ሳፋሪኮም የሞባይል የገንዘብ ማዘዋወሪያ አገልግሎቱን ኤም-ፔሳ በኢትዮጵያ ጀመረ

ሳፋሪኮም

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ኤም-ፔሳ የተባለውን በሞባይል የሚደረግ የገንዘብ ዝውውር አገልግሎቱን ዛሬ በይፋ ሥራ ሊያስጀምር ነው።

ሳፋሪ ኮም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፍቃድ በተሰጠው በሦስተኛው ወሩ ዛሬ ከሰዓት በኋላ 9 ሰዓት ላይ አገልግሎቱን በይፋ እንደሚጀምር አስታውቋል።

ሳፋሪኮም ባለፉት ሦስት ወራት ኤም-ፔሳን ወደ ሥራ ለማስገባ ባደረገው ዝግጅት የሙከራ ሥራዎችን ማከናወኑን፣ የቴክኒክ ዝግጁነቱን ማረጋገጡን፣ ከባንኮች ጋር ውል መፈጸሙን፣ ሠራተኞቹን ቀጥሮ ማሠልጠኑን እና የኤም-ፔሳ ወኪሎችን ማዘጋጀቱን አስታውቋል።

የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ እናት ድርጅት የሆነው ቮዳኮም ግሩፕ ሊሚትድ የኤም-ፔሳ አገልግሎቱን በመጪው ዓመት መስከረም 2016 ዓ.ም. አጋማሽ በኢትዮጵያ እንደሚጀምር ከዚህ ቀደም ገልጦ ነበር።

ሁሉም የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ደንበኞች *733# በመደወል የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉ የተገለጸ ሲሆን፣ መተግበሪያውም በአምስት ቋንቋዎች መዘጋጀቱን ድርጅቱ አሳውቋል።

ደንበኞች ኤም-ፔሳን በመጠቀም ወደ አገር ውስጥ ክፍያ መፈጸም፣ ከአገር ውስጥ እና ከውጭ ገንዘብ መቀበል፣ ለአገልግሎት ሰጪዎች ክፍያ መፈጸም፣ የአየር ሰዓት መግዛት፣ ከኤም-ፔሳ ወደ ባንክ ገንዘብ መላክ እንዲሁም ከባንክ ወደ ኤም-ፔሳ ገንዘብ ማዘዋወር ይቻላሉ ብሏል ግዙፉ የቴሌኮም ኩባንያው።

በአምስት ቋንቋዎች ተዘጋጅቷል የተባለው መተግበሪያ የአንድሮይድ ስልክ ተጠቃሚዎች መተግበሪያውን ከፕሌይስቶር በማውረድ መጠቀም እንደሚችሉ የተገለጸ ሲሆን፣ የአይኦኤስ ተጠቃሚ ደንበኞች ደግሞ መተግበሪያውን በቀጣዩ ሳምንታት ማግኘት ይችላሉ ተብሏል።

የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት ስታንሊ ንጆሮጌ ኤም-ፔሳ በኢትዮጵያ መጀመር አስደሳች መሆኑን ተናግረዋል።

ጨምረውም ይህ የሞባይል የገንዘብ ማዘዋወሪያ ሥርዓት በሰባት የአፍሪካ አገራት 51 ሚሊዮን ተጠቃሚዎች እንደሉት አስታውሰው፣ ኤም-ፔሳ ደኅንነቱ የተረጋገጠ የገንዘብ ማስተላለፊያ አገለግሎት መሆኑን ገልጸዋል።

እአአ ጥቅምት 2022 በኢትዮጵያ ሥራ የጀመረው ሳፋሪኮም በአገሪቱ ከ2.7 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች ማግኘቱን ኩባንያው ይገልጻል።

ባለፈው ግንቦት በሳፋሪኮም የሚመራው ኩባንያ የሞባይል ገንዘብ መላላኪያ ሥራ ለመጀመር ፈቃድ ያገኘ የመጀመሪያው የውጭ ድርጅት ሆኗል።

ለሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ኤም-ፔሳ የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ሰጪ ተቋም ፈቃድ የሰጠው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ነው።

ኤም-ፔሳ የሚሠራው እንዴት ነው?

ኤም-ፔሳ የተንቀሳቃሽ ስልክ የገንዘብ ልውውጥና ግብይት ሥርዓት ነው።

መሥራቹ የኬንያው የቴሌኮም ኩባንያ ሳፋሪኮም ሲሆን፤ አሁን ላይ በተለያዩ የአፍሪካ አገራት እየተተገበረ ይገኛል።

ኤም-ፔሳ ሰርዓት ከሲም ካርድ ጋር ከተያያዘ በኋላ ተጠቃሚዎች በስልካቸው አማካይነት ገንዘብ ማስቀመጥ፣ ገንዘብ መቀበል፣ ክፍያ መፈጸም፣ ከባንክ እና ወደ ባንክ ገንዘብን ማዘዋወር፣ ገንዘብ ለሌላ ኤም-ፔሳ ተጠቃሚ መላክ እና ሌላም የገንዘብ ልውውጥ ማካሄድ ይቻላሉ።

እአአ በ2007 በሳፋሪኮም እና ቮዳፎን የተጀመረው ኤም-ፔሳ፤ ኬንያ ውስጥ የሚተዳደረው በኬንያ ብሔራዊ ባንክ ነው።

ኤም-ፔሳ የሚለው መጠሪያ ውስጥ ኤም ሞባይልን ሲወክል፣ ፔሳ ደግሞ በስዋሂሊ ገንዘብ ማለት ነው።

የገንዘብ ልውውጥን የሚያሳልጡ የሳፋሪኮም ተወካዮች በተለያዩ መደብሮች ይገኛሉ። ለእነዚህ ተወካዮች ጥሬ ገንዘብ በመስጠት ወደ ኤም-ፔሳ ገንዘቡን እንዲያስገቡ ማድረግ ይቻላል።

በኤም-ፔሳ ተንቀሳቃሽ ስልክ ላይ ያለ ገንዘብን በጥሬ ገንዘብ ከተወካዮቹ የመውሰድ አማራጭም አለ።

በተለይ ኬንያ ውስጥ ከጉሊት አንስቶ እስከ ቅንጡ ሆቴሎች ድረስ ክፍያ የሚፈጸመው በኤም-ፔሳ ነው።

50 በመቶ የሚሆነው የኬንያ አጠቃላይ አገራዊ ምርት (GDP) በዚሁ ሥርዓት በኩል ይንቀሳቀሳል።

ኢትዮ ቴሌኮም ገንዘብ ለመቀበል፣ ለመላክ፣ የግብይት እና የአገልግሎትን ክፍያን ለመፈጸም እንዲሁም ከውጭ አገራት ገንዘብ መቀበል የሚያስችለውን ቴሌ ብር ከሁለት ዓመት በፊት መጀመሩ ይታወሳል።