በፓኪስታን ቅዱስ ቁርዓን ተራክሷል በሚል አብያተ ክርስቲያናት ተቃጠሉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በፓኪስታን ሁለት ግለሰቦች ቅዱስ ቁርዓንን አራክሰዋል በሚል በሺዎች የሚቆጠሩ የእስልምና እምነት ተከታዮች አብያተ ክርስቲያናትን ማቃጠላቸውን ፖሊስ አስታወቀ።
በተጨማሪም የክርስቲያኖች የተባሉ መኖሪያ ቤቶችን አውድመዋል ተብሏል።
ጥቃቱ የተፈጸመው በምስራቃዊቷ ፑንጃብ ግዛት ጃራንዋላ በተሰኘችው ከተማ ነው።
ፖሊስ ቢያንስ አራት አብያተ ክርስቲያናት መቃጠላቸውን ገልጿል።
ነዋሪዎች በበኩላቸው ከአብያተ ክርስቲያናቱ ጋር የተያያዙ እስከ 12 የሚደርሱ ህንጻዎች መጎዳታቸውን ተናግረዋል።
በፓኪስታን የእስልምና እምነትን ማራከስም ሆነ ማንቋሸሽ እስከ ሞት ያስቀጣል።
ምንም እንኳን ፍርድ ቤቶች የሞት ቅጣትን ተፈጻሚ ባያደርጉም ከዚህ ቀደም እምነቱን አንቋሸዋል በሚል በርካቶች ለደቦ የሞት ፍርድ ተዳርገዋል።
ፓኪስታን አብዛኛው ሕዝቧ የእስልምና እምነት ተከታይ ሲሆን ከ96 በመቶ በላይም እንደሆነ ይታመናል።
ሁለት ግለሰቦች ቁርዓንን አራክሰዋል የሚሉ ዘገባዎች በማኅበራዊ ሚዲያዎች በስፋት መጋራታቸውን ተከትሎ ረቡዕ ማለዳ ተቃውሞዎችና የእሳት ቃጠሎዎች ስለመፈጸማቸው ጥሪ እንደደረሳቸው አንድ የአካባቢው ባለስልጣን ለቢቢሲ ኡርዱ ተናግረዋል።
እነዚህ ግለሰቦች የእስልምና ቅዱስ መጽሐፍ የሆነው የቁርዓን ገጾች ላይ በቀይ ቀለም የሚያንቋሽሽ ጽሑፎች ጽፈው መገኘታቸውን ፖሊስን ዋቢ አድርጎ ሮይተርስ ዘግቧል።
የክርስትና እምነት ተከታይ የሆነው የ31 ዓመቱ ያሲር ባቲ በአሁኑ ወቅት ጥቃት ካስተናገዱት አንዱ ነው።
“የቤቴን መስኮቶች፣ በሮች ሰብረው ፍሪጅ፣ ሶፋ፣ ወንበሮች እና ሌሎች የቤት ቁሳቁሶችን አወጡ። ከዚያም ከቤተ ክርስቲያኑ ፊት ለፊትም ከምረው አቃጠሏቸው” ሲል ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ተናግሯል።
“መጽሐፍ ቅዱሶችንም አራክሰው አቃጠሉ። ምንም ምህረት የሚባል አልነበራቸውም” ብሏል።
በማኅበራዊ ድረ-ገጾች ላይ የተጋሩ ቪዲዮዎች እነዚህ ተቃዋሚዎች የክርስቲያን ህንጻዎችን ሲያወድሙ እና ፖሊስም ዝም ብሎ ሁኔታውን ሲመለከት አሳይተዋል።
የፑንጃብ ግዛት የማስታወቂያ ሚኒስትር አሚር ሚር በቁርዓን ላይ ተፈጸመ የተባለውን ማራከስ አውግዘው በሺዎች የሚቆጠሩ ፖሊሶች ማሰማራታቸውንና በርካታ ግለሰቦችም በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን በመግለጫቸው አስታውቀዋል።
አብያተ ክርስቲያናቱን ሲያቃጥል የነበሩት አብዛኞቹ ተህሪክ ኢ ለባይክ ፓኪስተን (ቲኤልፒ) ከተሰኘው እስላማዊ የፖለቲካ ፓርቲ የተውጣጡ መሆናቸውን የመንግሥት ምንጭ ለሮይተርስ ተናግረዋል።
ቲኤልፒ በበኩሉ በዚህ ላይ ተሳትፎ አልነበረኝም ሲል ክሱን ውድቅ አድርጓል።












