ኢትዮጵያውያን ሴት አትሌቶች ደምቀውበት ያለፈው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮን

ጉዳፍ ጸጋዬ፣ ለተሰንበት ግድይ እና ጎተይቶም ገ/ስላሴ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ከግራ ወደ ቀኝ ጉዳፍ ጸጋዬ፣ ለተሰንበት ግድይ እና ጎተይቶም ገ/ስላሴ

በአሜሪካዋ ግዛት ኦሪገን፣ ዩጂን ከተማ ውስጥ ሲካሄድ በሰነበተው 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ውድድር ላይ ሴት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ታሪክ በማስመዝገብ ደምቀው ታይተዋል።

ኢትዮጵያ በውድድሩ ካስመዘገበቻቸው 10 ሜዳሊያዎች 7ቱ የተመዘገቡት በተለያዩ ርቀቶች በተሳተፉ ሴት አትሌቶች አማካይነት የተገኙ ናቸው።

ኢትዮጵያ በ4 የወርቅ፣ በ4 የብር እና በ2 የነሐስ ሜዳሊያዎች ከአፍሪካ አንደኛ ከዓለም ደግሞ ከአሜሪካ በመቀጠል ሁለተኛ ሆና ውድድሩን አጠናቃለች።

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በዓለም የአትሌቲክስ ሻምፒዮን በርካታ ሜዳሊያዎች ሲያስመዘግቡ ይህ የመጀመሪያው ነው።

3 ወርቅ

ጉዳፍ ፀጋይ በ5 ሺህ ሜትር፣ ለተሰንበር ግደይ በ10 ሺህ ሜትር እንዲሁም ጎተይቶም ገ/ሥላሴ በማራቶን ኢትዮጵያ ካስመዘገበቻቸው 4 የወርቅ ሜዳሊያዎች ሦስቱን ማስገኘት ችለዋል።

ቀሪ አንድ የወርቅ ሜዳሊያ የተገኘው በወንዶች የማራቶን ውድድር በታምራት ቶላ አማካይነት ነው።

ከ4ቱ የብር ሜዳሊያዎች ሁለቱን ያጠለቁት ጉዳፍ ፀጋይ እና ወርቅውሃ ጌታቸው ናቸው። ይህም ጉዳፍ በ1 ሺህ 500 ሜትር፤ ወርቅውሃ ደግሞ በ3 ሺህ ሜትር መስናክል።

የተቀሩትን ሁለት የብር ሜዳሊያዎች ለሜቻ ግርማ በ3 ሺህ ሜትር መሰናክል እንዲሁም ሞሰነት ገረመው በማራቶን ለአገራቸው አስመዝግበዋል።

ሁለቱ የነሐስ ሜዳሊያዎች የተመዘገቡት በሁለት ሴት አትሌቶች ነው። ዳዊት ስዩም በ5 ሺህ ሜትር እንዲሁም መቅደስ አበበ በ3 ሺህ ሜትር።

ወርቅ ያስመዘገቡት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በውድድሩ ከፍተኛ ብቃታቸውን ከማሳየታቸው ባሻገር የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናንም ክብረ ወሰን ለማሻሻል በቅተዋል።

በታዋቂዋ ሴት አትሌት እየተመራ ያለው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ደራርቱ ቱሉ እና በኦሬጎን በ10ሺህ ሜትር ወርቅ ያስገኘችው አትሌት ለተሰንበት ግደይ
የምስሉ መግለጫ, የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ደራርቱ ቱሉ እና በኦሬጎን በ10ሺህ ሜትር ወርቅ ያስገኘችው አትሌት ለተሰንበት ግደይ

ደራርቱ ቱሉ ያለፉትን ጥቂት ዓመታት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሽንን በበላይነት ስትመራ ቆይታለች።

በተለያዩ የአትሌቲክስ መድረኮች ላይ የአገሯን ስም ያስጠራችው ደራርቱ፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ሆና ከተመረጠች በኋላ፣ ይህ የኦሪገኑ ሻምፒዮና ከፍተኛ ውጤት የተመዘገበበት ዓለም አቀፍ ውድድር ነው።

ደራርቱ ፌዴሬሽኑን መምራት ከጀመረች ወዲህ ሁለት ጊዜ በዓለም ሻምፒዮና፤ አንድ ጊዜ በኦሊምፒክ መድረክ፤ አንድ ጊዜ ደግሞ በዓለም የቤት ውስጥ ውድድር ኢትዮጵያ ተሳታፊ ሆናለች።

በኳታር ዶሃ በተሰናደው የ2019 የዓለም ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ሁለት ወርቅ፣ አምስት ብርና አንድ ነሐስ ይዛ ተመልሳለች።

በዚህ ውድድር የኢትዮጵያ አትሌቶች በሚታወቁበት የመካከለኛና ረዥም ርቀት ውድድር ተለመደውን ወርቅ ማስመዝገብ ባይችሉም ተስፋ ያላቸው አትሌቶች ታይተው ነበር።

ኢትዮጵያ በመድረኩ በስምንት ሜዳሊያ አምስተኛ ደረጃ ይዛ አጠናቀቀች።

ከዚህ በኋላ በደራርቱ የተመራው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ታላቅ ወደ ሚባለው የኦሊምፒክ መድረክ ነው ያቀናው።

በ2022 ቶኪዮ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ ያገኘችው ሜዳሊያ ብዛት አራት ነው። ይህ ውጤት ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ መድረክ ካመጣቻቸው ዝቅተኛ ከተባሉት የሚመደብ ነው።

ቀጥሎ ኢትዮጵያ የተሳተፈችበት ዓለም አቀፍ መድረክ ባለፈው መጋቢት የተካሄደው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ፍልሚያ ነው።

ይህ መድረክ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ደምቀው የታዩበት ነበር።

ኢትዮጵያ፤ በአራት ወርቅ፣ በሦስት ብርና በሁለት የነሐስ አሜሪካን አስከትላ ከዓለም ሁለተኛ ሆና አጠናቃለች።