የምያንማር ወታደራዊ አገዛዝ አራት አክቲቪስቶችን በሞት ቀጣ

በሞት ከተቀጡት መካከል አንዱ ኮ ጂሚ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምያንማር ወደታራዊ አገዛዝ ለዲሞክራሲ የሚሟገቱ አራት የማኅበረሰብ አንቂዎችን [አክቲቪስቶችን] በሞት መቅጣቱ ተሰማ።

ምያንማር ውስጥ የሞት ቅጣት ሲፈፀም ይህ በዓመታት ውስጥ የመጀመሪያው እንደሆነ ተነግሯል።

የቀድሞው ሕግ አዋቂ ፍዮ ዜያ ታው፣ ፀሐፊ ኮ ጂሚ፣ ህላ ምዮ እና አንግ ቱራ ዛው የተባሉት ለዲሞክራሲ የሚሟገቱ አራት ሰዎች "የሽብር ወንጀል ፈጽማችኋል" ተብለው ተከሰው ነበር።

ባለፈው ሰኔ የአገሪቱ ወደታራዊ አገዛዝ የሞት ቅጣቱን ሊፈፀም እንደሆነ ሲያሳውቅ የዓለም መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።

የምያንማር ወደታራዊ አመራር በዲሞክራሲያዊ መንገድ በተመረጡት አን ሳን ሱ ቺን ላይ መፈንቅለ መንግሥት አድርጎ ሥልጣን የያዘው በፈረንጆቹ የካቲት 2021 ነበር።

ይህን ተከትሎ በአገሪቱ የተነሳው ሰፊ ተቃውሞ በወታደራዊው አገዛዙ እርምጃ እንዲገታ ሆኗል።

መፈንቅለ መንግሥቱን ተከትሎ የተቋቋመው የፖለቲካ ፓርቲ የሞት ቅጣቱን በፅኑ እንደሚቃወም አስታውቋል።

ፓርቲው የዲሞክራሲ አቀንቃኞች፣ የተለያዩ ብሔሮች የትጥቅ ትግል መሪዎች እንዲሁም የቀድሞው ገዥ ፓርቲ አባላትን ያቀፈ ነው።

የመንግሥት ልሳን የሆነው የቴሌቪዥን ጣቢያ፤ አራቱ ሰዎች የተቀጡት "አቅጣጫ በመስጠት፣ ከሌሎች ጋር በማበር ጭካኔ የተሞላበት የሽብር ጥቃት ለመፈፀም በማሴራቸው ነው" ሲል ዘግቧል።

ጣቢያው አራቱ የማኅበረሰብ አንቂዎች በአገሪቱ ፀረ-ሽብር ሕግ መሠረት በሞት እንደተቀጡ ቢናገርም የተገደሉበትን ቦታ ከመግለጽ ተቆጥቧል።

የተባበሩት መንግሥታት እንደሚለው ሚያንማር ውስጥ ለመጨረሻ ጊዜ የሞት ቅጣት የተፈፀመው በፈረንጆቹ 1988 ነው።

ከዚህ ቀደም ምያንማር የሞት ቅጣት ተግባራዊ የምታደርገው በስቅላት ነበር።

ቢቢሲ ሪፖርተር እንደዘገበው በሞት የተቀጡት ሰዎች ቤተሰቦች ግለሰቦቹ ታስረው ከነበረበት ማረሚያ ቤት በር ላይ ቆመው እየተጠባበቁ ይገኛሉ።

ከአንቂዎቹ መካከል የፍዮ ሚስት ባሏ በሞት እንደሚቀጣ እንዳልተነገራት ገልጻለች።

አራቱ ሰዎች የሞት ቅጣት የተወሰነባቸው ባለፈው ጥር በዝግ ችሎት ጉዳያቸው ከታየ በኋላ ነው።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የሰዎች ጉዳይ በዝግ ችሎት መታየቱ ኢ-ፍትሐዊና ግልፅነት የጎደለው ነው ሲሉ ተሟግተው ነበር።

የ41 ዓመቱ ፍዮ የቀደሞው ገዥ ፓርቲ ኤንኤልዲ አባልና የሳን ሱ ቺ የቅርብ ወዳጅ ነበር።

ወደ ፖለቲካ ከመግባቱ በፊት የሂፕ ሆፕ ዘውግ አቀንቃኝ የነበረው ፍዮ በግጥሞቹ ፀረ-ወደታራዊ መልዕክቶችን በማስተላለፍ ይታወቃል።

የ53 ዓመቱ ኮ ጂሚ ደግሞ የአንድ የዲሞክራሲ አቀንቃኝ ንቅናቄ ነባር አባል ሲሆን የሚያንማርን ወታደራዊ አገዛዝ አጥብቆ በመቃወም ይታወቃል።

ስለተቀሩት ሁለቱ ግለሰቦች ብዙም የሚታወቅ ነገር የለም።

ሁለቱ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር የዋሉት የጁንታው መረጃ አቀባይ የነበረች ሴት ገድለዋል በሚል ተጠርጥረው ነው።

የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የሞት ቅጣቱን "በሕይወት የመኖር መብትን እንዲሁም ነፃነትንና የግለሰብ ደኅንነት መብትን የጣሰ ነው" ብለውታል።

ወታደራዊው አገዛዝ የታጠቁ ኃይሎችና ተቃዋሚ ፓርቲዎች ላይ የሚወስደውን እርምጃ አጠናክሮ ቀጥሏል።

ከመፈንቅለ መንግሥቱ በኋላ አን ሳን ሱ ቺ ሙስናን ጨምሮ በተለያዩ ወንጀሎች በቤት ውስጥ እሥር ላይ ይገኛሉ።

የቀድሞዋ መሪ ላይ የቀረበው ክስ በሃገሪቱ ሕግ መሠረት እስከ 150 ዓመት እሥር ሊያስቀጣቸው የሚችል ነው።

በወታደራዊ መንግሥት የተፈፀሙ ጥፋቶችን የሚመዘግብ አንድ ድርጅት ከመፈንቅለ መንግሥቱ ጀምሮ 14 ሺህ 847 ሰዎች ታሥረዋል፤ 2114 ሰዎች ደግሞ ተገድለዋል ይላል።