የአውሮፓ ዋንጫ የጨዋታ መረሃ ግብር፣ ስታዲየሞች እና ለዋንጫው የሚጠበቁ አገራት

Euro2024

በጀርመን አስተናጋጅነት የሚካሄደው በጉጉት የሚጠበቀው የ2024 የአውሮፓ ዋንጫ ከአንድ ሳምንት በኋላ ይጀምራል።

ውድድሩ በሚቀጥለው ሳምንት አርብ ሰኔ 7/2016 ዓ.ም. በይፋ ይጀመራል።

በመክፈቻው ጨዋታ ስኮትላንድ ከአዘጋጇ ጀርመን ጋር በባየር ሚዩኒክ ስታዲየም አሊያንዝ አሬና የመክፈቻውን ጨዋታ ያደርጋሉ።

በስድስት ምድቦች የተከፋፈሉት ቡድኖች በየምድባቸው በየዕለቱ ከሁለት እስከ አራት ጨዋታዎችን ያደርጋሉ።

የጨዋታ መረሃ ግብር

የዩሮ 2024 የእግር ኳስ ውድድር ሙሉ መርሃ ግብርን በፒዲኤፍ (PDF) አማራጭ ለማውረድ ይህን ይጫኑ 👉: የአውሮፓ ዋንጫ መርሃ ግብር

የአሸናፊነት ግምት ለማን ተሰጠ?

በዚህ ውድድር በአውሮፓ የእግር ኳስ መድረክ ትልቅ ስም ያላቸው እንደ ጀርመን፣ ስፔን፣ ጣሊያን፣ እንግሊዝ፣ ፈንሳይ፣ ኔዘርላንድስ፣ ቤልጂየም፣ ፖርቱጋል ተፋላሚዎች ናቸው።

ከእነዚህ አገራት መካከል ሦስቱ ቀዳሚ የአሸናፊነት ግምት የተሰጣቸው ሲሆኑ፣ እነሱም አስተናጋጇ ጀርመን፣ እንግሊዝ እና ፈረንሳይ ለዋንጫው ከፍተኛውን ግምት አግኝተዋል።

ለዘንድሮውን የአውሮፓ ዋንጫ ዝቅተኛ ግምት የተሰጣቸው ደግሞ ጂዮርጂያ፣ አልባኒያ፣ ስሎቬኒያ እና ስሎቫኪያ ናቸው።

የምድብ ድልድል

ምድብ ኤ፡ ጀርመን፣ ስኮትላንድ፣ ሃንጋሪ፣ ስዊትዘርላንድ

ምድብ ቢ: ስፔን፣ ክሮሺያ፣ ጣልያን፣ አልባኒያ

ምድብ ሲ፡ ስሎቬኒያ፣ ዴንማርክ፣ ሰርቢያ፣ እንግሊዝ

ምድብ ዲ፡ ፖላንድ፣ ኔዘርላንድስ፣ ኦስትሪያ፣ ፈረንሳይ

ምድብ ኢ፡ ቤልጂየም፣ ስሎቫኪያ፣ ሮማኒያ፣ ዩክሬን

ምድብ ኤፍ፡ ቱርክ፣ ጆርጂያ፣ ፖርቱጋል፣ ቼክ ሪፓብሊክ

ፈረንሳይ፣ እንግሊዝ፣ ፖርቱጋል፣ ቤልጂየም፣ ሮማኒያ እና ሃንጋሪ ለውድድሩ ለማለፍ በተደረጉ የማጣሪያ ጨዋታዎች አንዳችም ሽንፈት ሳይገጥማቸው ነው ለፍጻሜው ውድድር የደረሱት።

ሁሉንም የማጣሪያ ጨዋታዎች ያሸነፈችው ብቸኛዋ አገር ፖርቱጋል ነች። የክርስቲያኖ ሮናልዶ ቡድን በማጣሪያ ጨዋታዎች 36 ጎሎች አስቆጥሮ የገባበት ጎል 2 ብቻ ነው።

ስፔን፣ ስኮትላንድ፣ ቱርክ እና ኦስትሪያ በማጣሪያው አንድ ጨዋታ ብቻ ነው የተሸነፉት።

ጨዋታዎችን የሚያስተናግዱ ከተሞች

አስር የጀርመን ከተሞች ዝግጅታቸውን አጠናቀው ቡድኖችን እና ደጋፊዎችን ለማስተናገድ በመጠባበቅ ላይ ናቸው።

የመክፈቻውን ጨዋታ አሊያንስ አሬና ሲያስተናግድ የፍጻሜ ጨዋታው ደግሞ በርሊን በሚገኘው ኦሊምፒያ ስታዲዮን ይደረጋል።

የአስተናጋጅ ከተሞች እና የስታዲየሞች ዝርዝር መያዝ ከሚችሉት የተመልካች አቅም ጋር እንደሚለተለው ቀርቧል፡

  • በርሊን፡ ኦሊምፒአስታዲዮን (70ሺህ ተመልካች)
  • ኮሎኝ፡ ኮሎኝ ስታዲየም (47ሺህ)
  • ዶርትሙንድ፡ ቢቪቢ ስታዲዮን ዶርትሙንድ (66ሺህ)
  • ዱሰልዶርፍ፡ ዱሰልዶርፍ አሬና (47ሺህ)
  • ፍራንክፈርት፡ ፍራንክፈርት አሬና (48ሺህ)
  • ጌልሰንክረቸን፡ አሬና ኡፍሸለክ (50ሺህ)
  • ሃምቡርግ፡ ቮልክስፓራክስታዲየን ሃምቡርግ (50ሺህ)
  • ላይፕዚግ፡ ላይፕዚግ ስታዲየም (42 ሺህ)
  • ሚዩኒክ፡ ሚዩኒክ ፉትቦል አሬና (67ሺህ)
  • ስቱትጋርት፡ ስቱትጋርት አሬና፡ (54 ሺህ)

በውድድሩ የማንመለከታቸው ኮከቦች

በዚህ ውድድር የአውሮፓ አገራት ኮከብ እግር ኳስ ተጫዋቾች የሚታዩበት መድረክ እንደመሆኑ ሁለት እውቅ ተጫዋቾች በዩሮ 2024 ተሳታፊ አይሆኑም።

የማንችስተር ሲቲው አጥቂ ኧርሊንግ ሃላንድ እና የአርሰናሉ አማካይ ማርቲን ኦዴጋርድ አገራቸው ኖርዌይ ማጣሪያውን ማለፍ ባለመቻሏ በጀርመኑ የአውሮፓ ዋንጫ ጨዋታ ላይ አንመለከታቸውም።

ከእአአ 1996 ጀምሮ የውድድሩ ተሳታፊ ሆና የቆየችው ስዊዲን እንዲሁ ማጣሪያውን ማለፍ ባለመቻሏ ዘንድሮ አሌክሳንደር አይዛክን በመያዝ በጨዋታው ላይ አትሳተፍም።