስጥ የመቆየት እድሏ ተመናምኖ ነበር።
ከምድቡ የሁለተኛ ደረጃን ይዞ ወደ ቀጣይ ማጣሪያ ለማለፍ ትንቅንቅ ላይ የነበሩት ቻይና እና ታይላንድ የነበሩ ሲሆን፣ ከቻይና ሽንፈት በኋላ ታይላንድ መውደቋ የለየላትን ሴንጋፖርን በሦስት ግብ ልዩነት ካሸነፈች የማለፍ ዕድል ነበራት።
ነገር ግን ታይላንድ ሴንጋፖርን 3 ለ 1 ማሸነፍ ብትችልም ሦስት ንጹህ ግቦችን ባለማስቆጠሯ ቻይና ከውድድሩ ውጪ ከመሆን ተርፋ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ወደ ቀጣይ ዙር ማለፍ ችላለች።
ለዚህ ደግሞ የሴንጋፖር በረኛ ሐሳን በርካታ ግብ የሚሆኑ ኳሶችን በማዳን ቻይና በፉክክሩ ውስጥ እንድትቆይ አድርጓል ከሚሉ የቻይና እግር ኳስ ቡድን ደጋፊዎች የገንዘብ ስጦታ እየጎረፈለት ነው።
የሱቅ ባለቤት የሆነው የ40 ዓመቱ ጎልማሳ ግብ ጠባቂ ሐሳን ሰኒ ለሴንጋፖር መንግሥት ቴሌቪዥን እንደተናገረው የሱቁ የኤሌክትሮኒክስ ክፍያ መፈጸሚያ ኪውአር ኮድ በኢንተርኔት አማካይነት ከተሰራጨ በኋላ ከማያውቃቸው ሰዎች የገንዘብ ስጦታ እየደረሰው መሆኑን ገልጿል።
ግብ ጠባቂው በቡድኑ ላይ በርካታ ግቦች እንዳይቆጠሩ ያደረገውን ጥረት እንደውለታ የቆጠሩ የቻይና ብሔራዊ ቡድን ደጋፊዎች ኪውአር ኮዱን በመጠቀም ገንዘብ እየላኩለት ነው።
ሐሳን ለተወሰነ ጊዜ የገንዘብ ስጦታው ሲላክለት ደስ እንዳለው ገልጾ፣ ነገር ግን የሚላከው ገንዘብ በመቀጠሉ ጥያቄ እንደተፈጠረበት ተናግሯል።
“ይህ የሚላከው የገንዘብ ስጦታ የሚቆመው መቼ ነው? ይህስ ሕጋዊ ነው? የሚል ጥያቄ ተፈጥሮብኛል።” ብሏል።
ነገር ግን ሐሳን እስካሁን ምን ያህል ገንዘብ በስጦታ መልክ እንደተላከለት ያልተናገረ ሲሆን “የሚላከው ገንዘብ አንድ ቦታ ላይ መቆም አለበት” ብሏል።
“በዚህ ሁኔታ እና በሚደርሱኝ መልዕክቶች የተነሳ ቤተሰቦቼ በተወሰነ ደረጃ ግራ ተጋብተዋል” ሲል እየደረሰው ያለው አድናቆት ከፍተኛ መሆኑን ሐሳን ገልጿል።
በተጨማሪም ሐሳን በርካታ ግቦችን ካዳነበት ጨዋታ በኋላ በምሥራቃዊ የሴንጋፖር ዳርቻ ላይ ወዳለችው ሱቁ በርካታ የቻይና ብሔራዊ ቡድን ደጋፊዎች እየመጡ እቃዎችን እየሸመቱ ነው።
ባለፈው ሐሙስም ብዙ ሰዎች ከሱቁ የምግብ ሸቀጦችን በመግዛታቸው የተነሳ ክምችቱ አልቆበት እንደነበር ከአካባቢው የወጡ ሪፖርቶች አመልክተዋል።












