ፌስቡክ የቻይናውን ፕሬዝደንት ስም ሲተረጉም በአፀያፊ መልኩ በማንሻፈፉ ይቅርታ ጠየቀ

የፎቶው ባለመብት, AFP
ፌስቡክ የቻይናው ፕሬዝደንት ዢ ጂንፒንግን ስም ከበርማ ቋንቋ ወደ እንግሊዝኛ ሲተረጉም በማንሻፈፉ ይቅርታ ጠይቋል።
የቻይናው ፕሬዝደንት ወደ ምያንማር አቅንተው ይፋዊ የሥራ ጉብኝት እያደረጉ ባሉበት ወቅት ነው ይህ የተከሰተው። በጉብኝታቸው መሠረትም ዢ ከምያንማር መሪ አንግ ሳን ሱ ኪ ጋር መክረዋል።
የምያንማር ቋንቋ በሆነው በርሚዝ የሁለቱ መሪዎች መገናኘት ዜና ተፅፎ ወደ እንግሊኛ ሲተረጎም ነው የቻይናው ፕሬዝደንት ስም ተንሻፎ የተገኘው።
የቻይናው ፕሬዝደንት ዢ ጂንፒንግን ስም ወደ እንግሊዝኛ ሲገለበጥ 'ሺትሆል' ወይም 'ቆሻሻ ሥፍራ' ተብሎ ተነቧል። ይህን ደግሞ የለጠፉት የሳን ሱ ኪ ሰዎች ናቸው።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ይህን ያስተዋለው ፌስቡክ እክሉን ካስወገደ በኋላ መንሻፈፉ የተከሰተው በቴክኒካዊ ብልሽት ነው ብሏል። ወደፊት መሰል ጥፋት እንዳይፈፀም እተጋለሁ ብሏል ፌስቡክ።
በርሚዝ የምያንማር ኦፌሴላዊ ቋንቋ ሲሆን ሁለት ሶስተኛው የሃገሪቱ ሰው ይጠቀመዋል ተብሎ ይገመታል።
የዢ ስም ቋቱ ውስጥ እንዳልገባ ያመነው ፌስቡክ፤ ትርጉም አመንጪው ቴክኖሎጂ በግምት የገጣጠማቸው ቃላት የፈጠሩት ስህተት ነው ብሏል።
በምያንማር መንግሥት የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰዎች የተለጠፈው ሃተታ እንዲነሳ መደረጉም ታውቋል። ምንም እንኳ ቻይና ፌስቡክ ባይኖራትም የተንሻፈፈው ትርጉም ቻይና ውስጥ እንዳይሰራ መደረጉም እየተዘገበ ነው።
የቻይና መንግሥት የመረጃ ፍሰትን በመገደብ ይታማል። የሃገሪቱ ፕሬዝደንት ወደ ምያንማር ያቀኑት ስለ ሁለትዮሽ ግንኙነቶች ለመወያየት ነው ተብሏል።
የምያንማሯ መሪ ሳን ሱ ኪ የኖቤል ሰላም ሽልማት አሸናፊ ሲሆኑ የሮሂንጃ ሙስሊሞች ላይ በደረሰ ጥፋት ተወንጅለው ባለፈው ወር ፍርድ ቤት መቆማቸው አይዘነጋም።













