የፖፕ ኮከቧ ብሪትኒ ስፒርስ ከ14 ወራት ትዳር በኋላ ከባሏ ተለያየች

ብሪትኒ ስፒርስና ሳም አስጋሪ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የፖፕ ሙዚቃ ዘውግ ኮከቧ ብሪትኒ ስፒርስ ከ14 ወራት ትዳር በኋላ ከሳም አስጋሪ ጋር ፍቺ ፈፅማለች ሲሉ የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።

ጥንዶቹ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙት ብሪትኒ ስፒርስ በአውሮፓውያኑ 2016 አንድ የሙዚቃ ቪድዮ ስትሠራ ነው።

ብሪትኒ እና ሳም ጋብቻቸውን አነስ ባለ እና በታዋቂ ሰዎች በተከበበ ሥነ-ሥርዓት ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ ነበር የፈፀሙት።

የ29 ዓመቱ አስጋሪ፤ የ41 ዓመቷ ታዋቂ ሙዚቀኛ የአእምሮ ጤና ሕክምና ስታገኝ እና ከአባቷ ቁጥጥር ነፃ ስትወጣ አብሯት ነበር።

ነገር ግን ጥንዶቹ ትዳራቸው እየተንገዳገደ እንደሆነ የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ሲዘግቡ ቆይተዋል።

የብሪትኒ ስፒርስም ሆነ የሳም አስጋሪ ተወካዮች ስለፍቺው እስካሁን አስተያየት አልሰጡም።

ቲኤምዚ የተሰኘው ታዋቂ ሰዎች እያሳደደ ዘገባ የሚሠራ ጣቢያ ዜናውን ይፋ ሲያደርግ፤ አሶሺየትድ ፕሬስ ደግሞ ምንጩን ዋቢ አድርጎ አስጋሪ የፍቺ ወረቀት እንዳስገባ አስነብቧል።

ኢራናዊ አሜሪካዊው ሞዴል እና የአካላ ብቃት አሠልጣኝ አስጋሪ፣ የፖፕ ሙዚቃ ኮከቧ ስፒርስን የተዋወቃት ስላምበር ፓርቲ ለተሰኘ ሙዚቃዋ ቪድዮ ክሊፕ ስትቀርፅ ነው።

አባቷ ጄሚ የብሪትኒ ስፒርስን ሕይወት ተቆጣጥሮ ከእሱ ቁጥጥር ለመውጣት በምታደርገው ጥረት ትልቅ ሚና ተጫውቷል።

አስጋሪ ‘ብሪትኒ ነፃ ትውጣ’ የሚል ቲ-ሸርት አሠርቶ በኢንስታግራም ገፁ ቅስቀሳ ሲያደርግም ነበር።

አስጋሪ ለብሪትኒ ስፒርስ የእንጋባ ጥያቄ ያቀረበላት መስከረም 2021 (እአአ) ቤታቸው ውስጥ ነው።

ጋብቻ ከመፈፀማቸው በፊት ጥንዶቹ የመጀመሪያ ልጃቸውን ሊቀበሉ ዝግጅት ላይ እንዳሉ ቢገልጹም የኋላ ኋላ በእርግዝና ችግር ምክንያት ሕልማቸው እውን ሳይሆን እንደቀረ አሳውቀዋል።

'ታውዘንድ ኦክስ' በተሰኘው የካሊፎርኒያ መንደር የተሰናዳው የጋብቻ ሥነ-ሥርዓት እነ ማዶና፣ ፓሪስ ሒልተን እና ድሩ ባሪሙር የተጋበዙበት ነበር።

ነገር ግን በቅርቡ ጥንዶቹ የጋብቻ ቀለበታቸውን አውልቀው መታየታቸው ለሐሜት በር ከፍቷል።

ብሪትኒ እስካሁን እየተዘገበ ስላለው ፍቺ በማኅበራዊ ገፆቿ ያለችው ነገር የለም። ለመጨረሻ ጊዜ የለጠፈችው ጽሁፍ ፈረስ ለመግዛት መሰናዳቷን የሚገልጽ ነው።

ብሪትኒ 'ዘ ውማን ኢን ሚ' የተሰኘ የሕይወት ታሪኳን የሚተነትን መፅሐፍ ልታሳታም እየተዘጋጀች ሳለ ነው የፍቺ ወሬ መሰማት የተጀመረው።

የፖፕ ኮከቧ ብሪትኒ ከዚህ ቀደም ከልጅነት ጓደኛዋ ጄሰን አሌክሳንደር ጋር ትዳር ፈፅማ በ55 ሰዓት ውስጥ ፍቺ መፈጸሟ ይታወሳል።

ከዚያ በኋላ ደግሞ ከራፐሩ ኬቪን ፌዴርሊን ጋር ከ2004 እስከ 2007 (እአአ) በትዳር ቆይታለች።

ብሪትኒ ስፒርስ ከኬቪን ጋር በነበራት ትዳር ሁለት ልጆች አፍርታለች።