እስራኤል በጄኒን የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ላይ ጥቃት ከፈተች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የእስራኤል ጦር በሰሜን ዌስት ባንክ በሚገኘው ጄኒን መጠለያ ጣቢያ ላይ ከፍተኛ የሆነ ወታደራዊ ዘመቻ ጀመረ።
ወታደራዊ ዘመቻው በበርካታ የአየር ጥቃቶች ጀምሯል። ማሕበራዊ ሚዲያ ላይ የተጋሩ ምስሎች ከመኖሪያ መንደሮች አቅራቢያ ጭስ ሲወጣ አሳይተዋል።
የፍልስጤም ጤና ሚንስቴር በጥቃቱ እስካሁን ቢያንስ ሦስት ፍልስጤማውያን መገደላቸውን እና 12 የሚሆኑ ደግሞ መቁሰላቸውን አስታውቋል።
የእስራኤል መከላከያ ኃይል ወታደራዊ ዘመቻውን የከፈትኩት “ጄኒን አካባቢ በሚገኝ የአሸባሪዎች መሠረተ ልማት ላይ ነው” ብሏል።
“አሸባሪዎች የጄኒን መጠለያ ጣቢያን እንደ መደበቂያ ተጥቅመው ዜጎቻችንን ሲጎዱ ዝም ብለን ተቀምጠን አናይም” ብሏል የእስራኤል ጦር።
ጦሩ በጄኒን ከተማ የሚገኘው የፍልስጤማውያን የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ “ጠንካራ የአሸባሪዎች መገኛ ነው” ብሏል።
የፋታህ፣ ሃማሳ እና እስላሚክ ጂሃድ ፍልስጤማውያን ስብስብ የሆነው ‘ጄኒን ባታሊየን’ በበኩሉ “እስከመጨረሻ ጥይት እና እስትንፋሳችን ድረስ ወራሪውን ኃይል መታገላችንን እንቀጥላለን” ሲል ለእስራኤል ወታደራዊ ዘመቻ መልስ ሰጥቷል።
በርካታ ፊታቸው በጭምብል የተሸፈኑ እና የታጠቁ ፍልስጤማውያን በመጠለያ ጣቢያው ዙሪያ መሰማራተው ተገልጿል።
የመጠለያ ጣቢያው ነዋሪ የሆነው አህመድ ዛኪ የእስራኤል ወታደራዊ ተሸከርካሪዎች በበርካታ አቅጣጫዎች ወደ መጠለያ ጣቢያው ዙሪያ ሰርገው መግባታቸውን ለቢቢሲ ተናግሯል።
ፍልስጤማዊው የአምቡላንስ አሸከርካሪ ካህሊድ አላማድ ደግሞ፤ “በስደተኞች መጠለያ ጣቢያው እየተካሄደ ያለው ጦርነት ነው” ብሏል።
“መጠለያ ጣቢያውን ዒላማ ያደረጉ የአየር ጥቃቶች አሉ። ከአምስት እስከ ሰባት አምቡላንሶች ሆነን ሄደን በርካታ ቁሰለኞችን ይዘን እንመለሳለን” በማለት ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግሯል።

የፎቶው ባለመብት, EPA
ጄኒን መጠለያ ጣቢያ ከእአአ 1950ዎቹ ጀመሮ በ1989-49 በተካሄደው የአረብ-እስራኤል ጦርነት ምክንያት የተፈናቀሉ ፍልስጤማውያንን ሲያስጠልል ቆይቷል።
የተባበሩት መንግሥታት ጄኒን በግምት 14ሺህ ሰዎችን አስጠልሎ ይዟል ይላል።
ባለፈው ወር የእስራኤል ጦር በጄኒን የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ላይ ድንገተኛ ወረራ ፈጽሞ ቢያንስ ስድስት ፍልስጤማውያንን ገድሏል።
በዛ ወታደራዊ ዘመቻ ሰባተ የእስራኤል ፖሊስ አባላት እና ድንበር ጠባቂ መኮንኖች ጉዳት ደርሶባቸው ነበር።












