ታይላንድ በደል ደርሶበታል ያለችውን ዝሆን ግማሽ ሚሊዮን ዶላር ወጪ በማድረግ ወደ አገር መለሰች

ዝሆን

የፎቶው ባለመብት, EPA

ታይላንድ እአአ 2001 ለስሪ ላንካ በስጦታ መልክ የሰጠችው ዝሆን በደል ደርሶበታል በማለት በከፍተኛ ወጪ ወደ አገር መለሰች።

ብዝበዛ ተፈጽሞበታል የተባለው የዚህ ዝሆን ጉዳይ በታይላንድ እና ስሪ ላንካ መካከል ዲፕሎማሲያዊ አለመግባባቶችን እስከ መፈጥረት ደርሷል።

ታይላንድ 540ሺህ ዶላር ወጪ አድርጋ ዝሆኑን በአየር በልዩ ሁኔታ አጓጉዛ ትናንት እሁድ ወደ ታይላንድ መልሳለች።

ባንግኮክ የ29 ዓመቱ ዝሆን በአንድ የስሪ ላንካ የቡድሃ ቤተ-መቅደስ ውስጥ ብዝበዛ ተፈጽሞበታል መባሉን ተከትሎ ግዙፉ እንስሳት ወደ ትውልድ አገሩ እንዲመለስ ስትጠይቅ ቆይታለች።

በዝሆኑ ጉዳያ የስሪ ላንካው ጠቅላይ ሚንስትር ለታይላንድ ንጉሥ ይፋዊ ይቅርታቸውን አቅርበዋል።

4ሺህ ኪሎ ግራም የሚመዝነው ዝሆን ለእርሱ ተብሎ በተሰራው ማጓጓዣ ውስጥ ተደርጎ እና በታይላንድ የእንስሳት ተንከባካቢዎች ታጅቦ ቺያንግ ማይ ወደተባለች ከተማ ተወስዷል።

ዝሆኑ አራት እግሮቹ ላይ ላጋጠመው ጉዳት የሃይድሮቴራፒ ሕክምና ይደረግለታል።

ሁለቱም አገራት ዝሆኖችን እንደ ቅዱስ እንስሳት ነው የሚመለከቱት። እአአ 2001 ላይ የታይላንድ ንጉሥውያን ቤተሰብ አባላት ሙቱ ራጃ የተባለውን ይህን ዝሆን ጨምሮ 3 ግዙፍ እንስሳቱን ለስሪ ላንካ መንግሥት በስጦት ሰጥተው ነበር።

ሙቱ ራጃ ስሪ ላንካ ከደረሰ በኋላ በደቡባዊ የአገሪቱ ክፍል ወደሚገኘ ቤተ-መቅደስ እንዲያገለግል ተልኮ ነበር።

የእንስሳት መብት ተቆርቋሪ ቡድኖች ዝሆኑ የቤተ-መቅደስ ሠራተኞቹን እንዲያጓጉዝ መደረጉን እና ለረዥም ግዜ የቆየው የእግር ሕመሙ ትኩረት እንዳልተሰጠው ሲገልጹ ቆይተዋል።

መቀመጫውን ስሪ ላንካ ያደረገው ራሊ ፎር አኒማል ራይትስ ኤንደ ኢንቫሮመንት መሠራች የሆኑት ፓንቻሊ ፓናፒቲያ ዝሆኑን በተመለከት ለስሪ ላንካ መንግሥት ያቀረቡት ጥያቄ ምላሽ ሳያገኝ በመቅረቱ የታይላንድ መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ መጠየቃቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ፓናፒቲያ የስሪ ላንካ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣናት እርምጃ ሳይወስዱ መቅረታቸው የአገሪቱን ‘ስም አጉድፏል’ ብለዋል።

ይህ የእስሳት መብት ተሟጋች ለዝሆኑ መስቃየት ተጠያቂ የሆኑ ግለሰቦች በሕግ እንዲጠየቁ ጭምር ጠይቋል።

የሰሪ ላንካ የዱር እንስሳት ሚንስትር ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ሲናገሩ የታይላንድ አምባሳደር ከአንድ ዓመት በፊት ዝሆኑ ያለበትን ሁኔታ ከታዘቡ በኋላ ዝሆኑ ወደ ትውልድ አገሩ እንዲመለስ ታይላንድ አጥብቃ ስትጠይቅ ነበር ብለዋል።

የስሪ ላንካ ጠቅላይ ሚንስትር ዲኔሽ ጉናዋርደን ከጥቂት ሳምንታት በፊት በዝሆኑ ላይ ለደረሰው ጉዳት የታይላንድ ንጉሥን ይቅርታ መጠየቃቸውን እና በዝሆኑ ምክንያት የተበላሸው መተማመን መመለሳቸውን ለአገሪቱ ፓርላማ ተናግረው ነበር።