ቻይና ግዙፉን አዲስ አየር ማረፊያዋን ከፈተች

የፎቶው ባለመብት, AFP
አስራ አንድ ቢሊየን ዶላር የወጣበት አዲሱ የቻይና አየር ማረፊያ አገልግሎት ለመስጠት ተከፈተ።
በዋና ከተማዋ ቤይጂንግ ውስጥ የሚገኘው ይህ ዳዢንግ ተብሎ የሚጠራው ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ዛሬ ተመርቆ የተከፈተው በሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ነው።
አየር ማረፊያው 700 ሺህ ስኩየር ሜትር ስፋትን የሚሸፍን ሲሆን ይህም 98 የእግር ኳስ ሜዳዎችን እንደሚሸፍን የሃገሪቱ መንግሥት ዕለታዊ ጋዜጣ ቻይና ዴይሊ ዘግቧል።
የአየር መንገዶችን ደረጃ የሚመዘግበው ኤርፖርት ካውንስል እንደሚለው አሁን ቤይጂንግን እያገለገለ የሚገኘው አየር ማረፊያ ከአሜሪካው አትላንታ አየር ማረፊያ ቀጥሎ ብዙ አውሮፕላኖችን የሚያስተናግድ ነው።
የቻይና ባለስልጣናት እንዳሉት አዲሱ አውሮፕላን ማረፊያ ያስፈለገው የነበረው አውሮፕላን ማረፊያ ያለበትን ከፍተኛ መጨናነቅ ለመቀነስ ነው።
በታዋቂ አርክቴክት የታነጸው ዳዢንግ አየር ማረፊያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ይህ አዲሱ ዳዢንግ አውሮፕላን ማረፊያ በአንድ ህንጻ ውስጥ ትልቅ የመንገደኞች ማስተናገጃ በመያዙ ቀዳሚ ይሆናል ተብሏል። ይህ አውሮፕላን ማረፊያ ከአምስት ዓመት በኋላ ወደ ቤይጂንግ ይመጣሉ ተብለው ከሚጠበቁት መንገደኞች መካከል 170 ሚሊዮኖቹን ያስተናግዳል ተብሎ ይጠበቃል።
ከትላልቆቹ ዓለም አቀፍ አየር መንገዶች በተጨማሪ ሰባት ያህል የሃገር ውስጥ አየር መንገዶች ከዛሬ ጀምሮ ከዚህ ከአዲሱ አየር ማረፊያ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምሩ ተነግሯል።
መሃል ቤይጂንግ ከሚገኘው የታይናሚን አደባባይ በስተደቡብ 46 ኪሎ ሜትሮች እርቆ የሚገኘው የአዲሱ አየር ማረፊያ ንድፍ የተዘጋጀው በትውልድ ኢራቃዊ በዜግነት እንግሊዛዊ በሆነችው በእውቋ አርክቴክት ዛሃ ሃዲድ ነው።
ይህ አየር ማረፊያ ሲከፈት ቤይጂንግ ለንደንና ኒው ዮርክን የሚገኙበትን ግዙፍ አቀፍ አየር ማረፊያ ካላቸው ዓለም ከተሞችን ተቀላቅላለች።
እንደ አውሮፓዊያኑ በ1958 የተከፈተው ቤይጂንግ ካፒታል የሚባለው ነባሩ አውሮፕላን ማረፊያ ከ100 ሚሊዮን በላይ መንገደኞች ተጠቅመውበታል።












