የድሮን ጥቃት ማዕከላዊ ሞስኮ የሚገኝ ሕንፃ መታ

ማዕከላዊ ሞስኮው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የሞስኮው የንግድ ማዕከል በምሽት

ከዩክሬን የተቃጣ የድሮን ጥቃት ማዕከላዊ ሞስኮ የሚገኝ አንድ ሕንፃ መምታቱን የሩሲያ ባለሥልጣናት ገለጡ።

በጥቃቱ ምክንያት የደረሰው ፍንዳታ በከተማዋ የንግድ ልውውጥ በሚደረግበት ሥፍራ ከፍተኛ ድምፅ ፈጥሯል።

የሞስኮው ከንቲባ ሰርጌ ሶብያኒን የአየር መቃወሚያ አንድ ድሮን መትቶ ጥሎ የድሮን ስብርባሪ በከተማዋ ‘ኤክስፖር ማዕከል’ ላይ ወድቋል።

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የሩሲያ መዲና ሞስኮ ላይ የድሮን ጥቃቶች እየደረሱ ነው።

ማሕበራዊ ሚድያ ላይ የተለጠፉ ያልተጣሩ ምስሎች ጥቁር ጭስ ከአንድ ሕንፃ ላይ እየተንቦገበገ የሞስኮን ሰማይ ሲያጠቁር ያሳያሉ።

ዩክሬን እስካሁን ስለጥቃቱ ያለችው ነገር የለም።

የሩሲያ መከላካይ ሚኒስቴር በቴሌግራም ገፁ እንዳለው ጥቃቱ የደረሰው በሃገሪቱ አቆጣጠር ከንጋት 10 ሰዓት በኋላ ነው።

ሚኒስቴሩ እንዳለው የአየር መቃወሚያ ድሮኑ ከመኖሪያ ሰፈሮች ይልቅ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ወደሚገኙበት የሞስኮው ክፍል እንዲሄድ አድርጎታል።

አክሎ እስካሁን ምንም ዓይነት ጉዳት ሰው ላይ አለመድረሱን አሳውቋል።

ኤክስፖ ማዕከል የሚባለው የተለያዩ ስብሰባዎችና ኮንፈረንሶች የሚካሄዱበት ትልቅ አዳራሽ ሲሆን ከክሬምሊን 5 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ነው።

በሥፍራው የነበረ አንድ የዓይን እማኝ ጥቃቱ “በጣም ኃይለኛ ፍንዳታ አሰምቷል” ሲል ለሮይተርስ ዜና ወኪል ተናግሯል።

የሩሲያ መከላካይ ሚኒስቴር የድሮኑ ስብርባሪ ምንም ዓይነት እሣት አላስነሳም ሲል ከንቲባው በበኩላቸው ጥቃቱ “ይህ ነው የሚባል ጉዳት አላደረሰም” ብለዋል።

ታስ የተባለው የሩሲያ መንግሥት የዜና ወኪል፤ የማዕከሉ አንደኛው የውጭ ግድግዳ በከፊል ተጎድቶ መውደቁን የአደጋ ጊዜ ሠራተኞችን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።

ዘገባው አክሎ አደጋ የደረሰበት አካባቢ 30 ስኩዌር ሜትር የሚጠጋ ሥፍራ ነው ብሏል።

የሞስኮ ቭንኮቮ አየር ማረፊያ ከጥቃቱ በኋላ በጊዜያዊነት አገልግሎት ያቋረጠ ሲሆን ታስ እንደዘገባው አየር ማረፊያ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ድጋሚ ተከፍቷል።

እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ሞስኮ በዩክሬን ጦርነት ምክንያት ምንም ዓይነት ጥቃት ደርሶባት አያውቅም ነበር። ነገር ግን ከያዝነው የፈረንጆቹ ዓመት ጀምሮ የድሮን ጥቃት እየደረሰባት ነው።

ባለፈው ግንቦት 30 በርካታ ሕንፃዎች በተደጋጋሚ በደረሱ የድሮን ጥቃቶች መጎዳታቸው ተዘግቦ ነበር።

በተመሳሳይ ሐምሌ 30 እና 31 ከኤክስፖርት ማዕከሉ ብዙም ሳይርቅ የሚገኝ አንድ ሰማይ ጠቀስ ሕንፃ በድሮን ተመትቶ እንደነበር ይታወሳል።

በወቅቱ የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ጦርነቱ “ወደ ሩሲያ ድንበር እየተመለሰ ነው” የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።