በዕድሜ የገፉት አፍሪካዊው መሪ 40ኛ ዓመት የስልጣን ዘመናቸውን አከበሩ

ፖል ቢያ ወደ ስልጣን የመጡት እአአ በ1982 ነበር

የፎቶው ባለመብት, AFP

በአፍሪካ አንጋፋው ፕሬዝዳንት እና በአህጉሪቱ ለረዥም ጊዜ ስልጣን ተቆናጠው ከሚገኙ መሪዎች አንዱ የሆኑት ፕሬዝዳንት ፖል ቢያ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የስልጣን ዘመናቸውን 40ኛ ዓመት አክብረዋል።

በሃገር አቀፍ ደረጃ የመታሰቢያ ዝግጅቶች የተከናወኑ ሲሆን ደጋፊዎቹ ያስመዘገቡትን ውጤት እያከበሩ ናቸው።

የ89 ዓመቱ ፕሬዝዳንት ተቃዋሚዎች ግን በዚህ ደስተኛ አይመስሉም። ይልቁንም ሥልጣናቸውን ለወጣቱ ትውልድ እንዲያስረክቡ እየጠየቁ ነው።

የቢያ የረዥም ጊዜ አገዛዝ ታላቅ ህልም እና ጉልህ ውድቀቶችን ያስተናገደ ነው።

ሙስና የካሜሩን ትልቁ ውድቀት ነው ሲሉ የትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የቀድሞ ኃላፊ እና የቀድሞው ፕሬዝዳንታዊ ዕጩ አኬሬ ሙና ተናግረዋል።

"በማዕድን ዙሪያ እነማን ናቸው የሚያመርቱት? ምንስ ያመርታሉ? ለሃገሪቱ ምን ይከፍላሉ? ዜጎች የሃገራቸውን ሃብት ስለሚፈስበት ጉዳይ መረጃ የማያገኙበት ምክንያት ምንድን ነው?" ሲሉ ይጠይቃሉ።

መንግሥት የእንግሊዘኛ ተናጋሪ በሆኑ ሁለት ክልሎች ውስጥም መራር ጦርነት በማድረግ ላይ ይገኛል። በዚህ ምክንያት ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ካሜሮናዊያን ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ እና በሺህዎች የሚቆጠሩ ሲቪሎች ተገድለዋል።

"የሃገሩን ስም ከዩናይትድ ሪፐብሊክ ወደ ላ ሪፐብሊክ ደ ካሜሩን ቀይሮታል። ይህም የካሜሩንን ፈረንሳይኛ ተናጋሪ ሪፐብሊክ በ1961 ከመቀላቀላችን በፊት ትጠራበት የነበረበት ስም ነው" ሲሉ አንድ ግለሰብ የእንግሊዘኛ ተናጋሪዎቹ (አንግሎፎን) ብዙሃኑ ፈረንሳይኛ ተናጋሪዎች ላይ ያላቸውን ቅሬታ ገልጸዋል።

ሌላ ግለሰብ ደግሞ "አገዛዙ ለመለወጥ ቢሞክር ጥሩ ነው" ትላለች። "ለምን ሴት አትመራም? ለምንድነው ኃላፊነቱን ለወጣት የማያስረክቡት” ብላለች።

ሌላኛው ደግሞ "ያደረገውን ትንሽ ነገር እናደንቃለን" ነገር ግን ቢያ "ሄደው ለማረፍ" ጊዜው አሁን ሲል ጠቁሟል።

ከተመለሱ ከጥቂት ዓመታት በፊት ፕሬዝደንት ቢያ ከረጅም ጊዜ የውጪ ቆይታቸው ተመልሰው ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፤ እንዲሞቱ የሚፈልግ ሰው ሌላ 20 ዓመታት መጠበቅ አንዳለበት ጠቁመዋል።