ማሌዢያ ውስጥ አንድ የግል አውሮፕላን በመኪና መንገድ ላይ ተከስክሶ 10 ሰዎች ሞቱ

በማሌዢያ የደረሰው አደጋ

የፎቶው ባለመብት, EPA/EFE/REX/SHUTTERSTOCK

አንድ የግል አውሮፕላን በመኪኖች መንገድ መሐል ላይ ተከስክሶ ከመኪና እና ከሞተር ሳይክል ጋር በመላተሙ 10 ሰዎችን መሞታቸውን የማሌዢያ ፖሊስ ገለጸ።

በአደጋው አውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩ ስምንት ሰዎች እና ሁለት መሬት ላይ የነበሩ አሽከርካሪዎች ናቸው ሕይወታቸው ያለፈው።

አውሮፕላኑ ከመሬት ላይ ሲከሰከስ ሙሉ በሙሉ የፈንዳ ሲሆን፣ ከአደጋው ሥፍራ ከባድ ጥቁር ጭስ ወደ ሰማይ ሲነሳ ቪዲዮዎች አሳይተዋል።

አውሮፕላኑ ከማሌዢያዋ መዲና ኩዋላ ላምፑር ምዕራባዊ አቅጣጫ ላንግካዊ ከምትባለው የመዝናኛ ደሴት ወደ ሴላንጎር እተጓዘ ነበር ተብሏል።

ባለሙያዎች እንደሚሉት ቢችክራፍት 390 የተባለው ይህ አውሮፕላን ከመከስከሱ በፊት ከአየር ትራፊክ መቆጣጠሪያ ጋር የነበረውን ግንኙነት ተቋርጦ ነበር።

ምንም ዓይነት የአደጋ ጊዜ ጥሪ እንዳልደረሰ እና አውሮፕላኑ እንዲያርፍ ፈቃድ እንደተሰጠው ባለሥልጣናት አሳውቀዋል።

አነስተኛዋ አውሮፕላን ካሰፈረቻቸው ስምንት ሰዎች መካከል አንዱ የአካባቢው ፖለቲከኛ መሆናቸው ታውቋል።

ነገር ግን የአገሪቱ የትራንስፖርት ሚኒስትሩ አንተኒ ሎኬ የሟቾቹ ማንነት በአስከሬን ምርመራ ተረጋግጦ እስኪመጣ ድረስ መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

አውሮፕላን አብራሪው ሻህሩል ካማል ሮስላን ባለትዳር እና የአራት ወንድ ልጆች አባት ሲሆን፣ በአደጋው ሕይወቱን አጥቷል።

የማሌዢያ ሲቪል አቪየሽን ባለሥልጣን የመጀመሪያው ደረጃ ምርመራ እንደሚጠቁመው አውሮፕላኑ እንዲነሳ ፈቃድ የተሰጠው ሲሆን፣ ሁለቱ አብራሪዎች ልምድ ያላቸው ናቸው።

መርማሪዎች የአውሮፕላኑን የበረራ መረጃ መመዝገቢያ ጥቁር ሳጥን አሊያም መረጃ መሰብሰቢያ ቋትን ለማግኘት ጥረት እያደረጉ ነው።

አንድ የዐይን እማኝ ለሮይተርስ የዜና ወኪል እንደተናገሩት ፍንዳታው ከደረሰ በኋላ ወደ ሥፍራው ሄደው የተጎዱ ሰዎችን አይተዋል።