የዓለም ጤና ድርጅት ቻይና በኮቪድ የሚሞቱትን ሰዎች ቁጥር ማሳነሷ አሳስቦኛል አለ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ቻይና የኮቪድ ሟቾችን ቁጥር እያሳነሰች መሆኑ አሳስቦኛል ብሏል የዓለም ጤና ድርጅት።
ከሳምንታት በፊት ቻይና የእንቅስቃሴ ገደቦችን ማንሳቷን ተከትሎ ኮቪድ ወረርሽኝ እንደ አዲስ ተቀስቅሶ በርካቶችን ለሞት እየዳረገ ነው።
ይሁንና ቻይና ትክክለኛ የሞት ቁጥርን ትደብቃለች የሚል ክስ ይቀርብባታል።
ቻይና ዕለታዊ የሟቾችን ቁጥር ይፋ ማድረግ ማቆም ብቻ ሳይሆን ከታኅሣሥ ወዲህ 22 ሰዎች ብቻ ናቸው የሞቱብኝ የሚል ተአማኒነት የጎደለው አሐዝ ይፋ አድርጋለች።
የዓለም ጤና ድርጅት የአስቸኳይ አደጋዎች ዳይሬክተር ዶ/ር ማይክል ራየን የቻይናን ድርጊት ኮንነዋል።
"ቻይና የኮቪድ ሞት ብላ ለክስተቱ የሰጠችው ብያኔ ጠባብ ነው" ሲሉም ተችተዋል።
ቻይና ኮቪድ ተህዋሲ በሚያመጣው የጤና ቀውስ የሚሞቱ ዜጎችን በተህዋሲው የሞቱ ብላ አትቆጥራቸውም።
ዶ/ር ራየን የቻይና አሐዝ በትክክል በአገሪቱ እየተስተዋለ ያለውን ሐቅ አይወክልም ሲሉ ቅሬታቸውን አቅርበዋል።
በቻይና ሆስፒታሎች በታማሚች ተጨናንቀዋል፣ የጽኑ ሕሙማን ክፍሎችም ከፍተኛ ጫና ውስጥ ናቸው።
ቻይና ከባለፈው ወር ወዲህ ለሐኪሞቿ ባስተላለፈችው ቀጭን ትእዛዝ አንድ ሰው በኮቪድ ሞተ የሚባለው በቀጥታ በኮቪድ የመተንፈሻ አካል ጉዳት አደጋ ሲደርስበት ብቻ ነው ብላለች።
ነገር ግን ኮቪድ ተህዋሲ በባሕሪው ለተወሳሰበ የጤና እክል የሚዳርግ ሲሆን ሌሎች ተያያዥ የጤና እክል ያለባቸውና በዕድሜ የገፉ ሰዎችን ለሞት ይዳርጋል።
የዓለም ጤና ድርጅት መመሪያ አገራት የኮቪድ ሞትን ሲቆጥሩ ቀድሞ የሞት ቁጥርን እያነጻጸሩ ኮቪድ ተህዋሲ ያመጣውን ውስብስብ የጤና እክል ተከትሎ የሚሞቱ ዜጎችን እንዲመዘግቡ ያዛል።
ቻይና ግን ለዚህ ደንብ እየተገዛች አይደለም የሚል ቅሬታ ቀርቦባታል።
ቻይና በኮቪድ የሚሞቱብኝ ሰዎች ጥቂት ናቸው ብትልም ኤየርፊኒቲ የሚባለው የዩኬ የሳይንስ ጥናት ኩባንያ ግን በአሁኑ ሰዓት በቻይና 2 ሚሊዮን ሰው በኮቪድ መያዙን ይገምታል።
በየቀኑ ደግሞ በትንሹ 14ሺህ ሰዎች ይሞታሉ ይላል።
ቻይና ‘አንዳችም የኮቪድ ተህዋሲ በቻይና ምድር አልታገስም’ የሚለውን መመሪያዋን ካላላች ከዛሬ ወር በፊት ሆስፒታሎችና የቀብር ቦታዎች ተጨናንቀዋል።
ይህን ከፍተኛ የወረርሽኙን መዛመት ተከትሎ አገራት ከቻይና የሚመጣ ተጓዥ ከተህዋሲው ነጻ መሆኑን ማረጋገጫ ካልያዘ አናስገባም የሚል መመሪያን አውጥተዋል።
ከነዚህ በቻይና ላይ ጥብቅ አቋም ከወሰዱ አገሮች መሀል አሜሪካና ካናዳ ይገኙበታል።
ቻይና በበኩሏ እርምጃው ፖለቲካዊ ነው እበቀላችኋለው ብላለች።
በቻይና አዲስ የተህዋሲው ዝርያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መከሰቱን የዓለም ጤና ድርጅት ይፋ አድርጓል።
በዓለም ጤና ድርጅት የስጋት መከላከልና ማስጠንቀቂያ ዳይሬክተር ደ/ር አብዲ ራህማን ማህሙድ በቻይና የከፋው ወረርሽኝ ምናልባት በቻይና አዲሱ ዓመት ክብረ በዓልን ተከትሎ ከዚህም የከፋ ሊሆን ይችላል ብለዋል።
በቻይናዎቹ አዲስ ዓመት በሚሊዯን የሚቆጠሩ ሰዎች ከቦታ ቦታ ይዘዋወራሉ።












