የጦርነት ወንጀል መዝጋቢዋ ዩክሬናዊት ፀሐፊ በሩሲያ ሚሳኤል ጥቃት ተገደለች

ቪክቶሪያ አሜሊና

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በፅሑፎቿ እውቅናና ሽልማት ያጋበሰችው ዩክሬናዊቷ ቪክቶሪያ አሜሊና በሩሲያ የሚሳዔል ጥቃት ሕይወቷ አለፈ።

ማክሰኞ ዕለት በክራማቶርስክ ከተማ አንድ የፒዛ መሸጫ ውስጥ ሳለች ነው የሩሲያ ሚሳዔል ጥቃት የደረሰው።

የጦርነት ወንጀሎችን የምትመረምር ቪክቶሪያ በጥቃቱ ከሞቱ ሰዎች 13 ሰዎች መካከል አንዷ ሆናለች።

የፀሐፊዎች ማሕበር የሆነው ፔን ዩክሬን “ዶክተሮች ሕይወቷን ሊያድኑ የተቻላቸውን ቢያደርጉም ቁስሏ ከባድ ስለነበር ሳይቻላቸው ቀርቷል” ብሏል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ጥቃቱን የጦርነት ወንጀል ብለውታል።

ምስራቃዊቷ ክራማቶርስክ በዩክሬን ቁጥጥር ሥር ብትሆንም ሩሲያ ከያዘቻቸው ሥፍራዎች ብዙም አትርቅም።

የ37 ዓመቷ አሜሊና ከኮለምቢያዊያን ጋዜጠኞችና ፀሐፊዎች ጋር ሪያ ላውንጅ በተሰኘው መዝናኛ ሥፍራ እያወጋች ሳለ ነው ሚሳዔሉ የወደቀው።

በጥቃቱ 60 ያክል ሰዎች ከባድና ቀላል ጉዳት ደርሶባቸዋል።

ድኒፕሮ ወደሚገኝ ሆስፒታል በፍጥነት ብትወሰደም አርብ ዕለት በደረሰባት አደጋ ምክንያት መሞቷን ፔን ዩክሬን ገልጧል።

“ፀሐፊ ቪክቶሪያ አሜሊና ከዚህ ዓለም ሐምሌ 1/2023 መለየቷን ስንገልጥ በከባድ ሐዘን ነው” ብሏል ማሕበሩ።

“በመጨረሻዎቹ ቀናት ቤተሰቦቿና ጓደኞቿ ከጎኗ ነበሩ።”

አሜሊና ዩክሬን ውስጥ አሉ ከሚባሉ ወጣት ፀሐፊያን መካከል አንዷ የነበረች ሲሆን ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች በኋላ የጦርነት ወንጀሎችን መመዝገብ ጀምራ ነበር።

ከዚህ ባሻገር ጦርነት ያለባቸው ሥፍራዎች የሚገኙ ሕፃናትን መርዳት ጀምራ ነበር።

ባለፈው ዓመት የሕፃናት መፅሐፍ ፀሐፊው ቮሎድሚር ቫኩሌንኮ በሩሲያ ወታደሮች ታፍኖ መገደሉን ይፋ ያደረገችው አሜሊና ነበረች።

የመጀመሪያው እውነተኛ የጦርነት ታሪክ ላይ የተመረኮዘው መፅሐፏ በቅርቡ ይታተማል።

“እነሆ አሁን አሜሊና ራሷ የጦርነት ወንጀል ሰለባ ሆናለች” ብሏል ፔን ዩክሬን።

የአሜሊና የትዊተር ገፅ ከላይ የተሰቀለው ፎቶ በቦምብ የወደሙ ሕንፃዎችን ፎቶ ስታነሳ ያሳያል።

“እዚህ ፎተ ላይ የምታዩኝ እኔ ነኝ” ይላል መልዕክቱ።

“እኔ ዩክሬናዊት ፀሐፊ ነኝ። በቦርሳዬ የዩክሬናዊያን ገጣሚዎችን ስዕል ይዣለሁ። የመፃሕፍትን ፎቶ ማንሳት ያለብኝ ሰው መስላለሁ። ነገር ግን የሩሲያን የጦርነት ወንጀል መዘግባለሁ። የግጥም ሳይሆን የጦር መሣሪያ ድብደባን አደምጣለሁ። ለምን?”