የፈረንሳዊው ታዳጊ ቤተሰብ፡ “ፖሊስ ከመጠን በላይ ኃይል መጠቀም ሊያቆም ይገባል”

ፈረንሳይ ውስጥ በፖሊስ የተገደለው ናሄል ኤም

የፎቶው ባለመብት, SUPPLIED

የፈረንሳይ ፖሊስ በጥይት የገደለው ልጅ ቤተሰቦች አመፅ ተነስቶ ማየት እንደማይሹ ተናገሩ።

የቤተሰብ አባላቱ ለቢቢሲ ሲናገሩ የፈረንሳይ ፖሊስ አላስፈላጊ ኃይል መጠቀም ያቆም ዘንድ ምኞታቸው እንደሆነ ገልጸዋል።

ባለፈው ማክሰኞ ናሄል ኤም የትራፊክ ቁም ምልክት ጥሶ ሊያልፍ ሲሞክር በቅርብ ርቀት በጥይት ተመትቶ ነው የተገደለው።

“እኛ አመፅ ይነሳ አሊያም ጥላቻ ይስፋፋ አላልንም” ይላሉ የሟች ዘመድ።

ናንቴር በተሰኘችው የፓሪስ ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆኑት የልጁ ቤተሰቦች ናሄልን ለመዘከር አመፅ ጥቅም ላይ መዋል የለበትም ባይ ናቸው።

በታዳጊው ግድያ ምክንያት በተነሳ አመፅ በርካታ ሰዎች ሲታሰሩ ብዙ ንብረት ወድሟል።

“እኛ ንብረት ይውደም አሊያም ይሰረቅ አላልንም። ይሄ ሁሉ ለናሄል አይደለም” ይላሉ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የናሄል ዘመድ አዝማዶች።

አክለው “እኛ የጠራነው ሰልፍ ነው። የመንገድ ሰልፍ። ንዴታችንን ለመግለጥ፥ ሰላማዊ ተቃውሞ ማካሄድ እንጂ አመፅ አይደለም።”

የሟች ቤተሰቦች እንደሚሉት የፈረንሳይ ባለሥልጣናት፤ ትራፊክ መብራት ላይ አልቆም ያለን ፖሊስ ሊተኩሰበት ይችላል የሚለውን ሕግ መቀየር ይገባቸዋል።

የናሄል ቤተሰቦች የፈንሳይ ፖሊስ ኃይል “የተሻለ ሥልጠና ሊሰጠው ይገባል” ብለው ያምናሉ።

“የፖሊስ መሣሪያ ቁጥጥር እና ቁም የሚል ምልክት የሚጥሱ ታዳጊዎች ላይ ፖሊስ የሚጠቀመው ከመጠን በላይ የሆነ ኃይል ሊታሰብበት ይገባል።”

ፈረንሳይ በፈረንጆቹ 2017 የቀየረችው ሕግ ፖሊስ ኃይል እንዲጠቀም የሚፈቅድ ነው።

ተቃዋሚዎች ፖሊስ የትራፊክ ሕግን የሚጥሱ ሰዎችን እየገለደ ያለው በዚህ ሕግ ምክንያት ነው ብለው ያምናሉ።

ምክንያቱም አንድ አሽከርካሪ አልቆም ካለ አደጋ ነው አይደለም የሚለውን የሚወስነው በሕጉ መሠረት ፖሊስ ነው።

በዚህ ዓመት ሶስት ሰዎች የትራፊክ ሕግ በመጣሳቸው በፖሊስ ተገድለዋል።

ባለፈው ዓመት ግን እስከዛሬ ታይቶ በማይውቅ ሁኔታ 13 ሰዎች የትራፊክ ሕግ ጥሰዋል ተብለው በፖሊስ ተገድለዋል።

ሮይተርስ የዜና ወኪል እንደሚለው አብዛኛዎቹ የፖሊስ ጥይት ሰለባ የሆኑት ግለሰቦች ጥቁር አሊያም የአራብ ዘር ያለባቸው ናቸው።

የሟች ቤተሰብ ጎረቤት እና ጓደኛ የሆነው አናይስ በፈረንሳይ ክፍለ ከተማዎች ውስጥ ጥቁር ሆኖ መኖር ማለት ለዘረኝነት መጋለጥ አሊያም ለግጭት መዳረግ ነው ይላል።

የናሄል ዘመድ እንደሚሉት በተከሰተው አመፅ ሳቢያ ቤተሰቡ አረፍ ብሎ ሐዘኑን መወጣትና ታዳጊውን መዘከር አልቻለም።

እሑድ ጠዋት የናሄል አያት [የእናቱ እናት] አመፀኞች የልጃቸውን ሞት በጎ ላልሆነ ተግባር እንዳይጠቀሙበት ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።